ዲቮሽን 357/07፥ ረቡዕ፥ ነሐሴ 27/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ጌታን ጠበቅን፣ ከበርን!!!!
በለሱን የጠበቀ ፍሬውን ይበላል፣ ጌታውን የሚጠብቅ ይከብራል። ምሳ 27፡18
መጠበቅ ምን ማለት እንደሆነ ለማያውቅ ሰው፣ ምናልባት አንድ የልብ ወዳጅን አንድ ካፊቴሪያ ውስጥ ቁጭ ብሎ አሥር ደቂቃ ወይም ግፋ ቢል አንድ ሰዓት መጠበቅ የሚመስለው ይኖራል። ወይም በፀሎት ጌታን ዓመት ሁለት ዓመትም መጠበቅ ሊመስለው ይችላል።
መጠበቅ ማለት እንደ አብርሐም ሐያ አምስት ዓመትም ሊሆን ይችላል፣ ወይም መቶ ዓመትም ሊሆን ይችላል። አሥራ ሁለት ዓመትም፣ ሰላሳ ስምንት ዓመትም ሊሆን ይችላል። ከህጻንነት ጀምሮም ሊሆን ይችላል፣ ከማህጸን ጀምሮም ሊሆን ይችላል። ወይም ባስ ሲል እንደ አስፈላጊነቱ እስከ ሞት ድረስም ሊሆን ይችላል።
መጠበቅን እኛ አጣጥመን እናውቀዋለን!!! እረ እንዲያውም 'መጠበቅ-እና ፈተናዎቹ'፣ 'መጠበቅና ጥቅሞቹ' የሚል ሌክቸርም አስፈላጊ ከሆነ እንሰጣለን። ጠላታችን ተስፋ ይቁረጥ፣ ወደፊትም ይህንን ታማኙን ጌታ፣ የሚረባንን የሚያውቅልንን ኢየሱስን እ-ን-ጠ-ብ-ቃ-ለን!!!! ቢገድለንም ቢያድነንም እንጠብቀዋለን። የሰይጣንን አማራጭ አንቀበልም!!!
ግን የጠበቅነው በእርግጥ የሚመጣውን ጌታ ነው። ዘገዬ ብለን ጥለን መሔድ ጠፍቶን እኮ አይደለም። እንኳን ዓይን ተከድኖ በሚገለጥበት ቅጽበት መቶ ሺህ አማራጭ በበዛበት በዚህ እሳት በሆነ በመጨረሻው ዘመን ቀርቶ፣ ድሮም ቢሆን የራሳቸውን አማራጭ የተከተሉ አሉ፣ ፍጻሜያቸው አላማረም እንጅ።
ስለዚህ ከቦታችን ንቅንቅ ሳንል፣ በእርግጥ በራሱ ጊዜ የሚመጣውን የናዝሬቱ ኢየሱስን ጠበቅን። ከዚያስ? አገኘው፣ ከዚያስ? ከበርን!!! የጠበቅነው ማእበሉና ንፋሳቱ ሁሉ፣ የሚታዘዙለትን ጌታ ነዋ!!!!!
ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅጠናሁት፣ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኸቴንም ሰማኝ። ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፣ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፣ አረማመዴንም አጸና። አዲስ ዝማሬን ለአምላካችን ምስጋና በአፌ ጨመረ:: መዝ 40:1
---------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 9 ቀን ቀርቶታል
No comments:
Post a Comment