Wednesday, September 9, 2015

የአቋም መግለጫ የተጸለየበት ዘይትና ውሃ አገልግሎት – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው! (ክፍል ሁለት)

የአቋም መግለጫ (ክፍል ሁለት)

የተጸለየበት ዘይትና ውሃ አገልግሎት – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው!

አንድ የተዳከመ በሽተኛ፣ በቃሬዛ እየተወሰደ ነው፡፡ ይህ በሽተኛ አንድ ቦታ ላይ ሲደርስ፣ ‹‹ኧረ ጎራው፣ ኧረ ጎራው›› የሚል ፉከራ ይሰማል፡፡ ይኼኔ በሽተኛው ‹‹እባካችሁን አውርዱኝ›› ይላል፡፡ ተሸካሚዎቹም ከነቃሬዛው አውርደው መሬት ላይ ሲያስቀምጡት፣ ከቃሬዛው ላይ ቀና ብሎ፣ ‹‹እንቢ፣ እንቢ›› ማለት ጀመረ አሉ፡፡

እኛ የኢትዮጵያ ጴንጤቆስጤ ቤተእምነቶች በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎታችን ስለተዳከምን፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና አገልግሎቶች በሚቃወሙ ቡድኖች ቃሬዛ ላይ ወጥተናል፡፡  ከዚህ ቃሬዛ ላይ ቶሎ ወርደን፣ ወደ ጤናማው ማንነታችን ልንመለስ ይገባል፡፡ ወደ ቦታችን እስክንመለስ ድረስ፣ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ጌታ የቀባቸው ጀግኖች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ብቅ ሲሉ፣ ልንነቃና ልንነቃቃ፣ ‹‹እንቢ ለጠላት፣ እንቢ›› ማለት ይገባናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሃሌሉያ፣ እንቢ ለጠላት፣ እንቢ!

ወደ ዋናዎቹ ነጥቦች ከመግባቴ በፊት፣ ይህን አቋም ለማውጣት ያስገደደኝ አብይ ምክንያት ምን እንደሆነ በአጭሩ ደግሞ ልግለጽ፡፡ በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ አንዳንድ ቡድኖች፣ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ለመቃወም ውስጥ ለውስጥ ሲሄዱበት ከቆዩት አስተሳሰብ ሥር ሰድዶና ቅርንጫፍ አብቅሎ መራራ ፍሬ ማፍራት መጀመሩ ነው፡፡ ለዚህ አባባሌ ቢያንስ ሦስት ማስረጃዎችን ልስጥ፡፡

አንደኛው ማስረጃ፡፡ በአንድ አንጋፋ የሀገራችን ኅብረት ሥር በምትታተም መጽሔት ላይ፣ ነቢያት በዛሬው ዘመን ስለመኖር አለመኖራቸው በተከፈተው ውይይት ላይ፣ የሚገርሙ ክርክሮች መካሄዳቸው፣ አስተሳሰቡ ወዴት አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ በግልጽና በአደባባይ አስቀምጦ ያለፈ የወቅቱ የማንቂያ ደወል እንደነበር የቅርብ ትዝታ በመሆኑ፣ 

ሁለተኛው ማስረጃ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት ደግሞ፣ በምልክትና በተአምራት አገልግሎት፣ እንዲሁም በርካታ አጥቢያዎች በመትከል፣ ለረዥም ዘመናት በመላው ወንጌል አማኞች ዘንድ የሚታወቀውና እጅግ የሚወደድ የእግዚአብሔር ሰው፣ የገዛ አጥቢያው ‹‹ሐዋሪያ›› ብላ ስትሾመው በሀገሪቱ ውስጥ የተነሣውን ውዝግብ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ መሆኑ፣

ሦስተኛው ማስረጃ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለ ዘይትና ውሃ፣ ስለመሳሰሉትም አገልግሎት በመጽሔቶችና በተለያዩ የተደራጁ መንገዶች ጫና እየተደረገ መምጣቱ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን እየተለመደ የመጣው ባህል፣ ከእኛ ቀበሌ ውጭ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ምልክት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ተአምራትም በጌታ በኢየሱስ ስም ቢደረጉም ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ አገልግሎት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሺህ ጊዜ ሺህ ሰዎች ከአጋንንት እስራት ነጻ ቢወጡ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ሰዎች ጌታን ተቀብለው ቢድኑ እውቅና አይሰጣቸውም፡፡ በአገልግሎቱ የተፈወሱ ሺህ ጊዜ ሺህ ሕመምተኞች፣ በጸጋው የተገነቡ እልፍ ጊዜ እልፍ ቤተሰቦች፣ እና ሌሎችም ተራራ ተራራ የሚያካክሉ የእግዚአብሔር ጣት አሻራዎች ቢገኙም፣ ለእነዚህ የእግዚአብሔር ጣት አሻራዎች እውቅና ተነፍጓቸው፣ የጠጠር ያህል ጥቃቅን በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ ‹‹አበበ በሶ በላ፣ መጠንቆል ጀመረ፣ ሕዝብንም ዘረፈ፣ ውሃና ዘይት ሸጠ፣ ጨርቅና ቁሳቁስ ለወጠ››… እየተባለ አብያተክርስቲያናት ሲሸበሩና ሲተራመሱ እናያለን፡፡

አሁን ባለንበት ጊዜበሀገራችን እውን የሆነውን የእምነት ነጻነት ለመጋፋትና በኃይል ለመጫን በሚሞክሩ በጥቂት የአብያተክርስቲያናት ውስጥ ቡድኖች ዘመቻ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን በነጻነት ለመስበክና ጴንጤቆስጤያዊ ልምምዶችን ለማድረግ ወደሚያሳቅቅ ደረጃ እየደረስን ነው፡፡ በእነዚህ ቡድኖችና የቡድኖቹን ውስጣዊ አጀንዳ በደንብ ሳያጤኑ በሚከተሏቸው ወገኖች ምክንያት በሀገራችን  በአደባባይ ቆሞ በጌታ በኢየሱስ ስም ድንቅና ምልክት ማድረግ ወደሚያስኮንንበት፣ በሕዝብ አደባባይ በሽተኞች መፈወስና፣ ትንቢት መናገር ወደሚያሸማቅቅበት የውድቀት ምዕራፍ እየገባን ነው፡፡

በየአጥቢያዎች ውስጥ የሚታዩና የሚዳሰሱ ድንቅና ምልክቶች ቢደረጉም አገልጋዮች ለነቀፋና ለስደት የሚዳረጉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ወንጌላዊያን በሌሎች ኃይላት ሲሰደዱ፣ ሲዋረዱና ሲሸማቀቁ ነበር፡፡ ያንን ዘመን እጅ ለእጅ በመያያዝ በድል አልፈናል፡፡ አሁን የደረስንበት ጊዜ ግን በታሪካችን ሆኖ የማያውቅ፣ ወንጌላዊያን ወንጌላዊያንን የሚያሳድዱበትና፣ አገልጋዮች አገልጋዮችን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡበት እጅግ አደገኛው ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

በርግጥ፣ የቀድሞው የስደቱ ዘመን እንዳለፈ ሁሉ የአሁኑም ስደት ያልፋል፡፡ ነገ ስለሚሆነው አስቀድሞ መተንበይ ቢያስቸግርም፣ ጌታ ያስነሣቸው አገልጋዮችን የሚያሳድዱ ማናቸውም ኃይሎች ግን ዋጋ እንደሚከፍሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወዮልሽ ኮራዚወዮልሽ ቤተሣይዳወዮልሽ ቅፍርናሆምወዮልሽ ኢየሩሳሌም… ›› በማለት ነቢያትን ሲያሳድዱ፣ ሲገድሉና ሲወግሩ ለነበሩ ከተሞች ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር (ማቴ 1120-24 2337-39)፡፡ በውስጣቸውም ሆነ በጎረቤቶቻቸውም የሚበዙ ተአምራቶች የተደረገባቸው እነዚህ ከተሞች ባለመቀበላቸው ምክንያት የተሰጣቸውን ይህን ማስጠንቀቂያ ሰምተው አልተመለሱምና፣ ማስጠንቀቂያው በተሰጠ በሰላሣ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ በሮማዊው ማርሻል ቲቶስ ጡንቻ ደቅቀው ወደፍርስራሽነት መለወጣቸውን እናውቃለን፡፡

ይህ ማስጠንቀቂያ ለእኛም ነው! ዛሬ ነቢያትን የሚያሳድዱ አብያተክርስቲያናት ከድርጊታቸው ካልታቀቡና ንሥሐ ካልገቡ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ መፈራረስና ወደ ወናነት የመቀየራቸው እውነታ የማይታበል ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በማክፋፋትና አገልጋዮችን በማሳደድ ስህተት የሠሩ፣ በአንድ ወቅት ሕዝብ ሞልቶባቸው የነበሩ፣ በየፕሮግራሞቻቸው ጊዜ መቆሚያና መቀመጫ ይጣበብባቸው የነበሩ አንዳንድ በአዲስ አበባና በክልል አካባቢ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት፣ ዛሬ ዛሬ ብዙ ባዶ ወንበሮችና ክፍት አዳራሾች መሆን መጀመራቸው፣ ችግሩ አስቸኳይ ንስሐ የሚያስፈልገው ነው፡፡

አሁን ወደ ዋናው ነጥቤ ልግባ፡፡ ነቢያት አዘውትረው ሲጠቀሙ የምናያቸው፣ የተጸለየበት ዘይት፣  የተጸለየበት ውሃ፣ የተጸለየበት መሐረብ ወይም ጨርቅ አገልግሎት፣ እና የማባዛት አገልግሎት ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው? የሚለውን በአጭሩ እንመለከትና በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆዎች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የማቀርባቸው ነጥቦችና ማብራሪያዎች በዋናነት በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዱና መጽሐፍ ቅዱሳዊና የሆኑ ሁሉም አንብቦ መረዳት እንዲችል ተደርጎ የቀረቡ ትንታኔዎች ናቸው፡፡ ነጥቦቼን ከማቅረቤ በፊት ግን፣ ለተከበሩ አንባቢዎቼ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝን መሠረተ እምነት ለማሳወቅ ያህል፣ በአጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያሉት፣ ስድሳ ስድስቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ስህተት የሌለባቸው፣ የማይወድቁና የማይሻሩ፣ በዘመናት የማይለወጡና የማይሻሻሉ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ እንደሚችሉ፣ የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ እንደሚጠቅሙ እንደሆኑ አምናለሁ፣ አምኜም እሰብካለሁ፣ እጽፋለሁም።

1ኛ፣ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት “holy anointing oil”  አገልግሎት፡፡

በብሉይና ሐዲስ ኪዳን  የቅብዓት ዘይት አገልግሎት በአጠቃላይ ሲታይ ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች እና ለውበት መጠበቂያ ተግባሮች ጥቅም ላይ ውሎ እናገኛለን፡፡ ከእነዚህም መካከል ሕመምተኞችን ለመፈወስ፣ አገልጋዮችን ለመሾምና፣ አስከሬን ሳይበሰብስ እንዲቆይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

እግዚአብሔር ሙሴን የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት እንዲያጋጅ በሰጠው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ዘይት፣  አሮንና ልጆቹ ለክህነት ሥራ ሲቀበቡት እናያለን (ዘጸ 3022-30)፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ እግዚአብሔር ሙሴን በዚህ ዘይት፣ የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩን ታቦት፥ ገበታውንና ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንና ዕቃውን፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ሁሉ እንዲቀባ አዘዘው(ዘጸ 3026-29)። ሙሴም የታዘዘውን አደረገ፡፡ እዚህ ላይ ዘይቱ እንዲቀባ የተደረገው በቁሳቁሶች ላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን አዳዲስ ነገሥታት ሲሾሙ ነቢያት በዘይት ይቀቧቸው ነበር፡፡ ከነገሥታቱ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ሳዖል (1ሳሙ 101) ዳዊት (1ሳሙ 1613) ኢዩ(2ነገ 93) ይገኙበታል፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የቅብዓት ዘይት ሕመምተኞችን ለመፈወስ(ያዕ 514-15) ለአምልኮ፣ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ እንዲሁም ለቀብር ማዘጋጃ (ማር 143-9 ሉቃ 2355-56) ዓላማዎች ውለዋል፡፡

የአላዛርና ማርታ እህት ማርያም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር በሰው ሁሉ ፊት የቀባችውና፤ በባህሉ ዘንድ ለሴት ልጆች የክብር ምልክት የሆነውን ጸጉርዋን እንደ ፎጣ በመጠቀም እግሩን ያበሰችበት ምክንያት፤ ከአምልኮ ሌላ መገለጫ ሊሰጠው አይችልም፡፡ በዚህ ታሪክ ላይ እኔን ሦስት ነገሮች አስገርመውኛል፣ አስደንቀውኛልም፡፡ 1ኛው፣ የማርያም የአምልኮ ሁኔታ ሲሆን፣ 2ኛው፣ የአስቆሮቱ ይሁዳ ቁጣና ትችት፣ ሲሆን 3ኛው፣ ጌታ ኢየሱስ ስለ ጉዳዩ የሰጠው ምላሽ ነው፡፡

ሴት ልጅ ክብሯን ጥላ ጌታን ስታመልክ ያየው የአስቆሮቱ ይሁዳ ተቆጣ፡፡ ይሁዳን ወደዚህ ቁጣና ትችት ያደረሰው ምክንያት ምን እንደሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ ሲያጋልጥ፣ ‹‹ይሁዳ ይህን የተናገረው ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው›› ይላል(ዮሐ 126) ንጉሡ ዳዊት ክብሩን ጥሎ ጌታን ሲያመልክ ሜልኮል እንዴት እንደነቀፈችው እናውቃለን (2 ሳሙ 616-23)፡፡

በይሁዳም ሆነ በሜልኮል የደረሰውን እናውቃለንይሁዳ አጋንንት ገብቶበት፣ ጌታን አሳልፎ መሸጡን፣ ራሱንም በገዛ እጁ ማጥፋቱን እናውቃለን፡፡ ሜልኮልም እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ ሳትወልድ መቅረቷን እናውቃለን ታውቃላችሁ፣ አምልኮአችንን የሚነቅፉ ሰዎች ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ይህም ሁኔታ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ስለማርያም ደግሞ እንዲህ ሲል ነው የመለሰው፣ ‹‹ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለችእውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል›› (ማር 144-9)፡፡

እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ቢያንስ አንድ ቁም ነገር ልንማር እንችላለንበቅባት አገልግሎቱ ላይ እየሰነዘርን ያለውን ትችት እንተወው፣ አገልጋዮቹን በቁጣና በውክቢያ አናዳክማቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ አስራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ሁለት ሁለት አድርጎ በላካቸው ጊዜ፣ በርኵሳን መናፍስት ላይና ድውያንን እንዲፈውሱ ሥልጣን እንደሰጣቸው፣ ደቀመዛሙርቱ ወጥተውም ብዙዎች ንስሐ እንዲገቡ እንደሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም እንዳወጡ እናውቃለን፡፡ በማርቆስ ወንጌል 67-13 ባለው ቦታ ላይ በግልጽ ተጽፎ እንደምናነብበው፣ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ለሕመምተኞች መፈወሻ የሚሆን የቅብዓት ዘይትም በእጃቸው ይዘው የተሰማሩ ይመስላል፡፡ ቁጥር (13) ላይ እንዲህ ይነበባል፡- ‹‹ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።››

ይህ ‹‹ብዙ ድውዮችን ዘይት እየቀቡ መፈወስ›› ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ፣ በኢየሱስ ደቀመዛሙርት የተደረገ መሆኑን ስናይና፣ ኢየሱስም ‹‹ለምን እንዲህ አደረጋችሁ?›› ብሎ ሲቆጣቸውና ሲተቻቸው ተጽፎ ያለማንበባችን እውነታ፣ ጌታ ከቅብዓት ዘይት አገልግሎት ጋር ጥል እንደሌለው፣ ዛሬም የእርሱ ደቀመዛሙርት ለስሙ ክብር እንዲሆን የቅብዓት ዘይት ቢጠቀሙ የማይከፋው መሆኑን ነው፡፡

በእውነት በቅብዓት ዘይት አገልግሎት ጌታ ካልከፋው፣ በአገልግሎቱም ብዙ ድውያን ከተፈወሱበትና ብዙዎችም ከተባረኩበት እኛስለምን እንከፋለን? ‹‹ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል›› (ያዕ 514-15)

2ኛ፣ የቅብዓት ውሃ “anointing oil” አገልግሎት፣

የውሃ ጥምቀትን ወይም የውሃ መርጨት ጉዳይን ጨምሮ፣ በቤተክርስቲያን የሚደረጉ የቅብዓት ውሃ ወይም የተጸለየበት ውሃ አገልግሎት አስፈላጊነት ላይ ክርክሮች ቢኖሩም፣ ጉዳዩ በቸልታ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡ የውሃ ጥምቀት ጉዳይ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን የደኅንነት ጸጋ ሰዎች ትዕምርታዊ በሆነ መልኩ መቀበላቸውን ያሳያል፡፡

በብሉይ ኪዳን፣ ‹‹የመታጠቢያው ሰን›› የሚቀመጠው በመሰዊያውና በመገናኛው ድንኳን መካከል ሲሆን፣ ካህናቱ መስዋዕት ለማቅረብ በሚመጡበት ጊዜ እጃቸውን እንዲታጠቡበት የታዘዘ ለውስጣዊ መንጻት የሚፈጸም ውጫዊ ድርጊት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውሃ ትዕምርታዊ(symbolic) ለሆነ ኃጢአተኞችን ከኃጢአታቸው የማንጻት መንፈሳዊ አቅምና የማዳን ኃይል እንዳለው፣ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆኖ ስለመገለጡ ከዚህ በታች የቀረቡ ጥቅሶች  አስረጅ ናቸው፡፡

ለምሣሌ ያህል፣ (ዘሁልቁ 87) ላይ፣ ‹‹ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም፡፡›› በዕብራዊያን (1022) ላይም ‹‹ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤››

‹‹እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ››(ማቴ 311)፡፡ ‹‹ያመነ የተጠመቀም ይድናል››(ማር 1616) ‹‹… ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› (ዮሐ 35) ‹‹ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው›› (1ጴጥ 321) ‹‹ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ (ኤፌ 525-27)

‹‹ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረኢየሱስም፦ የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ … ›› (ዮሐ 134-10) ‹‹ጲላጦስምውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ›› (ማቴ 2724) እነዚህና ከላይ የቀረቡ ጥቅሶች ለመንፈሳዊው የውስጥ መንጻት ትዕምርታዊ (symbolic) የሆነ ውጫዊ መገለጫ ነው፡፡

ውሃ ለመንፈስ ቅዱስ ትዕምርታዊ ሆኖ መቅረቡን ደግሞ ቀጥለው የቀረቡ ጥቅሶች ያሳያሉ፡፡ ‹‹በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ፡፡ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና›› (ዮሐ 738) ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ›› (ዮሐ 414) ‹‹አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ›› (ራዕ 216)

‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ››(ሕዝ 3625-27) ሌሎችም ብዙ ጥቅሶች ቢኖሩም በዚሁ ይበቃናል፡፡

በብዙ ነቢያት ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ ውሎ የምናገኘው ‹‹የቅብዓት ውሃ›› ወይም (anointing Water) የሚለው ስያሜ፣ (ዘሁልቁ 517) ላይ የተወሰደ ስለመሆን አለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ባይኖረኝም፣ በዚህ ቦታ የተጠቀሰውም ‹‹የተቀደሰ ውሃ፣ ወይም የቅናት ውሃ›› በብሉይ ኪዳን ዘመን ባሎች ሚስቶቻቸው ከሌላ ወንድ ጋር መርከስ አለመርከሳቸውን በካህኑ ፊት ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ የዋለ ውሃ ነው፡፡ ሴቶቹ ከሕጋዊ ባላቸው ውጭ በመሄድ ከሌላ ወንድ ጋር ረክሰው ከሆነ፣ በጭናቸውና ሆዳቸው ላይ በግልጽ በሚታዩ በሽታዎች የሚመቱበት፣ ኃጢአት አልሠሩ እንደሆነም ደግሞ ውሃው በእነርሱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትልበት አሠራር ነው፡፡


እንደ ዳመና ዙሪያችንን የሞሉት እነዚህ አስረጆች፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በጸሎትና በልዩ ምሪት የተዘጋጀ የጥምቀት፣ የተጸለየበት፣ የቅብዓት ውሃ የታለመለትን ዒላማ ለመምታት የሚያስችል መንፈሳዊ አቅም ሊኖረው እንደሚችል ያሳያሉ፡፡ የውሃ ጥምቀት እየወሰዱ ሳለ ከሕመማቸው የተፈወሱ ሰዎች ምስክርነት የተለመደ ከመሆኑም በላይ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ቋንቋ እየተናገሩ ከውሃው የሚወጡ በርካታ ምዕመናን ደግሞ በዓይኔ ማየቴን እመሰክራለሁ፡፡ (ቀጣዩንና የመጨረሻ የሆነውን ስለተጸለየበት መሐረብ ወይም ጨርቅ አገልግሎት፣ እንዲሁም ስለማባዛት አገልግሎት፣ ያለኝን መጽሐፍ ቅዱሳዊና የግል አቋሜን፣ እንዲሁም በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች፣ ጌታ ቢፈቅድ በነገው ዕለት ይዤ እቀርባለሁ፤ ተባረኩልኝ

No comments:

Post a Comment