Friday, October 31, 2014

የሰላም ወንዝ!



ዲቮሽን ቁ.51/07     አርብ፣ ጥቅምት 21/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የሰላም ወንዝ!

ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር (ኢሳ 48፡17-18)

ወዳጄ ሆይ፣ የወንዝ አፈሳሰስ ቆም ብለው አስተውለው ያውቃሉ! ወንዝ ከላይ ወደታች ይወርዳል! ጧትም ሆነ ማታ ሳያቋርጥ ይፈስሳል! ከእግዚአብሔር የሆነ ሰላም ጠዋትና ማታ ሳያቋርጥ በሚፈስስ ወንዝ ይመሰላል! እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር የሆነ ሰላም ነው! ከእግዚአብሔር የሆነ ሰላም ጠዋትና ማታ ሳያቋርጥ፣ ከላይ ወደታች ይፈስሳል!

ወዳጄ ሆይ፣ ወንዝ ፍሰቱ የሚቀንሰው ወይንም የሚደርቀው ድርቅ የመጣ እንደሆነ ወይንም ወደወንዙ ቆሻሻ የሚጣል ከሆነ ብቻ ነው! መንፈሳዊ ድርቅ ከክርስቶስ ያገኘነውን ሰላም ሊቀንሰው ወይንም ሊያደርቀው ይችላል! የሰላማችን ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ዓለማዊነት ወደ ሕይወታችን መግባት ሲጀምር ይህ ሰላም ሊደፈርስ፣ ሊደርቅ ይችላል! 

ወዳጄ ሆይ፣ ጠዋትና ማታ የማያቋርጥ ሰላም መጎናጸፍ ይፈልጋሉ? ከነፍስዎ ሞልቶ ወደ ውጭ የሚፈስስ እውነተኛ ሰላም እንዲኖረዎ ይመኛሉ? እንግዲያውስ ከጌታ ለመማር ራስዎን ያዘጋጁ! የሚሰጥዎትን ትምህርት፣ የሚሰጥዎትን የቤት ሥራ፣ የሚሰጥዎትን ፈተና በትጋት ይወጡ! ቀሽም ተማሪ አይሁኑ! 

ወዳጄ ሆይ፣ የሰላምን መንገድ ከጌታ ይማሩ! የደስታን መንገድ ከጌታ ይማሩ! የማይረባን አስጥሎ የሚረባን ለሚያስይዝ ለታላቅ መምህር ሁለንተናዎን ይስጡ!  የእውነተኛን ደስታ መርቶ የሚያሳየውን ጌታን ይከተሉ! 

ወዳጄ ሆይ፣ የክርስቶስ ሰላም ከውስጣችን በሙላት እንዲፈስስ መንፈሳዊ ሕይወታችንን በየዕለቱ ልንንከባከብ ይገባል! ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ ‹‹ሰላም አለኝ እንደ ወንዝ የሚፈስስ፣ አዕምሮዬን የሚያረሰርስ፣ ደስታ አለኝ ከውስጤ የማይጠፋ፣ ኢየሱስ ክብሩ ይስፋ›› እያልን የምንዘምረው ዝማሬ እውነት የሚሆነው! 

-------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Thursday, October 30, 2014

ተንኮታኩቶ መውደቅ!



ዲቮሽን ቁ.50/07     ሐሙስ፣ ጥቅምት 20/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ተንኮታኩቶ መውደቅ!

አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ … እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም። ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ።… በድያለሁ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን፦ ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው…(ዘሁ 22፡27-35)


ሰው የፈለገውን መንገድ መርጦ የመጓዝ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ በጉልበት አይጠመዝዘውም፡፡ ሆኖም የሰው ነጻ ፈቃድ በእግዚአብሔር እቅድ ላይ በተጽዕኖ በሚነሳበት ጊዜ እግዚአብሔር የራሱን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡ 

እግዚአብሔር ሰውን ከራሱ መንገድ ለመመለስ ሲፈልግ የሚወስደው የመጀመሪያው እርምጃ መንገድ መዝጋት ነው፡፡ ሁለተኛው እርምጃ አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ሦስተኛው እርምጃ ትምክህትን ከነድጋፉ አንኮታኩቶ መጣል ነው! 

በለዓም ለተሰጡት ሁለት ማስጠንቀቂያዎች አዎንታዊ ምላሽ አልሰጠም፡፡ በመሆኑም፣ ከቦታ ወደቦታ ለሚያደርጋቸው ጉዞዎች ሙሉ ድጋፉ የሆነችውን የአህያውን ጉልበት ያዘና ጣለበት! ምርኩዙ ተሰብሮ ስለወደቀበት በለዓም ለመቆም ተገደደ!  

ወገኖች ሆይ፣ የጤርሴሱን ሳውል አስቡ! በደማስቆ መንገድ ላይ ምርኩዙ ሲሰበር ነው ቀጥ ብሎ የቆመው! ናቡኬደነጾርን አስቡ! አርፎ እንዲቀመጥ ሲነገረው አሻፈረኝ ብሎ የንጉሥነት ማዕረጉ ተገፎ፣ ከሰውነት ተራ ወጥቶ እንስሳ ሲሆን ነው ቀጥ ብሎ የቆመው! 

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዴ ክብር አይወድልንም! መከራና ችግር ሾጥ ሾጥ ካላደረገን ነገር አይገባንም! እሳት ለመያዝ እንደሚፈልጉ ሕጻናት፣ ሲከለከሉም እንደሚያለቅሱ ሁሉ  የሚጎዳንን ለመያዝ ትግል እናደርጋለን! 

ታውቃላችሁ፣ ‹‹ምከረው፣ ምከረው፤ እንቢ ካለ መከራ ይምከረው›› እንዲሉ ባለመመከራችን ችግር እንቀምሳለን! በገዛ እጃችን እሳቱን ለኩሰን፣ አንድደን አፏፍመን እንቃጠላለን! በሠራነው ስህተት እንጎዳበታለን! ለእምቢተኝነታችን ዋጋ እንከፍላለን! 

ወገኖች ሆይ፣ መስማት ከፈለግን ጌታ ይናገራል! በቃል፣ በነቢያት፣ በወቅቱ ሁኔታ፣ በወጀብ፣ በአውሎ ንፋስ ጌታ ይናገራል! ማዳመጥ ከቻልን ሁኔታዎቻችን አፍ አውጥተው ጮኸው ይናገራሉ! ማየት ከፈለግን ዓይኖቻችንን ይከፍታል! ዓይኖቻችን ከፍቶ ራሱን ያሳየናል! በመንገዳችን ያለውን፣ ከፊት የሚመጣውን፣ ተደብቆ ያለውን፣ ያልተገለጠውን … ገልጦ ያሳየናል!

ወገኖች ሆይ፣ ባልተፈቀደ መንገድ ገብተን እንዳንዳክር፣ የማይወድደውን እንዳንሞክር ጌታ ይርዳን! መንገዳችን ሲዘጋ ወደ መንገዱ እንድንዞር፣ አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ ራሳችንን እንድንመረምር፣ መርኩዛችን ሲሰበር ጌታን እንድንይዝ ጸጋው ይደግፈን! 

-------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Wednesday, October 29, 2014

አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ!



ዲቮሽን ቁ.49/07     ረቡዕ፣ ጥቅምት 19/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ!

የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች እርሱም ደግሞ መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ (ዘሁ 22፡24-26)

ሰው የፈለገውን መንገድ መርጦ እንዲጓዝ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ በጉልበት አይጠመዝዘውም፡፡ ሆኖም የሰው ነጻ ፈቃድ በእግዚአብሔር እቅድ ላይ በተጽዕኖ በሚነሳበት ጊዜ እግዚአብሔር የራሱን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡
የመጀመሪያው የእግዚአብሔር እርምጃ መንገድ መዝጋት ነው፡፡ መንገድ የሚዘጋው ሰው መሄጃ ስለሚያጣ ቆም ብሎ እንዲያስብ ነው፡፡ 

ሁለተኛው የእግዚአብሔር እርምጃ አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንገዳችንን ሲዘጋ ቆም ብሎ ማሰብ ለመልካም ውጤት ያበቃናል፡፡ ነገር ግን በእንቢታ የራሳችንን መንገድ የምንከተል ከሆነ እግዚአብሔር መንገዳችንን በመዝጋት ብቻ አያልፈንም፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ከተዘጋብን መንገድ በተጨማሪ ወዲያ ወዲህ እንዳንፍጨረጨር አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባናል፡፡ 

እግዚአብሔር የበለዓምን መንገድ በመዝጋቱ ምክንያት አህያው ከመስመር ወጥታ ነበር፡፡ በለዓም አህያውን ወደ መስመሩ ለመመለስ የዱላ ናዳ ቢያወርድባትም መመለስ አልሆነላትም! የዱላው ውርጅብኝ የመረራት አህያ የሞት ሞቷን ተንደርድራ በመሄድ በሁለት አጥሮች መካከል እየጠበበ በሚሄድ ግንብ መካከል ገብታ ተሰነቀረች! በለዓም ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› እንዲሉ የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ! 

ታውቃላችሁ፣ ጌታ አጣብቂኝ ውስጥ ካስገባን መነቃነቅ አንችልም! ወደምንመኘው መሄድ፣ ወደምንፈልገው መድረስ አይሆንልንም! 

ወገኖች ሆይ፣ የኢትዮጵያን የደርግ ሥርዓት አስቡ! ደርግ ሥርዓቱን ሲጀምር ‹‹ያለ ምንም ደም፣ ኢትዮጵያ ትቅደም፣ መሐይም አይኖርም፣ ድህነት አይኖርም፣ ተፈጥሮን ተቆጣጥሬ፣ ወንዞችን ገድቤ፣ ሙስናን አጥፍቼ… እያለ ይዘፍን ነበር፡፡ መንገዱ ዝግ ነውና እንደዘፈነው አልሆነለትም፡፡ ስለሆነም፣ የዘፈኑ ቀለም ተለውጦ ‹‹ከሁሉ በፊት አብዮቱ፣ ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር፣ አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋጋለን፣ አብዮት ልጇን ትበላለች፣ በመራራው ትግል ወደፊት…›› ሆነ!

ወገኖች ሆይ፣ የደርግ–ኢሠፓ ሥርዓት ‹‹ዘራፍ ጀግናው!›› ‹‹ኧረ ጎራው!›› ‹‹ቀይ ሽብር፣ ተገንጣይ አድሃሪ›› እያለ እየፎከረ ከመንገዱ ሳይመለስ ለአስራ ሰባት ዓመታት ቆየ! በዚህም አቅሙ እየደከመ፣ ኢኮኖሚው እየከሰመ፣ ጦርነቱም እየተፋፋመ ሄደ!

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር የደርግ–ኢሠፓ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኮሚኒዝምን ተግባራዊ እንዳያደርግ መንገዱን ዘግቶበት ነበር! ነገር ግን ደርግ ቆም ብሎ መንገዱን መመርመር አልቻለምና፣ ኮሚኒዝምን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ያልማሰው ጉድጓድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም! ሆኖም ሙከራው ሁሉ ፉርሽ ይሆንበት፣ ሥራውም ሁሉ እንደ እንቧይ ካብ ይናድበት ነበር!

ወገኖች ሆይ፣ መንገዱ ሲዘጋበት አርፎ ሊቀመጥ አልቻለምና ሁለተኛውን እርምጃ ወሰደበት– አጣብቂኝ ውስጥ አስገባው! በመራራው ትግል የተማረሩ ‹‹ጓዶች››፣ ምሁራንና ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ወታደሮች፣ ምዕመናንና የሐይማኖት መሪዎች፣ አኢወማዎችና አኢሴማዎች (ወጣቶችና ሴቶች) ሥርዓታቸውን እየካዱ መውጣት ጀመሩ!

ወገኖች ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት አያዋጣም! ከእርሱ ጋር መጣላት ያደቅቃል! የጀመርነውን እንድናቆም ከጠየቀን ‹‹ካፈርኩ´አይመልሰኝ›› ማለቱ ፈጽሞ አይጠቅምም! ከእግዚአብሔር ጋር እልህ መጋባት የትም አያደርስም! 

ወዳጆች ሆይ፣ ብርጭቆ ከብረት ጋር ቢጋጭ ራሱን እንደሚጎዳ ከእግዚአብሔር መጋጨት እራስን ይጎዳል! ስለሆነም፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንጋጭ! መንገዳችንን ሲዘጋ በጊዜ እንመለስ! አለበለዚያ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባናል! ከእርሱ አለመስማማት ለበለጠ ጉዳት፣ የበለጠ ኪሳራ ያደርስብናል! 

-------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Tuesday, October 28, 2014

ጥሪና – ዝንባሌ!



ዲቮሽን ቁ.48/07     ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ጥሪና – ዝንባሌ!

ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና (ዕብ 11:24-26


ጥሪና ዝንባሌ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው! ዝንባሌ አብሮ ተወልዶ አብሮ የሚያድግ ተሰጥኦ ነው፡፡ ማናቸውም ዓይነት ትምህርትና ሥልጠና ተሰጥኦን ሊተካ አይችልም፡፡ ማናቸውም ዓይነት የሕይወት ከፍታ ዝንባሌን አያረካም፡፡ በተጠራንበት ነገር አቅጣጫ እስካልተሰማራን ድረስ እፎይታ አይገኝም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሙሴ የግብጾችን ጥበብ ሁሉ የተማረ የተመራመረ (የሐዋ 7፡22) ቢሆንም፣ በቤተመንግሥት የሚኖር ልዑል ቢሆንም፣ የተጠራበት ነገር አለና አርፎ መቀመጥ አልቻለም! ስለሆነም፣ ከቤተመንግሥት ድሎት ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ!

ታውቃላችሁ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ድሎት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ሀብት ቢኖር ወደተጠራንበት መስመር ካልገባን በስተቀር፣ በተጠራንበት ሥራ እስካልተሰማራን ድረስ እፎይታ አይገኝም!

ታውቃላችሁ፣ ዝንባሌያችንን ተከትለን እስካልሠራን ድረስ፣ በሕይወታችን ውስጥ እርካታ አናገኝም፡፡ ጥሪያችንን ተከትለን እስካልተሰማራን ድረስ እፎይታ አይኖረንም!

ታውቃላችሁ፣ ሰው በራሱ ጥረት የእግዚአብሔርን ጥሪ ማግኘት አይችልም! ነገር ግን ለእግዚአብሔር የሚቀና መንፈስ ያለው ሰውና ዘወትር ለሕዝቡ የሚቆረቆር ሰው ሳይታወቀው ራሱን የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ሆኖ ያገኘዋል!

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር ለአንድ ነገር ጠርቶን ከሆነ አእምሮአችን ስለተጠራንበት ስለዚያ ጉዳይ ቀንና ማታ እየተጨነቀ እረፍት አያገኝም፡፡ በትንሽ ቅልቁ ነገር ሁሉ ሆድ እየባሰን እንታወካለን! ስለጉዳዩ ላለማሰብ እንኳ ብንወስን አይሳካልንም! ከጉዳዩ መሸሽ መራቅ ብንፈልግ የትም አናመልጥም!

ወዳጄ ሆይ፣ በአካባቢዎ በሚሠራው ክፉ ነገር ምክንያት ሁልጊዜ በውስጥዎ እረፍት የማይሰማዎ ከሆነ በሕይወትዎ አንድ ነገር እየሆነ ነው! በኃጢአት ላይ መንፈስዎ የሚቆጣ፣ የሚበሳጭ፣ የሚረበሽ፣ የሚያለቅስና የሚቃወም ከሆነ እርስዎ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ መሆንዎትን ይወቁ! መንፈስዎ በሚበሳጭበት ነገር አቅጣጫ ጥሪ እንዳለዎ ይመኑ! ያመኑበትን ጥሪ ይቀበሉ! ለተቀበሉትም ጥሪ ተገቢ ምላሽ ይስጡ!

-------------------------
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)