Tuesday, September 8, 2015

የአቋም መግለጫ (#2) - የተጸለየበት ዘይትና ውሃ አገልግሎት – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው!



የአቋም መግለጫ (#2) ማክሰኞ፣ ጳጉሜ 3/2007
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ

የተጸለየበት ዘይትና ውሃ አገልግሎት – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው!

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በነቢያትና በአገልግሎቶቻቸው ላይ ነቀፋና የሰላ ትችት እየተሰነዘረ ነው! እነዚህ ነቀፋዎችና ትችቶች ሦስት መሠረታዊ እንድምታ ያላቸው ናቸው፡፡ አንደኛው፣ ‹‹ነቢያት የተጸለየበት ዘይት፣ ውሃ፣ ጨርቅና ሌሎችም ማናቸውም ቁሳቁሶች ጌታን ስለሚሸፍኑ መጠቀም የለባቸውም›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹ነቢያት ቁሳቁሶቻቸውን ለገቢ ማስገኛነት እየተጠቀሙ ነው›› የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በደፈናው ‹‹ቁሳቁሶችን መጠቀምና የመሳሰሉ ልምምዶች አጋጋንታዊና የጥንቆላ ሥራ ነው›› የሚል ነው፡፡

የመጀመሪያና ሁለተኛ እንድምታዎች፣ ከሞላ ጎደል ተቀባይነት ያላቸው አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ግን በስውር መንገድ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ከልክሎ ለአጋንንት እውቅና የሚሰጥ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም፣ መላው የኢትዮጵያ ምዕመናን ጤናማ፣ ሚዛናዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ ይኖራቸው ዘንድ የግል አቋሜን እንደሚከተለው ይፋ አደርጋለሁ፡፡

ከላይ የቀረቡ ሁለት ምስሎችን እስኪ ለጥቂት ሰከንዶች አስተውለው ይመልከቱ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ምስሎች ሁለት ዓይነት የቴኦሎጂ አመለካከት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በቁጥር (1) የተመለከቱት ሊብራል ቴኦሎጂያኖች፣ በሳይንሳዊ መንገድ ካልተፈተነና ካልተረጋገጠ በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ፣ የሰው ልምምዶችንና፣ ባህልን እንደወረደ ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡

በሊብራሎቹ አመለካከት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፣ ወይም የእምነታቸውን የአንበሣ ድርሻ የሚወስደው ‹‹አመንክዮ›› ወይም (Reason) ነው፡፡ የንጽረተ ዓለማቸው መሠረት የገዛ ዓዕምሮአቸው ወይም ዕውቀታቸው ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሌላው አማኝ ሰፍ ብለው ለመጠቀም፣ አዘውትረው ለመጥቀስ ወይም በድፍረት ለመስበክ አቅም የላቸውም፡፡

ሊብራል ቴኦሎጂያኖቹ፣ በአስተምህሮአቸው ውስጥ የጎላ ቦታ ከያዘው ‹‹አመንክዮ›› ወይም (Reason) የተነሣ፣ ነቢያት የሚጠቀሙባቸውን የተጸለየበት ዘይት፣ ውሃ፣ ጨርቅና ሌሎችም ማናቸውም ቁሳቁሶች ሊቀበሉ ቀርቶ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ያለ ሣይንሳዊ መንገድ ቢሰበክላቸው ሊቀበሉ አይችሉም፡፡ ለነገሩ በሚወድዱት ሳይንሳዊ መንገድም ቢቀርብላቸው እንዲህ በቀላሉ ‹‹አሜን›› ማለት አይሆንላቸውም፡፡ እነዚህን ምሁራን በቃል ለማሳመን ከመልፋት፣ ድንጋይ ከስክሶ ስንዴ ዘርቶ ለማጨድ መልፋቱ የተሻለ ውጤት ያስገኛል፡፡

በዚህ መንፈስ ተጽዕኖ ሥር የወደቁ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና ተማሪዎች፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስብከቶችን በመተቸት፣ አገልግሎትን በመንቀፍ፣ አምልኮና ጸሎትን በመተቸት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በሳይንሳዊ መንገድ ያጠኑ ስለሆነና ታሪካዊ ዳራዎቹም ሆኑ መልዕክቶቹ ለእነርሱ አዲስ ባለመሆናቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ስብከት በጉጉት ለማዳመጥ ትዕግሥቱ የላቸውም፡፡ የሌሎችን አገልግሎት በአደባባይ ሲነቅፉ፣ ቃላት ሲሰነጥቁና ሲመጻደቁ የሚታዩትን ያህል፣ የተሻለ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ሲያበረክቱ አይታይም፡፡

ሊብራል ቴኦሎጂያኖቹ በአደባባይ ላይ ቆመው የሌሎችን ሰዎች አገልግሎት ሲነቅፉና ሲያጣጥሉ ይታያሉ እንጂ፣ ወደ ሕዝብ ወርደው ለታመመ ሲጸልዩ፣ አጋንንት ሲያወጡ፣ ትንቢት ሲናገሩ፣ ለጠፉትም ወንጌል ሲመሰክሩና ደቀመዛሙርት ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነት ችግሮች ላሉባቸው ሰዎች ከመጸለይ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል?

በተራ ቁጥር (2) የተመለከተው ምሳሌ ደግሞ ጤናማ ቴኦሎጂ እንዴት ያለ እንደሆነ ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡ እነዚህ ቴኦሎጂያኖች መሠረተ እምነታቸው በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ወይም በባህል ውስጥ የሠራውንም ሆነ ከግላቸውም ከሌሎችም ሰዎች ልምምድ የተረዱትን፣ እንዲሁም የራሳቸውን አመንክዮ አንድ ላይ አጣምረው ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን መረዳት የሚያሳድጉበት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሳይንሳዊ መንገድ አያስፈልግም ብለው ባያጣጥሉም፣ ነገር ግን ሰው ሠራሹ ሳይንሳዊ ትንታኔ መጽሐፍ ቅዱስን መወሰን አለበት ብለው ደግሞ አያምኑም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው እንዲፅፉ ያስቻለው ጌታ፣ የተጻፈውን ቅዱስ ቃል ማንኛውም ሰው መረዳት እንዲችል ያስችላል ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደወረደ የሚቀበሉና በውስጡ የተጻፉ መልዕክቶችንም በተግባር ለመለማመድ የሚጥሩ ናቸው፡፡

በርግጥ እግዚአብሔር ከሚያወሩት በላይ የሚለማመዱት አምላክም ጭምር ነውና፣ እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደወረደ በመቀበላቸውና በግልም የሚለማመዱት በመሆናቸው፣ እንዲሁም ጌታ በታሪክ ውስጥ የሠራውንና ተቀባይነት ያለው ባህል የሆነውን ሁሉ አንድ ላይ ስለሚቀበሉ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ የተመቹ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው፣ በዚህኛው መንደር የሚታዩ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴዎች በየጊዜው መነጋገሪያ ሲሆኑ የሚሆኑት፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በተራ ቁጥር (1) የተመለከቱ ቴዎሎጂያኖች መጽሐፍ ቅዱስን እናውቃለን ይበሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ኃይል የማይቀበሉ በመሆናቸውና፣ በተራ ቁጥር (2) መንደር የሚገኙ ቴኦሎጂያኖች በሚያካሂዱአቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ያነጣጠሩ ትችቶች የማቅረባቸው እውነታ ሲታይ፣ ከበስተኋላው ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነ ለመለየት አይቸግርም፡፡

የኢትዮጵያ ምዕመናን ሆይ፣ ለሁሉም ነገሮቻችን ዳኛው መጽሐፍ ቅዱስ ነውና፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጸለየበት ዘይት፣ ውሃ፣ ጨርቅና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ምን ይላል? በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሊኖረን የሚገባው አመለካከትስ እንዴት ያለ ነው? (ጌታ ቢፈቅድ፣ ይህንን በቀጣዩን ክፍል፣ ነገ እንመለከታለን፡፡)

No comments:

Post a Comment