Thursday, September 3, 2015

አዎን፣ ከናዝሬት መልካም ነገር ወጣ!!!

ዲቮሽን 358/07፥ ሐሙስ፥ ነሐሴ 28/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


አዎን፣ ከናዝሬት መልካም ነገር ወጣ!!!


ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? ዮሐ 1፡46


እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ አዎን ከናዝሬት መልካም ነገር ወጣ!!!! ጠላታችን፣ “እውን አንተ ነህ እንዲህ የሆንከው?” እያለ ሲከሰን፣ መልሳችን እጥር ምጥን ያለና ግልፅ ነው፤ አዎን እኔ ነኝ። ነው መልሳችን።



የማንጠቅም፣ አልባሌ፣ ተራ ሰዎች ነበርን። ሆኖም ግን፣ ከእኛ መልካም ነገር ወጣ። ስማችን፣ አድራሻችን፣ አይታወቅም ነበር፣ ግን ይባስ ብሎ፣ ለሚጠፉት የሞት ለሚድኑት ደግሞ የሕይወት ሽታ ሆነን ብቅ አልን።


መቼም ዲያብሎስን ይከፋዋል፣ ወይም የደገሰልን ድግስ ይበላሽበታል ብለን ወህኒቤት እንቅርለት እንዴ?! አሊያስ ሌጌዎንና ሠራዊቱ በሐዘን ይዋጣል ብለን በምድረበዳ ቀልጠን አንቀር! ወይስ የጠላት የሞት ግብዣ ከንቱ ከሚሆንበት ብለን በሐጢያት፣ በድካም፣ በጭለማ ተውጠን አንቀር ነገር!


እረ ገና ምኑ ተይዞ! ገና ከዚህም የሚበልጥ ነገር እናያለን። ይህማ ጅማሬያችን ብቻ እኮ ነው። የሕይወትን ውሃ ጠጣነው፣ ዳግም መጠማት የለም፤ የሕይወትን እንጀራ በላነው ዳግም መራብ ብሎ ነገር እኛ ሠፈር የለም። እረ አለ ገና!! ገና ከዚህ የሚበልጥ ክብር፣ እልልታ፣ ድልና ምስጋና ማንን ሆነና የሚጠብቀው! እኛን ብቻ እኮ ነው! አሁን እኮ ድል ነሺዎች እንጂ፣ ድል ተነሺዎች አይደለንም። ገና ተጠራጣሪ እና ፈሪ ልባ ያላቸውን ሁሉ እየጎተትን እናወጣለን፣ እረ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቀን እናድናለን!!


ገና ምኑ ታይቶ፣ ራስ እንጂ ከእንግዲህ ጭራ መሆን አ-በ-ቃ!!!! በኢየሱስ በመስቀል ላይ ስራ አበሳችን ሁሉ ተ-ወ-ገ-ደ።


በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ እንዲህ ያለ እምነት አለን፣ ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ በራሳችን ብቃት ከእኛ የምንለው አንዳች ነገር የለም። 2 ቆሮ 3፡4

---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 8 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment