ዲቮሽን 302/07 ሓሙስ ፤ ሓምሌ 02/07
(በ ወንድም ጌታህን ሓለፎም )
ኢየሱስ
የደህንነት
አምላክ
!
“አምላካችንስ የደህንነት አምላክ ነው ከሞትም ማምለጥ ከእግዚአብሔር ነው!” መዝ (68፡20)
ለስው ልጆች በሙሉ ደህንነት፣ እረፍትን፣ ህይወትን የሚያስብና የሚሰጥ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ማንም የለም፡፡ ከዘላለም ሞት ማምለጥም የሚቻለው ሁሉን በሚችል ጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ አዎ አምላካችን የደህንነት አምላክ ነው፣ ከሞትም ማምለጥ የሚቻለው ሞትን ድል ባደረገው በእግዚአብሔር ብቻ ነው!
አንድ ወቅት አንድ የባእድ አምልኮ የሚያመልክ ሰው ከሚያጥንለትና ከሚሰዋለት ክፉ መንፈስ ያልጠበቀውና ይሆናል ብሎ ያልገመተው ትእዛዝ መጣበት፡፡ እሱም እንዲህ የሚል ነበር “ልጅህን ሰዋልኝ!”
ይህ ባእድ አምላኪ ግለሰብ ለወትሮው ክፉው መንፈሱ አድርግና አምጣ ያለውን ሁሉ ሽቅብ ወጥቶ ቁልቁል ወርዶ ከየትም ብሎ ያመጣና ይገብርለት፣ ትእዛዙንም ይፈጽም ነበር፡፡ ጥቁር ወይፈን፣ ወሰራ ዶሮ፣ ግንባረ ዶቃ በግ፣ ካገኘ በገንዘቡ ቢያጣ ተበድሮና ተለቅቶ አቅርብ የተባለውን ግብር ይገብር ነበር፡፡ እንዲህም እያደረገ ብዙ ዘመን አሳለፈ፡፡ ክፉው መንፈስ በስተመጨረሻው አምጣ ያለው ግን የጉልበቱን ፍሬ የገዛ ልጁን ነበርና ተጨነቀ፣ ደነገጠ፣ ፈራ፣ ሰማይና ምድሩም ዞረበት፡፡
የአብራኩን ክፋይ ልጁን እንዴት ብሎ ደሟን ያፍስስ? እንዴት አይኑ እያየ እንደ በጎች፣ እንደ ፍየሎች ደም የልጁን ደም ያፍሰስ? ግራ ተጋባ፤ የት ይድረስ? የት ይደበቅ? ክፉውን መንፈስ አልታዘዝም ቢል ደግሞ እንደማይራራለት እንደማያዝንለት ያውቃል፡፡ ግብር ሲያጓድል፤ አምጣ የተባለው ሲዘገይ መንፈሱ እንዴት እንደሚቀጣውና እንዴት እንደሚያስጨንቀው ያውቃል፡፡
በመጨረሻም ይህንን ቀንበር መሸከም አልቻለምና እንደ መፍትሄና እንደ እረፍት ሆኖ ያገኘው ነገር ቢኖር እራሱን ማጥፋት ነበረ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጭንቀት ለመገላገልም አማራጭና መተኪያ የሌላትን ህይወቱን በገዛ እጁ አጠፋት፡፡ “አይኔ እያየ ልጄን ከምገብር፤ ይህንን መከራ ይህንን ግፍ ከምሸከም እራሴ ላይ እርምጃ ብወስድ ይሻላል” ብሎ ወሰነ፡፡
ወገኖቼ ይህን አይነትና ሌሎችንም ይህን የሚመስሉ እውነተኛና አሳዛኝ ታሪኮችን ሰምተን ሊሆን ይችላል፡፡ አዎ ጌታም በዮሐ 10፡10 “ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጅ ስለሌላ አይመጣም እኔ ህይወት እንዲሆንላችው እንዲበዛላችውም መጣሁ” እንዳለ፤ ከሰይጣን ምን ደህንነት ይገኛል? ህይወትን ከሚሰጥ ከጌታ ከኢየሱስ በቀርስ እረፍትና መጽናናት፤ ደህንነትስ ከየት ይመጣል? ሌባው ከማረድ ከመግደል በቀር ለሰው ልጆች ደህንነትን ሊሰጥ እንዴት ይችላል?
ወገኖቼ እውነት ነው “አምላካችን የደህንነት አምላክ ነው” ይህን አምላክ የሚሰጠውን የደህንነት ዋስትና በውነት የጌታን ጣእም ከሚይውውቅ በስተቀር ማን ሊረዳው ይችላል? ከሞትስ ማምለጥ የሚቻለው፤ ሞትን ድል ካደረገው ከአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በስተቀር በሌላ በማን ሊሆን ይቻላል? አዎ ሌሎችን ከሞት ለመታደግ የሞት ስልጣን መሻር አለበት፤ የሞት ጉልበት የሞት ሃይል መዋረድ አለበት፡፡ ይህንን ያደረገ ደግሞ ብቸኛው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
አዎ ህይወትን፤ እረፍት እና ደህንነትን መስጠት በተመለከተ፤ ሞትን ድል ካደረገ በስተቀር ከሌላው አይታሰብም፡፡ ጻድቃን ህይወትን ደህንነትን ዘላለማዊነትን ሊሰጡ አይችሉም ምክኒያቱም ሞት በተባለው ባላንጣ ተሸንፈዋልና፤ መላእክቶችም ቢሆኑ ለሰው ልጅ ደህንነትንና ዘላለማዊነትን ሊሰጡ አይችሉም ፍጡራን ናቸውና የእግዚአብሔር እርዳታ ያስፈልጋቸዋልና ለአንድ ሰው ሚሊዮን ብር ሊሰጥ ችሎታ ያለው ቢሊዮኔር ውይም ሚልዮኔር በስተቀር የኔ ቢጤና የናንተ ቢጤ ከየት ያመጣዋል?
ዳዊት ለነፍሱ እንዳስረገጠላት እውነቱን እንዳስገነዘባት እኔና እናንተም የጸና እውቀት ሊኖረን ይገባል! ካንዱ ብቸኛ ጌታ በስተቀር ደህንነትን ሊሰጥ የሚችል ማንም የለም፡፡ ከሞትም ማምለጠ የሚቻለው የሁል የበላይ በሆነው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ዘንድሮ እንደሆነ ድብቅ አጀንዳው የተሰወረው ሁሉ ማንነቱ ገሃድ እየወጣ ነው፡፡ ዝንብ እንኳን ቢሆን አይገድሉም እየተባሉ በጨዋነታቸውና በመልካም ስነ ምግባራቸው የሚወደሱት የቡድሃ ተከታዮች እንኳ ከነሱ እምነት ውጭ ያሉትን የንጹሃንን ደም በግፍ እያፈሰሱ እንደሆነ በበርማ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡ ሁሉ አማልክት መግደል እንጅ ማዳን አይችሉም፡፡ የሚገድሉ አማልክቶች ደግሞ ምንጫቸው ሰይጣን ነው፡፡ ስለዚህ እኔና እናንተ ህይወትን ከሚሰጠው፤ ከሞት ከሚያስመልጠው ከዚህ እውነተኛ ጌታ ጋር መጣበቅ ያስፈልገናል፡፡ አዎን “አምላካችንስ የደህንነት አምላክ ነው ከሞትም ማምለጥ ከእግዚአብሔር ነው!”
No comments:
Post a Comment