Saturday, August 8, 2015

እውነት ራሴን እወደዋለሁ?????

ዲቮሽን 332/07፥ ቅዳሜ፥ ነሐሴ 2/07 ዓ/ም 
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

እውነት ራሴን እወደዋለሁ?????

ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። ዘሌ 19፡ 18

መንፈስ ቅዱስ ባልንጀራን ስለመውደድ፣ ጠላትን ስለመውደድ፣ ከራሳችን ይልቅ ለሌላው ስለማሰብ አጥብቆ ይመክረናል። እናም የይቅርታንና የፍቅርን ምሳሌ ሲያስተምረን፣ “ባልጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይለናል።

ዘንድሮ ግን ብዙዎቻችን፣ እንኳን ሌላውን ልንወድ ራሳችንን እንኳን ጠልተን፣ በገዛ ስጋችን እና ነፍሳችን ላይ ፈርደን፣ እንደምንኖር የታወቀ ነው።

ራሳችንን ብንወድማ ወንድሞቻችንን እየያዝን ፍርድቤት ለፍርድቤት አንጓተትም፣ ራሳችንን ብንወድማ ሰውነታችንን በመጠጥ እና በዝሙት አናቆሽሽም፣ ራሳችንን ብንወድማ የሲኦል ፍርደኞች ለመሆን አንጋፋም፣ ራሳችንን ብንወድማ ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል እንግዳ ትምሕርት እና ሕይወት ውስጥ አንገባም።

ራሳችንን ብንወድማ መንፈሳችንን ከማይጠቅም ነገር እንከለክላለን፣ ራሳችንን ብንወድማ፣ በጸሎት እየተጋን የእግዚአብሔርን ፊት የበለጠ እንፈልጋለን፣ ራሳችንን ብንወድማ ውሸትንና ክፋትን ከጉሮሮአችን እናርቃለን፣ ራሳችንን ብንወድማ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ብቻ እንፈልጋለን። ራሳችንን ብንወድማ የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግስት እንፈልጋለን።

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ። መዝ 139:14

አንተ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ እባክህ አሁን ራሳችንን የምንወድበትን ኃይል ላክልን? ሁሉን ታደርግ ዘንድ በእርግጥ ትችላለህና ተባረክልኝ።

No comments:

Post a Comment