ዲቮሽን ቁ.49/07 ረቡዕ፣ ጥቅምት
19/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
አጣብቂኝ
ውስጥ ስንገባ!
የእግዚአብሔርም መልአክ
ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ
አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች እርሱም ደግሞ መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት
ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ (ዘሁ
22፡24-26)።
ሰው የፈለገውን መንገድ
መርጦ እንዲጓዝ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ በጉልበት አይጠመዝዘውም፡፡ ሆኖም የሰው ነጻ ፈቃድ በእግዚአብሔር
እቅድ ላይ በተጽዕኖ በሚነሳበት ጊዜ እግዚአብሔር የራሱን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡
የመጀመሪያው የእግዚአብሔር
እርምጃ መንገድ መዝጋት ነው፡፡ መንገድ የሚዘጋው ሰው መሄጃ ስለሚያጣ ቆም ብሎ እንዲያስብ ነው፡፡
ሁለተኛው የእግዚአብሔር እርምጃ
አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንገዳችንን ሲዘጋ ቆም ብሎ ማሰብ ለመልካም ውጤት ያበቃናል፡፡ ነገር ግን በእንቢታ
የራሳችንን መንገድ የምንከተል ከሆነ እግዚአብሔር መንገዳችንን በመዝጋት ብቻ አያልፈንም፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ
ከተዘጋብን መንገድ በተጨማሪ ወዲያ ወዲህ እንዳንፍጨረጨር አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባናል፡፡
እግዚአብሔር የበለዓምን
መንገድ በመዝጋቱ ምክንያት አህያው ከመስመር ወጥታ ነበር፡፡ በለዓም አህያውን ወደ መስመሩ ለመመለስ የዱላ ናዳ ቢያወርድባትም መመለስ
አልሆነላትም! የዱላው ውርጅብኝ የመረራት አህያ የሞት ሞቷን ተንደርድራ በመሄድ በሁለት አጥሮች መካከል እየጠበበ በሚሄድ ግንብ
መካከል ገብታ ተሰነቀረች! በለዓም ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› እንዲሉ የባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!
ታውቃላችሁ፣ ጌታ አጣብቂኝ
ውስጥ ካስገባን መነቃነቅ አንችልም! ወደምንመኘው መሄድ፣ ወደምንፈልገው መድረስ አይሆንልንም!
ወገኖች ሆይ፣ የኢትዮጵያን
የደርግ ሥርዓት አስቡ! ደርግ ሥርዓቱን ሲጀምር ‹‹ያለ ምንም ደም፣ ኢትዮጵያ ትቅደም፣ መሐይም አይኖርም፣ ድህነት አይኖርም፣ ተፈጥሮን
ተቆጣጥሬ፣ ወንዞችን ገድቤ፣ ሙስናን አጥፍቼ… እያለ ይዘፍን ነበር፡፡ መንገዱ ዝግ ነውና እንደዘፈነው አልሆነለትም፡፡ ስለሆነም፣
የዘፈኑ ቀለም ተለውጦ ‹‹ከሁሉ በፊት አብዮቱ፣ ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር፣ አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋጋለን፣ አብዮት
ልጇን ትበላለች፣ በመራራው ትግል ወደፊት…›› ሆነ!
ወገኖች ሆይ፣ የደርግ–ኢሠፓ
ሥርዓት ‹‹ዘራፍ ጀግናው!›› ‹‹ኧረ ጎራው!›› ‹‹ቀይ ሽብር፣ ተገንጣይ አድሃሪ›› እያለ እየፎከረ ከመንገዱ ሳይመለስ ለአስራ
ሰባት ዓመታት ቆየ! በዚህም አቅሙ እየደከመ፣ ኢኮኖሚው እየከሰመ፣ ጦርነቱም እየተፋፋመ ሄደ!
ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር
የደርግ–ኢሠፓ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኮሚኒዝምን ተግባራዊ እንዳያደርግ መንገዱን ዘግቶበት ነበር! ነገር ግን ደርግ ቆም ብሎ መንገዱን
መመርመር አልቻለምና፣ ኮሚኒዝምን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ያልማሰው ጉድጓድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም! ሆኖም ሙከራው ሁሉ
ፉርሽ ይሆንበት፣ ሥራውም ሁሉ እንደ እንቧይ ካብ ይናድበት ነበር!
ወገኖች ሆይ፣ መንገዱ
ሲዘጋበት አርፎ ሊቀመጥ አልቻለምና ሁለተኛውን እርምጃ ወሰደበት– አጣብቂኝ ውስጥ አስገባው! በመራራው ትግል የተማረሩ ‹‹ጓዶች››፣
ምሁራንና ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ወታደሮች፣ ምዕመናንና የሐይማኖት መሪዎች፣ አኢወማዎችና አኢሴማዎች (ወጣቶችና ሴቶች) ሥርዓታቸውን
እየካዱ መውጣት ጀመሩ!
ወገኖች ሆይ፣ ከእግዚአብሔር
ጋር መጣላት አያዋጣም! ከእርሱ ጋር መጣላት ያደቅቃል! የጀመርነውን እንድናቆም ከጠየቀን ‹‹ካፈርኩ´አይመልሰኝ›› ማለቱ ፈጽሞ
አይጠቅምም! ከእግዚአብሔር ጋር እልህ መጋባት የትም አያደርስም!
ወዳጆች ሆይ፣ ብርጭቆ
ከብረት ጋር ቢጋጭ ራሱን እንደሚጎዳ ከእግዚአብሔር መጋጨት እራስን ይጎዳል! ስለሆነም፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንጋጭ! መንገዳችንን
ሲዘጋ በጊዜ እንመለስ! አለበለዚያ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባናል! ከእርሱ አለመስማማት ለበለጠ ጉዳት፣ የበለጠ ኪሳራ ያደርስብናል!
-------------------------
(ይህን
ዕለታዊ
ዲቮሽን
ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችዎም
እንዲያገኙ
ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment