የአቋም መግለጫ (ክፍል ሦስት)
3ኛ፣ የተጸለየበት መሐረብና የማባዛት አገልግሎት፣
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ
ይላል፣ ‹‹እግዚአብሔርን
እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም
ነው ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ›› (መዝ 66፡3)።
ሥራው ግሩም የሆነ ይህ እግዚአብሔር፣ በሰው ልጆች መካከል ግሩምና ድንቅ ነገሮች ሊያደርግ ይችላል፡፡ ኃይሉ ብዙ የሆነው የሠራዊት
ጌታ እግዚአብሔር፣ በመሐረብ ወይም በጨርቅ፣ በድንጋይም ሆነ በማናቸውም ግዑዝ ነገር ክብሩን ሊገልጥ ይችላል፡፡ ጠላት ግን ይህን
ይዋሻል፡፡
ስለ ጨርቅ አገልግሎት
ስናነሳ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረው ኡሪምና
ቱሚም አገልግሎት መቼም አይዘነጋም፡፡
ኡሪምና ቱሚም ለእስራኤል ልጆች ትክክለኛ ፍርድ ይሰጥ ዘንድ በአሮን ልብ ላይ የሚንጠለጠል፣ ማለትም በደረቱ ላይ በተዘጋጁ የኤፉዱ
ኪሶች ውስጥ የሚቀመጥ ትዕምርታዊ መገለጫ(symbolic) ነው፡፡ ከአሮን ዘመን በኋላም በነበሩ ሊቀካህናት ይህ ሕግ ሆኖ ይሠራበት
ነበር፡፡ ‹‹በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን
ታደርጋለህ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ
በልቡ ላይ ይሸከማል››(ዘጸ 28፡30)።
በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ ካህናትና ሌዋውያን መዘምራኑም ለአገልግሎት ወደ ቤተመቅደስ ሲገቡ ወይም ሲያመልኩ የበፍታ ኤፉድ ይለብሱ ነበር፡፡ የኤፉዱ ቀለም ነጭ ሲሆን፣ ትርጉሙ የሚያመለክተውም በፍጹም ልብ፣ በፍጹምም ነፍስ፣ በፍጹምም ሐሳብ ጌታ አምላካቸውን እንደሚያመልኩና ለእርሱ ብቻ እንደሚሰግዱ ነው፡፡ ኤፉድ መልበስ ለካህናት እንደ ግዴታ የሆነ ደንብ ሲሆን፣ በተሰጠ ልብ ጌታን ማምለክ ለሚፈልጉ ሁሉ የተፈቀደ ትዕምርታዊ የጽድቅና የቅድስና ምሣሌ ነው፡፡
‹‹ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር›› (1ሳሙ 2፡18)፤ ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር›› (2ሳሙ 6፡14)።
በአዲስ ኪዳን ዘመን
ደግሞ፣ ከጌታ ኢየሱስ ከራሱ ልብስ ጀምሮ ብዙ ተአምራቶች ተሠርተዋል፡፡ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል የነበረች፣ ከአሥራ ሁለት ዓመት
ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት የኢየሱስን ልብስ ከኋላው ሆና በዳሰሰች ጊዜ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን
ጊዜ መቆሙን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል(ማቴ
9፡20-21)፡፡ ሴትየዋ የተፈወሰችው የጌታ
ኃይል በልብሱ በኩል አልፎ ነው፡፡ ጌታ ወደ እርስዋ ዘወር ባለ ጊዜ፣ ‹‹እንዴት እኔን ትተሽ ልብሴን›› ብሎ አልነቀፋትም፡፡ ይልቁንም፣
‹‹ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል›› ነው ያላት፡፡
ሰዎቻችን የአገልጋዮችን
እጅ ለመጨበጥ፣ እጅ እንዲጭኑባቸው፣ ሁሌም እንደጣሩ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በስተጀርባው አገልጋዮችን ብጨብጥ፣ እጅ ጭነው ቢጸልዩልኝ፣
እባረካለሁ፣ እፈወሳለሁ፣ … የሚል እምነት ይዟል፡፡ ለእያንዳንዱ አባል ወይም ኮንፍራንስ ተሳታፊ ወይም ተከታይ እጅ መጫን ፈጽሞ
አይቻልም፡፡ ስለሆነም፣ አንዳንድ አገልጋዮች ጌታን ሰምተውና መንፈስ ቅዱስን ታዝዘው፣ በመሐረቦቻቸው ላይ ጸልየው ሕዝብ እንዲያገኛቸው
ቢሰጡና የተቀበሉትም ቢባረኩበት ምንም ችግር የለውም፡፡ ይህ አሠራር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይጋጭም፡፡
ሌላው
በሐዋሪያው ጴጥሮስ ሕይወት የተከሰተው አስደናቂ የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ የጴጥሮስ ጥላ በድውያንና
በርኵሳን መናፍስት በሚሰቃዩ ሰዎች ላይ ሲያርፍ ሁሉም ይፈወሱ ነበር፡፡ ‹‹ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ
ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና
በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር›› (የሐዋ 5፡15-16)። በሐዋርያት
እጅ እንዲህ ዓይነት ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ሲደረግ ብዙ ሰዎች ወደ ጌታ ይመጡ ነበር፡፡ ብዙዎችም ጌታን ያከብሩ ነበር፡፡
የጌታ ስም በእንዲህ
ዓይነት አስደናቂ መንገድ ሲከብር፣ የሐይማኖት ሰዎች ለጌታ ክብርን ሊያመጡ ሲገባ፣ ያደረጉት ተቃራኒውን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ
ይላል፣ ‹‹ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው። በሐዋርያትም ላይ
እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው›› (የሐዋ 5፡17-18) ይላል። ተመልከቱ! ድውያንና እርኩሳን መናፍስት የያዟቸው
ሰዎች ሁሉ በሐዋርያቱ ጥላ ያለምንም ክፍያ በነጻ በተፈወሱበትና ጌታም በዚህ የከበረበት ሁኔታ ሳለ፣ እነዚያን በጎ ሥራ የሠሩትን
ሐዋሪያት መደብደብና ወደ ወኅኒ መጣል ምን የሚሉት ዓይነስውርነት ነው! ጌታ ከዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ዓይነስውርነት ይጠብቀን፡፡
ደግነቱ፣ ያ ያከበሩት
ጌታ መልአኩን በሌሊት ወደ ወኅኒው ቤት ላከና፣ ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ባለበት፣ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት በተጠንቀቅ ቆመው
ሳሉ፣ ኮሽታ ሳይሰማ፣ የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና። ‹‹ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ››
አላቸው። ደቀመዛሙርቱም የተነገራቸውን ታዝዘው፣ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ፣ የፈውስ አገልግሎታቸውንና ልምምዳቸውን ቀጠሉ።
(የሐዋ 5፡19-20)
ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ሐዋሪያቱን
ያስደበደቡና በወኅኒ ያኖሩ የሐይማኖት ሰዎች ፍርደገምድል በሆነ ሸንጎአቸው ፊት ሐዋርያቱን ለማቆም፣ ሸንጎውንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች
ሁሉ ሰብስበው፣ ወታደሮቻቸውን ወደ ወኅኒ ቤት ቢልኩ፣ ሐዋርያቱ ግን
በወኅኒው ውስጥ አልነበሩምና ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፡፡ በሽንፈቱ አንገታቸውን የደፉ የሐይማኖቱ መሪዎች፣ ምንተፍረታቸውን በቤተመቅደሱ
ውስጥ እያስተማሩ ያሉትን ደቀመዛሙርት አምጥተውም በሸንጎ በማቆም፣ ‹‹(በኢየሱስ) ስም እንዳያስተምሩ አጥብቀው ቢጠይቋቸው፣ ጴጥሮስና
ሐዋርያቱ ፣ ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል›› የሚል ምላሽ በድፍረት ሰጥተዋል (የሐዋ 5፡27-29)፡፡
አገልጋዮች ሊታዘዙ የሚገባው
ጌታንና ቃሉን ነው እንጂ፣ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ላይ የሚቆጡ ሰዎች ሸንጎ የሚያቀርቡትን ማስጠንቀቂያ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ አይደለም፡፡
ሸንጎው መከራና ስደት ሊያመጣ መቻሉ የታወቀ ቢሆንም፣ ከክርስቶስ ፍቅር ግን ሊለየን አይችልም! ‹‹ሞት
ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም
ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል
ተረድቼአለሁ›› (ሮሜ 8፡38-39)።
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለተመሣሣይ ልምምዱ አንጀት በሚያቃጥል ቋንቋ ሲጽፍ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ…››(2ቆሮ 11፡26) ይላል፡፡ የኢትዮጵያ አገልጋዮች ወገኖች
እያደረሱባቸው ካለው ስደት ከቅዱስ ቃሉ በመማር እንዲጽናኑ አበረታታለሁ፡፡
በሐዋሪያ
ጳውሎስ እጅ እግዚአብሔር የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ ሰዎች ‹‹ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ
ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፣ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር፣ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር›› (የሐዋ 19 11-12)፡፡ ወገኖች
ሆይ፣ ቀደም ብሎ በቀረበው ጥቅስ ላይ፣ የሐዋርያ ጴጥሮስ ጥላ፣ የሚያርፍባቸው
ድውያንና በክፉዎች መናፍስት የሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ ይድኑ እንደነበር አይተናል፡፡ አሁንም፣ ሰዎች ከሐዋሪያ ጳውሎስ አካል ላይ ጨርቅ
ወይም ልብስ እየወሰዱ በድውዮችና በክፉዎች መናፍስት በሚሰቃዩ በሽተኞች ላይ ሲጥሉ ወይም ሲያስቀምጡ፣ ደዌያቸው ይለቃቸው ነበር፣
ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር፡፡ በሐዋርያት እጅ እንዲህ ዓይነት ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ሲደረግ ብዙ ሰዎች ወደ
ጌታ ይመጡ ነበር፡፡ ብዙዎችም ጌታን ያከብሩ ነበር፡፡
የነቢዩ ኤልያስ ጨርቅ ወይም መጎናጸፊያም ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ነቢዩ ኤልያስ በእሳት
ሠረገላ ወደ ላይ በተወሰደ ጊዜ መጎናጸፊያውን ለኤልሳዕ ጥሎለታል፡፡ መጎናጸፊያውን ከተቀበለ በኋላ የነበረው የነቢዩ ኤልሳዕ
ሕይወት ከቀድሞው አገልግሎቱ እጅግ የተለየ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህች መጎናጸፊያ ብዙ ዝርዝርና ሐተታ ባይሰጠንም፣
በኤልሳዕ ሕይወት የታዩ ለውጦችና ድንቃድንቅ ነገሮችን ስንመለከት፣ ከበስተኋላው አንድ የሆነ ጠረን ሊሸትተን መጀመሩ የማይካድ
ሐቅ ነው፡፡
መቼም
ቀድሞ ያልነበረ ነገር በአንድ ቀን፣ ያውም እንዲህ ባለ ቅጽበት ሲሆን ተአምራዊ ነውና፣ ከሰው አስተሳሰብ ወጣ ብሎ ማሰቡ የተሻለ
ይሆናል፡፡ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች፣ (1ኛ) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከመሄዱ በፊት፣ በመጐናጸፊያው፥
የዮርዳኖስን በመምታትና ወዲህና ወዲያም ተከፍሎ ከኤልሳዕ ጋር ሁለቱም በደረቅ መሻገራቸው አንድ ብርቱ ነጥብ ነው (2ነገ 2፡8)።
(2ኛ)
ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከተወሰደ በኋላ፣ ኤልሳዕ ከኤልያስ የወደቀውን መጐናጸፊያ አንስቶ፥ በዮርዳኖስ ዳር በመቆም፣ ውኃውን መታና፣
‹‹የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?›› ብሎ ሲናገር፣ ዮርዳኖስ ልክ እንደበፊቱ ሁሉ ወዲህና ወዲያ ተከፍሎ ኤልሳዕ መሻገሩ
ሌላው ብርቱ ነጥብ ነው(2ነገ 2፡13-14)።
(3ኛ)፣
ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ፣ ‹‹የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል›› ብለው መመስከራቸው፣
ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር መደፋታቸው ሌላው ብርቱ ነጥብ ነው (2ነገ (2ነገ 2፡15)፡፡ ከነዚህ ነጥቦች ተነስተን፣
‹‹የእግዚአብሔር ኃይል በኤልያስ መጎናጸፊያ አልፎ ሠርቷል›› ብሎ መናገር፣ ወይም ዛሬም ጌታ በተጸለየበት መሐረብና ጨርቅ አልፎ
ሊሠራ ይችላል ብሎ መቀበል ምንም ችግር አያስከትልም፡፡
በሀገራችን ብዙም ልማዱ የለም እንጂ፣ በሌላው ሀገር፣
አንድ ሰው ሲያለቅስ በአጠገቡ ያለ ሌላ ሰው እንባውን ማበሻ መሀረብ ከኪሱ አውጥቶ ይሰጠዋል፡፡ መሀረብ የተሰጠው ሰው ተቀብሎ
እንባውን ያብስበታል፣ ከሐዘኑ ይጽናናበታል፣ መንፈሱንም ያበረታታበታል፡፡ ይህ በዚያ ባህል ያለውን ሐዘንተኛ ለማጽናናት
የሚደረግ ባህላዊ መግለጫ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ደግሞ፣ ከሚያለቅሰው ሰው ጋር ድምጻችን ከፍ አድርገን እንድናለቅስና ሐዘንተኛው
የሚሆነውን ተከትለን እንድንሆን ይጠበቅብናል፡፡ በእኛ ባህል መነጽር የሌሎቹን ልማድ ስንመለከት፣ ‹‹ለሰው የማያዝኑ፣ ድንጋይ
ልብ ያላቸው ሰዎች›› ብለን ልንፈርጃቸው እንችል ይሆናል፡፡ እነርሱም በሐዘን ጊዜ በእኛ ሠፈር የሚታየውን ድራማዊ ገጽታ
ቢመለከቱ ሳይገረሙ አይቀሩም፡፡
ልማዶቻችን እንደየሰዉ መረዳት ይለያያሉ፡፡ ስለሆነም፣
ተራራ ተራራ የሚያካክሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረተ እምነቶቻችን እስከተጠበቁና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እስካልተጣሰ ድረስ፣
በጥቃቅን ልምምዶች ምክንያት ልንጣላና ልንለያይ አይገባም፡፡
የሀገራችን ነቢያትም ሆኑ ከውጭ የሚመጡ አገልጋዮች ከጌታ ሰምተውና ታዝዘው ለሚያገለግሉት ሕዝብ
በሚያበረክቱት የመሐረብ ወይም በጨርቅ አገልግሎት
ምክንያት ትርምስ ሊፈጠር አይገባም፡፡ የመሐረብ አገልግሎት የሚሰጡ አገልጋዮችን በርቀት ቆመን ከምንተቻቸው ይልቅ፣ ለምን እንዲያ
እንደሚያደርጉ ጠጋ ብለን ብንጠይቃቸው፣ በቂ ማብራሪያ ከራሳቸው አንደበት ልናገኝ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡
4ኛ፣ በእጅ መዳፍ ላይ አንጸባራቂ ሽርፍራፎች ወይም ዘይት መታየት
(oil or glitters)
ሰዎች
በእውነትና በመንፈስ ጌታን ሲያመልኩ መንፈሳዊ ነገሮች መከሰታቸው የተለመደ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጌታን በክብር ዙፋኑ ላይ
ተቀምጦ ማየትና መላዕክትን መመልከትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዓይነት ሰማያዊ ክስተቶች ማየት ይገኝበታል፡፡ አምልኮአችን መንፈሳዊ ደረጃው
ከፍ ባለ ቁጥር ከሰማያዊ አካላት ወይንም የብርሃን አካላት ጋር ንኪኪ ማድረጉ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ንኪኪ
በሚኖርበት ጊዜ በመካከላችን አስደናቂና አስገራሚ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስ እንደሚነግረን፣ ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር አይቶ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ፊቱ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ ‹‹…እግዚአብሔር ከእርሱ
ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ
ቁርበት አንጸባረቀ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። (ዘጸ 34፡29-30)፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር፣ እንደሚከተለው
ይላል፣ ‹‹ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥
ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም?››
(2ቆሮ 3፡7-8)፡፡
አዲስ
ኪዳን ከብሉይ ኪዳን ዘመን ይልቅ የተሻለ የእግዚአብሔርን ክብር የምናይበት እንጂ፣ ‹‹ድሮ እንዲህ ነበረ›› እያልን፣ ተረት እያወራን
በድንግዝግዝና በእውር ድንብር የምንኖረው አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ክብር በእኛ ላይ ሲገለጽ፣ እንኳን የእጃችን መዳፍ፣ ፊታችን፣
ልብሳችንም ጭምር ሊያንጸባርቅ ሊያብለጨልጭም ይችላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብና ዮሐንስን ይዞ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ፣ ‹‹በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ›› (ማቴ 1፡1-2)፡፡ እነርሱም፣ በታሪክ ከመስማት ባለፈ አይተዋቸው የማያውቋቸው
ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ማየት ቻሉ (ማቴ
17፡3)፡፡
ሰማያዊ
ነገር የሚያንጸባርቅ ክብር የተሞላ ነው፡፡ ይህን ክብር መናፈቅና መለማመድ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡ እኔና ቤተሰቤ ይህን ደጋግመን
አይተነዋል፡፡ ማንም ሰው ይህን ክብር ከናፈቀና ራሱን ካዘጋጀ መመልከት የሚችል መሆኑን ሳላፍርበት፣ ሳልሸማቀቅም እመሰክራለሁ፡፡
እውነተኛ
አምልኮ ሰዎችን ወዳልተለመደ የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የተጠራነውም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደዚህ የእግዚአብሔር
ክብር መገለጥ እንድንገባ ነው፡፡ ስለሆነም፣ በሙሴ ሕግና በነቢያት እንዲሁም በመዝሙራት፣ ደግሞም በወንጌላትና በሐዋርያት የተጻፈውን
ሁሉ ማስተዋልና መለማመድ እንችል ዘንድ እግዚአብሔር አእምሮአችንን፣ ዓይናችንንም ይክፈትልን፡፡
5ኛ፣ የማባዛት አገልግሎት፣
በብሉይ
ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስለማባዛት አገልግሎት በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ኤልያስ በድርቁ ዘመን
ወደ አንዲት መበለት ቤት ገብቶ፣ የነበራትን የመጨረሻ ጭላጭ ነገር እንድትሰጠው ካደረገ በኋላ፣ ተራግፎ ከነበረው ማድጋና ማሰሮ
ውስጥ ዱቄቱንና ዘይቱን በማባዛት ለሦስት ዓመታት ያህል ሳይጨረስ እንዲቆይ ማድረግ ችሏል (1ነገ17፡10-16)፡፡ ኤልሳዕም ባለ
ዕዳ ልጆቿን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስባት ለነበረች ባልቴት ዘይት በማባዛት ሽጣ ዕዳዋን እንድትከፍልና የቀረውን እንድትበላ አድርጓል
(2ነገ 4፡1-7)፡፡ ደግሞም የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበስቦ፥ ሰማርያን ከብቦ ባስጨነቃት ጊዜና የሚበላ ነገር
በጠፋ ጊዜ፣ ሰማሪያ በምርኮ እንድትንበሸበሽ መንፈሳዊ ዓለሙን በማዘዝ እህል እንዲረክስ አድርጓል(2ነገ 7፡1-20)፡፡ ሌላም ብዙ
ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡
በአዲስ
ኪዳን ደግሞ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቃና ዘገሊላው ውሃን በዘይት ከማባዛት ጀምሮ፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣዎች በማባዛት ከ5ሺ
በላይ ሰዎችን መግቦ 12 ቅርጫት ሙሉ አትርፏል፣ እንዲሁም ሰባት እንጀራና ጥቂት ዓሣዎች በማባዛት ከ4ሺ በላይ ሰዎችን መግቦ
7 ቅርጫት ሙሉ አትርፏል(ዮሐ 2፡1-11፣ ማቴ 14፡19-21፣ 15፡32-39)፡፡ ጌታችን እነዚህን ተአምራት ካደረገ በኋላ ደቀመዛሙርቱ
እንጀራ ባለመያዛቸው ምክንያት ሲጨነቁ አይቶ አንድ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል፣ እንዲህ ሲል፡- ‹‹ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን
እርሾ(ትምህርት)
ተጠንቀቁና ተጠበቁ!››(ማቴ 16፡5-12)፡፡ እኛም እንጠንቀቅ፡፡
ማጠቃለያ፣
የክርስትና እምነት በተለይም
የጴንጤቆስጤ መሠረተ አስተምህሮ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገኘው ድነት በኋላ፣ ዕለት ተዕለት ለሆነው እንቅስቃሴ በመንፈስ ቅዱስ አሠራርና
ልምምድ ላይ ይደገፋል፡፡ የጴንጤቆስጤ መሠረተ አስተምህሮ፣ ለማናቸውም አስተምህሮውና ልምምዱ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ዋና ዳኛና ማነጻጸሪያ
ያደርጋል፡፡
ጴንጠቆስጤዎች የመጽሐፉ
ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የመንፈሱ ሰዎች፣ የእሳቱ ሰዎችም ጭምር ናቸው፡፡ ይህ መንፈስ ከሚሰጣቸው ምሪት ተነስተው፣ ከእጅ መጫን በተጨማሪ፣
ዘይት፣ ውሃ፣ መሐረብ ወይም ጨርቅ ወይንም ማናቸውንም ቁሳቁስ ለአገልግሎታቸው ድጋፍ አድርገው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህንም የሚያደርጉት
ብድግ ብለው ከመሬት ተነስተው ሳይሆን፣ በምሪትና የጌታን ድምጽ ሰምተው፣ በሕዝብ ፊት ከመጠቀማቸውም በፊት በግላቸውና በቤታቸው
አረጋግጠው ካዩ በኋላ ነው፡፡
ይህን ሲያደርጉ፣ ከየአቅጣጫው
ነቀፋና ትችች መኖሩ አያከራክርም፡፡ ነገር ግን ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱሳችን የብዙ ቅዱሳን ልምምዶች የተሞላ እንደሆነና፣ እነዚያ ልምምዶች
ዛሬም ጌታ እንደፈቀደ አንዳንዶቹ ወይም ሁሎቹም በሥራ ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ
ለዘላለምም ያው ነውና (ዕብ 13፡8)፣ ትናንትና
የሠራው ጌታ ዛሬም በዙፋኑ ላይ እንደሆነ፣ በቁሳቁስ አልፎ ሊሠራ እንደሚችል አያከራክርም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናት የማይሻር፣ የማይወድቅና የማይለወጥ መሆኑን ካመንን፣ የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥
የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ እንደሚጠቅም ካመንን፣
በሙሴ በትር ውስጥ መለኮታዊ
ኃይል አልፎ ይሠራ እንደነበር አያከራክርም፡፡ ይህችን በትር ለመለኮታዊ ኃይል መተላለፊያነት የመረጠው፣ ሙሴንም ያለማመደው ጌታ
ራሱ እንደነበር አያጨቃጭቀንም፡፡
በሊብራሎች ዘንድ ስለአሥሩ
መቅሰፍቶች ተፈጥሮአዊ ማመኻኛ ቢሰጥም፣ በሙሴ በትር መለኮታዊ ኃይል አልፎ፣ በግብጽ ሀገር ብዙ ድንቆችና ተአምራቶች መደረጋቸውን፣
ባህር ተከፍሎ ሕዝብ መሻገሩን፣ ከአለት ውሃ መፍለቁንና ብዙ ሌሎች ተአምራቶች መደረጋቸውን አንክድም፡፡ ኤልሳዕ በኢያሪኮው አጨንጋፊና
ገዳይ ውሃ ላይ ባፈሰሰው ጨው ውስጥ(2ነገ 2፡20-22 )፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ የወደቀውን የምሳሩን ብረት ከጥልቅ ወደላይ
ለማንሳፈፍ የተጠቀመበት እንጨት ውስጥ(2ነገ 6፡1-7 )፣ መለኮታዊ ኃይል መኖሩን አንክድም፡፡
በሳምሶን ጸጉር ጉንጉን
ውስጥ መለኮታዊ ኃይል የነበረ መሆኑን አንክድም፡፡ ጸጉሩ ከተላጨ በኋላ ግን እግዚአብሔር ከእርሱ ተለየ፡፡ እርሱ ግን ይህን አላወቀምና
ወጥቶ እንደ ወትሮውም ጊዜ ለማድረግ ሲሞክር በቀላሉ በጠላት እጅ ወድቆ፣ ሁለት ዓይኑም ጠፍቶ እንደማንኛውም ተራ ሰው፣ ለጠላቱ
እህል የሚፈጭና ለብዙሃንም መሳቂያና መሳለቂያ ለመሆን መብቃቱን አንክድም(መሣ 16)፡፡
ለሙሴ ጽላት ቀርጾ የሰጠው፣ በፊቴ ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ ያለው ጌታ ራሱ ነበር፡፡ ይህ የቃል ኪዳኑ ታቦት የእግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ስለመሆኑ ትዕምርታዊ ምሣሌ መሆኑን
ደግሞ አንክድም፡፡ ይህን ታቦት ከተፈቀደለት ካህን በስተቀር
ማንም እንዳይነካው ሕግጋት ያወጣውም፣ እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲመሰክር፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ስለነካ፣ ስለ ድፍረቱ የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ነድዶ ነው ዖዛ እዚያው ተቀስፎ የሞተው (2ሳሙ 3፡6-8)፡፡ እኛም የማይገባንን
ነገር ያለቦታችን ገብተን ለመነካካት ስንሞክር የዖዛ ስብራት እንዳይገጥመን ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
በአሜሪካና በሌሎችም
አንዳንድ ሀገሮች የሚገኙ ወግ አጥባቂ ባፕቲስቶች ከኪንግ ጄምስ ትርጉም ሌላ አይቀበሉም፡፡ በእነዚህ ቤተእምነቶች ውስጥ ከዚህ ሌላ
ትርጉም አይሰበክም፣ በስህተት የሚሰበክበት ሁኔታ ከተፈጠረም፣ ብዙዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰማሉ፣ ስብከቱንም ሊያስቆሙ ይችላሉ፡፡
ይህ የዚያ ቤት ባህል ነው፡፡ ብዙዎቻችን ይህን ባህል ባንወደውና ባንቀበለውም፣ ልናከብርላቸው ግን ይገባል፡፡ እንደዚሁም ካሪዝማዊያኑና
ጴንጤቆስጤያዊያኑ የሚያነብቧቸውንና የሚለማመዷቸውን ትርጉሞች ሌሎች ሊያከብሩላቸው ይገባል፡፡ መደጋጋፍ እንኳ ባይቻል፣ በመከባበርና
በመተሳሰብ አብረን የእግዚአብሔርን መንግሥት መገንባት እንችላለን፡፡
ለምሳሌ ለመጥቀስ፣ እኔ
የውሃ ጥምቀት የወሰድኩት ገና ጨቅላ ሕጻን ሳለሁ ሲሆን፣ ውዳሴ አምላክ እየዘመርኩ፣ ከሰንበት ትምህርት ጀምሮ እስከ 10 ዓመቴ
ድረስ ያደግሁት በመካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ነገር ግን ወላጆቼ አሁን መግለጽ በማልፈልገው ምክንያት ወደ ጴንጠቆስጤ ቤተእምነት ወደ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ሲቀላቀሉ፣
እዚያው ተወስጄ 12 ዓመት ሲሞላኝ በጥልቅ ውሃ ተጠመቅሁ፡፡ አድጌ ወደ ሀይስኩል ስገባና፣ ከአካባቢዬ ራቅ ብዬ ስሄድ ደግሞ፣ የሄድኩበት
ከተማ ውስጥ የሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን አልነበረችም፡፡
ከልጅነቴ ጀምሮ ከአገልግሎት
ተለይቼ ለማላውቀው ለኔ ዓይነቱ ለጋ ወጣት ሁኔታው ከባድ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ ቀድሞ በሕጻንነት ጊዜዬ አብረውኝ በመካነ ኢየሱስ
ቤተክርስቲያን ያገለግሉ ጓደኞቼን አገኘሁና፣ ከእነርሱ ጋር ከከተማው ራቅ ብላ በቅርቡ ወደተከፈተች መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን
አብረን እየሄድን ማምለክ ጀመርን፡፡ ማንነቴን ሌላ ማንም ሰው ስለማያውቅ፣ ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ከጓደኞቼ ጋር አብረን
‹‹ለ›› መዘምራን መሠረትንና ማገልገልና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግ ጀመርን፡፡ ከዚህ ልምምዴ የተነሣ፣ ለእኔ የመካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን
በልቤ ውስጥ ለየት ያለ ቦታ አላት፡፡
የሚገርማችሁ ነገር፣
በረዥም ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አስተምህሮዬ፣ አንድም ቀን በሕጻናት ጥምቀት ላይ የከረረ አቋም ወይም ተቃውሞ አሰምቼ
አላውቅም፡፡ በተለይም፣ ተዋቂው የስነመለኮት ምሁር ኤሪክሰን ክርስቲያን ቴኦሎጂ በሚለው መጽሐፉ ገጽ 1040 ላይ፣ ከሚያገለግላት
ቤተእምነት የተለየ አቋም በማንጸባረቅ፣ የሕጻናት ጥምቀት ጉዳይ በማበረታታት ያስቀመጠው የመደምደሚያ ሐሳብ በጣም ይገርመኛል፡፡
እንግዲህ እኔ እስከማውቀው
ድረስ፣ መካነኢየሱስ በምትለማመደው የሕጻናት ጥምቀት ጉዳይ፣ በአብያተክርስቲያናት መካከል ክርክርና መወጋገዝ ደርሶ አያውቅም፡፡
ሌሎችም በሚያደርጓቸው ወጣ ያሉ ባህሎች ምክንያት በኅብረቱ ውስጥ ችግር አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ታዲያ በኅብረቱ ውስጥም ሆኑ ከኅብረቱ
ውጭ ያሉ ጴንጤቆስጤዎች ባላቸው ልምምድ ምክንያት ለምን የከረረና የመረረ መለያየት ይሆናል? ቃሉ ምን ይላል ተብሎስ ለምን አይመረመርም?
የመካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን
በኮሚኒስቱ ዘመን፣ ለኢትዮጵያ ጴንጤቆስጤዎችና ለጴንጤቆስጤ ልምምዶች በሯን በሰፊው በመክፈትና፣ በልምምዱ ውስጥ የገቡትን እንደነ
መኮንን ነገራ፣ ተስፋዬ ዲነግዴና በሊና ሣርካ የመሳሰሉ አገልጋዮቿን ሳታሳድድ፣ ይልቁንም አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማመቻቸት ታሪክ
የማይረሳው ሥራ ሠርታለች፡፡ ከክቡር ጉዲና ቱምሣ ጀምሮ እስካሁን ያሉ መሪዎች ለሉተራዊ ማንነታቸው ሳያዳሉ ከካሪዝማዊያኑና ጴንጤቆስጤዎቹ
ጋር አብረው በፍቅር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን እግራቸው ከኅብረቱ ውስጥ ገና ወጥቶ ሳያበቃ፣ ጴንጤቆስጤዎቹ ዋጋ መክፈል ጀምረዋል፡፡
መደምደሚያ፣
በርግጥ አሁን እየተደመጠ
ያለው የልምምዶች ነቀፋ፣ ከባዶ መረጃ የመጣ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ አገልጋዮች የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎችን ለማይገባ ዓላማ
ጥቅም ላይ ማዋላቸውም አይካድም፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ቁሳቁሶችን በመጠቀም ሒደት ላይም አንዳንድ ግልጽ የሆኑ ችግሮች ይኖራሉ፡፡
እነዚህን ሒሶች ልንውጥና የሚሰነዘሩብንን ነቀፋዎች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ዛሬ ነገ ሳንል፣ ልንፈታቸው ይገባል፡፡
በእኛ ምክንያት አሕዛብ እንዳይሰናከሉ፣ የእግዚአብሔርም ስም እንዳይሰደብ ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባል፡፡
ሁሉም አገልጋዮች አንድ
ዓይነት አቋምና ልባዊ ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ፣ የጸጋ ስጦታውን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በሚጣረስ መልኩ
ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ስለሆነም በተሰጠን ጸጋ እንዴት እየሠራንበት እንደሆነ አስተውለን እንወቅ፡፡ ዛሬ የምንሠራውና የምንዘራው አረምና
አረማሞ፣ ነገ እኛኑ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል አንርሣ፡፡
በትልቅም ቤት የእንጨትና
የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉና ልንጠነቀቅ
ይገባል (2ጢሞ 2፡20)፡፡ ሐዋርያትና ነቢያት የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጣቸው መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን
መሠርተዋል፡፡ እኛ በዚህ መሠረት ላይ ጡብ የምንጨምር ስለሆነ፣ ይህን መሠረት ሳናበላሽና ሳንለቅቅ፣ እያንዳንዳችን በእርሱ ላይ
እንዴት እንደምናንጽ እንጠንቀቅ(1 ቆሮ 3፡10)፡፡
የቃልኪዳኑ ታቦት እጅግ
አስገራሚ ነገሮችን ያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ እስራኤል በኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ግን፣ ሕዝቡን ከአደጋ የማያድን መሆኑን አንዘንጋ፡፡
ይህ ታቦት እንዲህ ያለ ክብርና ኃይል ያለው ቢሆንም፣ ሰው እንዲያመልከው አልተፈቀደም፡፡ በአገልግሎታችን በምንጠቀማቸው ልዩ ልዩ
ቁሳቁሶች አልፎ ጌታ ለክብሩ ሊጠቀም ቢችልም፣ ድንቅና ተአምራቶች ቢሠሩ፣ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት በፊቴ አይሁኑልህ›› ያለው ጌታ ከእርሱ
ሌላ ጣዖት በፊቱ እንድናስቀምጥ ፈጽሞ እንደማይወድድ፣ ጣዖት ሆኖ ከተገኘም ከመቅጣትና ከማዋረድ ወደኋላ የማይል አስፈሪ አምላክ
መሆኑን በማወቅ፣ ማናቸውንም ነገሮች ስናደርግ እርሱን በመፍራትና በፊቱ በመንቀጥቀጥ ይሁን፡፡
ድውያንን የሚፈውሰው
ዘይቱ፣ ወይም ውሃው፣ ወይም መሐረባችን ወይም ጨርቃችን ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ አልፎበት መሆኑን አንርሳ፡፡ እርሱ እጁን
ከእኛ ላይ ካነሳ፣ እኛም ሆንን ቁሳቁሶቻችን ባንዴ የማንጠቅም ባለመድኃኒቶች፣ ወይም አልጫ በመሆኑ ምክንያት ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው
እንደሚረገጥ ጨው እንደምንሆን አንርሣ፡፡ በአገልግሎታችን ሁሉ ክብር የሚገባው ለጌታ እንጂ፣ ለቁሳቁሶች እንዳይሆን በንግግራችንም
ሆነ በአስተሳሰባችን ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ በፀሎታችን ጉልበት ምክንያት እነዚህ ነገሮች እንደተባረኩ በማሰብ፣ የተፈወሱና ከአጋንንት
እስራት የተፈቱ ሰዎችን በማየት በራሳችን መመካት እንዳንጀምር ዓይኖቻችንም ከጌታ እንዳናነሣ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
በጸጋ አገልግሎት ውስጥ
ለብዙ አገልጋዮች መውደቅና ባጭር መቀጨት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ የገንዘብ ፍቅር ነው፡፡ በዚህ መንገድ ጠላት እንዳያገኘንና
ያለ ርህራሄ ሰባብሮ እንዳይጥለን፣ እንጠንቀቅ፡፡ አገልግሎታችን ዘመን እንዲዘልቅ፣ ሳንወድቅና ሳንወርድ ጌታ እስኪመጣ ድረስ እንድንገሰግስ፣
ወይም በዕድሜ ገፍተን ሌላ እስኪተካን ዕለት ተዕለት መጸለይና መጠንቀቅ እንዳለብን፣ እግዚአብሔርንም እየፈራን መመላለስ እንደሚገባን
ለቅጽበትም ቢሆን አንዘንጋ፡፡
የጸጋ ስጦታዎች፣ አገልጋዩም
ሆኑ ማናቸውም ቁሳቁሶች ጌታን የሚሸፍኑ፣ የእግዚአብሔርን ክብር የሚነኩ መሆን የለባቸውም፡፡ የተአምራትና ድንቆች ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር
ብቻ ነውና፣ ማናቸውንም ነገር ስንጠቀም ለእግዚአብሔር ክብር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በምናደርገው ማናቸውም ነገር የእግዚአብሔር
ስም እንዳሰደብ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ ስለምናደርገው ስለማናቸውም ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ እንደምንሰጥ ማወቅ ይገባል፡፡ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችንን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምናደርግ
በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑረን(1ጴጥ 3፡16)። አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፣ እምነትና
በጎ ሕሊና ይኑረን (1ጢሞ
1፡19)፡፡
ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን
እርሾ (ትምህርት)
እንጠንቀቅ፣ እንጠበቅ! (ማቴ 16፡5-12)፡፡ የሰዎችን ትችትና ማስፈራሪያ በመፍራትም፣ በወንጌል አገልግሎታችን፣ እንዲሁም ከመንፈስ
ቅዱስ የታዘዝነውን እንዳናርግ ቢከለክሉንም፣ ከሰው
ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ እንደሚገባ እንወቅ (የሐዋ 5፡29)፡፡ እግዚአብሔር ያነጻውን እኛ አናርክሰው (የሐዋ 10፡15)፡፡ የተጻፈው ሁሉ ለጥቅማችን ነውና፣ የእግዚአብሔር መንፈስ
ያለበትን መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ሁሉ ፊት በድፍረት ከመስበክ፣ በልሣን ከመናገርም አንቆጠብ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን
ይባርክ፡፡
አዲሱ 2008 ዓ.ም.
መልካም ነገሮች ሁሉ መቀበያ የተባረከ ዓመት ይሁንላችሁ፡፡
በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ
ቅዱስ አንድ አምላክ ስም፡፡
No comments:
Post a Comment