Sunday, March 29, 2015

የቀባኋቸውን አትዳስሱ – በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ!

ዲቮሽን . 200/07፣ እሁድ መጋቢት 20/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


የቀባኋቸውን አትዳስሱ – በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ!

የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ (1ዜና 16፡21-22፤ መዝ 105፡14-15)።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን፣ የተቀቡትን የዳሰሱ፣ በነቢያቱም ላይ ክፉ ያደረጉ ሰዎች በሕመም፣ በልዩ ልዩ መቅሰፍትና በሞት ተገስጸዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ወዳጅ ከሆነው ከአብርሃም ሚስቱን ሦራን የነጠቁ ነገሥታት በታላቅ መቅሰፍት ተመትተዋል፣ በታላቅ ግሳጼም ቅጣት ተቀብለዋል (ዘፍ 12፡17፤ 20፡3)፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በያዕቆብ ላይ ግፍ የሠራው ላባ የሠራው ግፍ ሳያንስ ከሚሸሽበት መንገድ አሳድዶ ሊመታው ሲገሰግስ ሳለ ጌታ በሌሊት ሕልም መጥቶ፣ ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳይናገረው አስጠንቅቆታል(ዘፍ 12፡17፤ 20፡3)፡፡ ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ያዕቆብ ከላባ አምልጦ ወደ ትውልድ ቀዬው በመመለስ ሳለ ኤሣው በቂም በቀል 400 ሰዎች አስከትሎ ያዕቆብን ለመግደል እየመጣ ሳለ መላእክቱን በመላክ ተከላክሎለታል(ዘፍ 32-33)፡፡  ጠንቋዩ በለዓም እስራኤላዊያን ሊረግም ሲነሣ መልዐኩን በመላክ መንገዱን ዘግቶታል(ዘኁ 22)፡፡  

ወገኖች ሆይ፣ በመርዶክዮስ ላይ የስቅላት ሞትን የሸረበው ሐማ የሆነውን አስቡ! ነቢዩን ዳንኤል በሐሰት ከስሰውት በአንበሶች ጉድጓድ ያስጣሉትን ሰዎች ፍጻሜ አስቡ! ከአምላካቸው በቀር ማንም እንዳያመልኩ የወሰኑትን እነዚያን ወጣቶች በእቶን እሳት ውስጥ ያስጣሉትን ሰዎች እስኪ አስተውሉ!

ታውቃላችሁ፣ ስለአገልጋዮቹ ጌታ ይቆረቆራልና እርሱ የቀባቸውን በሚዳስሱት ላይ እጁን ይዘረጋል! በነቢያቱም ላይ ክፉ በሚያደርጉት ግሳጼውን ያወርዳል!

ወገኖች ሆይ፣ በእግዚአብሔር ነቢያት፣ በተቀቡ አገልጋዮቹ ላይ የምንሠራውን ነገር ደጋግመን መመርመር ደጋግመን መጠየቅ ደጋግመን መጠንቀቅ እጅግ ያስፈልጋል! ‹‹የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ›› ብሎ የተናገረው ጌታ ራሱ ነውና ይህን ማስጠንቀቂያ መጠንቀቅ ይገባል!


ታውቃላችሁ፣ ይኼ ማስጠንቀቂያ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው መኖሩን እያዩ፣ ከፍተው እያነበቡ፣ እየሰበኩና እያስተማሩ፣ ነገር ግን የተቀቡትን የሚዳስሱ፥ በነቢያቱም ላይ ክፉ የሚያደርጉ፣ መሪዎች ቢሆኑ አገልጋዮች ቢሆኑ – ከጠንቋዩ በለዓም፣ ከጨካኙ ፈርኦን፣ ከኤሣውና ላባ፣ ከአቤሜሌክ ይልቅ፣ ጌታን የመመልከት ብቃት የሌላቸው፣ ድምጹንም ለመስማት አቅም የሌላቸው – አይነ ስውሮችና ደንቆሮዎች ናቸው!

No comments:

Post a Comment