Friday, September 4, 2015

መሰወር አበቃ!!!!!!!

ዲቮሽን 359/07፥ አርብ፥ ነሐሴ 29/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
መሰወር አበቃ!!!!!!!
በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ማቴ 5፡14
እስከዛሬ ተሰወርን አይደል? ተቆልፎብን በጭላንጭል በበር ቀዳዳ እንደሚያይ ልጅ ሆነን ስንት ጊዜ አለፈ! ሲያስቡት እኮ ቀላል ይመስላል! ግን በእውነት ቀላል አይደለም። አሁንማ ተነቃቅተናል! ማን ሰውሮን እንደነበር ገብቶናል! አይ ጠላት ሞኝነቱ፣ የእኛን ኢየሱስ ምን የሚያግደው ነገር ያለ መስሎት ነው፣ በስውር ሊያስቀረን ያሰበው! እኛ እኮ በማይለወጥ ኪዳን፣ በዘላለም ፍቅር፣ በጽኑ ክንድ፣ በበረታች እጅ የተያዝን ከወርቅም ከእንቁም በላይ የሆንን የእግዚአብሔር ልጆች ነን!!
አይ ዓቅምን አለማወቅ! እንዲያው ጠላት ምን ቢደፍር ነው፣ ከተማን የምናክል ሰዎች ሊሰውረን የበቃ! እንዴት ቢያደነዝዘን ነው፣ መብራት ሆነን ከእንቅብ በታች የተቀመጥነው!
ለነገሩ ግዴለም፣ የዓለም ብርሐን፣ የምድር ጨው ሆነን በበቀል እንደምንገለጥ አውቆ እኮ ነው፣ ዋጋችንን ያሳነሰብን!!! አሁን ስናበራ ጉዱ ይፈላበት አይደል! መታሰቢያው እስከማይገኝ ድረስ ጥርግርግ አድርገን ስናስወጣው ምን ይል ይሆን!
ዛሬ በመከራችን ላይ እንስቅበታለን! ዛሬ ባስለቀሰን በማናቸውም ጉዳይ፣ የትም ሆነን እንስቅበታለን። ምክንያቱም፣ መሰወር አ-በ-ቃ። ዛሬ በመከራችሁ ላይ ፍርስ ብላችሁ ሳቁበት! እረ ሳቁ በደንብ! ማልቀስ፣ መቆዘም፣ መተከዝ አ-በ-ቃ እኮ!!! አሁን ተራው የእኛ ነው-ወገኖቼ- በሉ ሳቁ!!! ከት-ከት-ከት ብላችሁ ሳቁ!!
ብርሐንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺና አብሪ። ኢሳ 60፡1
ኢየሱስ ጌታ ነው! ኢየሱስ ያድናል!!!
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 7 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment