Saturday, March 28, 2015

ከእግዚአብሔር ጋር – መጣላት!

ዲቮሽን .199/07፣ ቅዳሜ መጋቢት 19/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ከእግዚአብሔር ጋር – መጣላት!

ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል (ሮሜ 8፡7)፡፡

የእግዚአብሔር ጠላትነት ምሽጉ ያለው በሐሳባችን ወይንም በአእምሮአችን ውስጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጠላትነት ያለው ባልተለወጠ ሰው ሐሳብ ወይንም ዳግመኛ ባልተወለደ ሰው አእምሮ ውስጥ ነው፡፡

ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው አእምሮ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ ነውና ራሱን ለእግዚአብሔር ማስገዛት አይችልም፡፡ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ ሰው ለእግዚአብሔር መገዛት ቢፈልግ እንኳ የእግዚአብሔር መንፈስ ውስጡ የለምና ይህን ለማድረግ ፍጹም ይሳነዋል፡፡ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያሰ ሰው እግዚአብሔርን ማስደሰት በፍጹም አይችልም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና – ያልተለወጠ ሰው ሐሳብ የሞት መንትያ ነው! ይህም ማለት በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ አእምሮ ወደ ሞት ይመራል ማለት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ስለሥጋ ማሰብ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ማለት ነው! ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉና በሥጋ አስተሳሰብ የሚመላለሱ ወደ ሞት ይወርዳሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ በየቤተክርስቲያኑ ብዙ መታለል አለ! ሰዎች እጃቸውን አንስተው ጌታን ሲቀበሉ፣ የደኅነት ትምህርት ተምረው ሲጨርሱ፣ የውሃ ጥምቀቱን ሲያጠናቅቁ በቃ በአባልነት መዝገብ ይመዘገባሉ! እነዚህ ወገኖች የደቀመዝሙርነት ትምህርት ተከታትለው ሲጨርሱ፣ ልዩ ልዩ አገልግሎት ይጀምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው ችግሩ!

ወገኖች ሆይ፣ ነፍሳት ጌታን ሲቀበሉ በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ ልንጸልይ ይገባል! በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ሐሳባቸው ከኃጢአት ቁጥጥር ሥር አርነት ይወጣል! በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቀ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ዘንድ ይኖራል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ የሚኖር ሰው አስተሳሰቡ መንፈሳዊ ይሆናል፡፡ ስለመንፈስ ማሰብ ሕይወትና ሰላም አስከትሎ ይመጣል!

ታውቃላችሁ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሥጋ ሥራ እንጂ የመንፈስ ፍሬ የማይታይባቸው ብዙ አባላት አሉ፡፡ ከመዋደድ ይልቅ ጥልና ክርክር ጭቅጭቅ ንትርክ የሚወድዱ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ደስታ የሌላቸው፣ ከሰላም የተጣሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይጣሉ ስለሥጋ አያስቡ!  ይደቅቃሉና ስለሥጋ አያስቡ! ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይሞታሉና በሥጋ አስተሳሰብ አይመላለሱ! በሥጋ አስተሳሰብ የሚመላለሱ ወደ ሞት ይወርዳሉና በሥጋ አስተሳሰብ አይመላለሱ!  

------------------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!) 

No comments:

Post a Comment