የአቋም መግለጫ (#1) እሁድ፣ ጳጉሜ 1/2007
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ
የነቢይ ቲቢ ጃሹዋ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
መንፈሳዊ እሴት ይጨምርልናል፡፡
በናይጄሪያዊው ነቢይ ቲቢ ጃሹዋ ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አስተያየቶች
ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የመወሰኑ ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ፣ መምጣቱን
በሚደግፉና በማይደግፉ አካላት መካከል እጅግ ከባድ ውጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ውጥረት በከፍተኛ ጥበብና በሰከነ መንገድ ካልተያዘ
በስተቀር፣ አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት ይዘው የቆዩትን የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ወደማፈራረስና ወደ መበታተን
ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት የጴንጠቆስጤዎቹም፣ የሉተራኑም፣
የሜኖናይቱም፣ የባፕቲስቱም፣ የፕሬስቢተሪያኑም፣ የሌሎችም ጭምር ነው፡፡ ይህ ኅብረት በእነዚህ የተለያዩ ዲኖሚኔሽኖች ያለውን የውስጥ
ልዩነቶች በማክበርና፣ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት የተቋቋመ፣ በብዙ መስዋዕትነትና እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች መካከል
እያለፈ ዛሬ ወደደረስንበት ምዕራፍ የተሸጋገረ ተቋም ነው፡፡
ይህ ተቋም ያለ ማንም ውጫዊ ጫና፣ ነገር ግን በመለኮታዊ አሠራር፣ ከኅብረት
ወደ አንድነት እየተሸጋገረ ያለ፣ ለሌሎችም ሀገሮች የሚተርፍ አርአያነት የተጎናጸፈ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም፣ በጥንቃቄ ሊሄድ የሚገባው
ተቋም ነው! ይህንን ተቋም ሊመሩ የሚገባቸው መሪዎች፣ በጥንቃቄ ሊመሩ ይገባቸዋል! ይህንን ተቋም የሚመሩ ግለሰቦች አባቶቻችን ሲገነቡት
በነበረው መሠረት ላይ ጡብ የሚደምሩና እሴት የሚጨምሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት መሪዎች የሠራዊት ጌታ
እግዚአብሔር ለምድሪቱ ያለውን የወቅቱን ፈቃድ ሊያውቁና ሊከተሉትም ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ ዝግጁነት ባይኖራቸው፣ ቢያንስ በመላው
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች ዘንድ ያለውን የነፍስ ጩኸት ሊያዳምጡ ይገባል፡፡ እነዚህ ሁለቱን ለማድረግ ባይችሉ፣ ቢያንስ ለዚህ
ኅብረት መቋቋምና ማደግ ለተሰዉ፣ ብዙ ስቃይና ዋጋ ለከፈሉ አባቶቻችንን ክብር ሲሉ፣ እንዲሁም ከትውልድና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳን
ሲሉ ራሳቸውን ካሉበት ኃላፊነት ማንሳት ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
በወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ሥር የታቀፍን ቤተእምነቶችና ተባባሪ
ድርጅቶች በየግል ሰነዶቻችን ላይ ካልሆነ በስተቀርና ጥቂት ግለሰቦች የምናራምደው የየራስ አስተምህሮ ከመኖሩ በስተቀር፣ በሁሉም
አማኞቻችን ዘንድ ያለው መንፈሳዊ ልምምድ አንድ ዓይነት ነው ብሎ መናገር፣ መደምደምም ይቻላል፡፡ ይህንን እውነት ለመቀበል የሚከብደው
ቢኖር፣ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ጥናት ማካሄድ ይችላል፡፡
መንፈሳዊ ምግብና ውሃ የተራበውና የተጠማው ሕዝባችን ወቅታዊ ጥያቄው ግልጽ
ነው፡፡ ሕዝባችን የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ተርቧል፤ የላቀ ደረጃ የጸጋ ስጦታዎች አገልግሎት ተጠምቷል፡፡ ሕዝባችን እረኛ እንደሌላቸው
በጎች ተጥሎና ተጨንቆ ነው ያለው፡፡ ሕዝቡ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይቶ የሚያዝንለትና መንፈሳዊ ረሀቡንና ጥማቱን የሚመግብና
የሚያረካ መሪ እየፈለገ ነው፡፡ ሕዝቡ መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው የበሩ፣ ወንጌልን በሥልጣን የሚሰብኩ፣ በስሙ አጋንንት የሚያወጡ፣ ድውያንን
የሚፈውሱ፣ ትንቢት የሚናገሩና በቃልና በሥራ ምሣሌ የሚሆኑ መሪዎች ይፈልጋል፡፡ በዚህ በዚህ አቅጣጫ ሕዝባችን በመሪዎቹ ተስፋ እየቆረጠ
ሄዷል፡፡ በጸጋ ስጦታ አጠቃቀም፣ ለሚመሩት ሕዝብ አርአያ የሆኑ መንፈሳዊያን መሪዎች ቁጥር አጥጋቢ አይደለም፡፡
የአብያተክርስቲያናት መሪዎች፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ ያገኘነውን የእምነት
ነጻነት በሚገባ አልተጠቀምንበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙ ቤተእምነቶች በየራሳችን ቤተእምነት ውስጥ አባሎቻችንን አስተባብረን፣ በታላቁ
ተልዕኮ ሥራ ላይ አብሮ ከመሰለፍ ይልቅ በጥቃቅን ነገሮች ምክንያት እርስ በርስ ባለመግባባት በርካታ ዓመታት አባክነናል፡፡ እርቅና
ሰላም ለማውረድ ባለመዘጋጀታችን ምክንያት መሪዎች አንዳችን በሌላችን ላይ ጉዳት ስናደርስና፣ ሕዝባችንንም ስንበድል ቆይተናል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ፣ የመንፈስ ቅዱስን እንቅስቃሴ ከምድሪቱ ላይ
የማጥፋት ዘመቻ በሰፊው ተከፍቷል፡፡ በቅርቡ በነቢይ ቡሽሪ ላይ፣ ቀጥሎም በነቢይ ታምራት ላይ፣ አሁን ደግሞ በቲቢ ጃሹዋ ላይ የተከፈቱ
የጥላቻ ዘመቻዎች የዚሁ ዓላማ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ የዓመጻ ዘመቻዎች በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ግቦች አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው
የጴንጠቆስጤን እንቅስቃሴ መደፍጠጥና እሳቱን ከምድሪቱ ላይ ማስወገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት
ኅብረት ማፈራረስና መበታተን ነው፡፡
የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ጥላ፣ አባል ቤተእምነቶቹ አንዳቸው
የሌላቸውን አስተምህሮና ልምምድ የሚጫንና፣ አንዱ ቤተእምነት በሌላው ቤተእምነት አስተምህሮና ልምምዶች ላይ ዘመቻ የሚያካሂድበት
የእርስ በርስ ጦርሜዳ ሳይሆን፣ በመከባበርና በመደጋገፍ መርህ ላይ የተመሠረተ ኅብረት ነው፡፡
በዚህ ኅብረት ውስጥ ያሉ አባል ድርጅቶች ያሏቸው ዶክትሪኖች፣ ልምምዶች የተለያዩ
ናቸው፡፡ ለምሣሌ ብንወስድ አባል ድርጅቶቹ በየፊናቸው የሚያከናውኗቸው የውሃ ጥምቀትም ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መረዳቶችና ልምምዶች
ወጥ አይደሉም፡፡ በዚያው ኅብረት ውስጥ፣ አንዱ ‹‹በዛሬው ዘመን ሐዋርያትና ነቢያት የሉም›› ብሎ ሲያምን፣ ሌላው ደግሞ ‹‹በቀድሞው
ዘመን ይሠራ የነበረው መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በተመሣሣይ ሁኔታ ሊሠራ ይችላል›› ብሎ ያምናል፡፡
አባል ድርጅቶቹ የአገልግሎት አጋርነት እንጂ፣ የዶክትሪን አንድነት ወይም
ወጥነት የላቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ባለበት፣ አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ተነስቶ፣ ‹‹የእኔን አስተምህሮና ልምምድ ‹ስታንዳርድ› ወይም
ዋና መለኪያ አድርገህ ካልተቀበልክ!›› ብሎ ሊያስገድደው አይችልም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለውም፣ ጥቂት
አካላት ቡድናዊና ድብቅ አጀንዳቸውን፣ ወደ መላው የወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት አምጥተው ለመጫንና የሚያደርጉትም እንቅስቃሴ
ገና በእንቁላሉ ሳለ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ አለበዚያ ኋላ አድጎ አድጎ የአብያተክርስቲያናት ኅብረትን የማፈራረስ ደረጃ እንዳይደርስ
ያሰጋል፡፡
ከሀገሪቱ ዜጎች ወደ 20% ለሚሆነው ሕዝባችን የተሻለ አመራርና አገልግሎት
ያስፈልገዋል፡፡ በየአጥቢያዎቻችን ለሚገኙ አባሎቻችን ጥናታዊ መጠይቆች ብናቀርብላቸው በምድራችን ላይ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ
እንዲስፋፋ ይፈልጋሉ፡፡ በርግጥ ሕዝባችን እንደ ነቢይ ቲቢ. ጆሽዋ ያሉ አገልጋዮች በምድሪቱ መጥተው እንዲያገለግሉት ይፈልጋል፡፡
የእነዚህ አገልጋዮች መምጣት ለወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት በተለይም ለጴንጠቆስጤያውያን
የሚጨምሩት እሴት መኖሩ አይካድም፡፡ ስለሆነም፣ ናይጄሪያዊው የሲናጎግ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽንስ ዋና መጋቢ፣ የእግዚብሔር ሰው፣ ነቢይ
ቲቢ ጆሹዋ የጌታ ፈቃድ ሆኖ፣ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ የሚጨምርልን እሴት ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም፣ ይህ ታላቅ የዘመናችን የእግዚአብሔር
ሰው በስቴዲዮምና በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝቶ የሚሰጠውን አገልግሎት የመካፈል ዕድሉ የሚያጋጥማቸው ወገኖች በኮንፍራንሱ ወቅትም ሆነ
ከኮንፍራንሱ በኋላ የሚመሰክሩትን ነገር አብረን የምናየውና የምንሰማው ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
-------------
ከነገ ጀምሮ፣ በነቢያት አገልግሎትና ልምምዶች፣ ስለዘይት አገልግሎት፣ ስለተጸለየበት ውሃ አገልግሎት፣ ስለተጸለየበት መሐረብ (ጨርቅ፣ ቁሳቁስ) አገልግሎት፣ ስለማባዛት አገልግሎት፣ ስለፈውስና ተአምራት አገልግሎት ወዘተ… አጫጭር መግለጫዎች ይፋ አደርጋለሁ፡፡
ከነገ ጀምሮ፣ በነቢያት አገልግሎትና ልምምዶች፣ ስለዘይት አገልግሎት፣ ስለተጸለየበት ውሃ አገልግሎት፣ ስለተጸለየበት መሐረብ (ጨርቅ፣ ቁሳቁስ) አገልግሎት፣ ስለማባዛት አገልግሎት፣ ስለፈውስና ተአምራት አገልግሎት ወዘተ… አጫጭር መግለጫዎች ይፋ አደርጋለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment