Friday, July 10, 2015

ቃሉ – ይገለጥ!



ዲቮሽን 303/07 አርብ፥ ሐምሌ 3/07 /
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ቃሉይገለጥ!

ዕዝራም በሕዝቡ ሁሉ ላይ ከፍ ብሎ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ መጽሐፉን ገለጠ፤ በገለጠውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ ... ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ (ነህምያ 8 : 5-6)

ወገኖች ሆይ፥ ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሰው ከመላው ሕዝብ መካከል የሙሴ ሕግ መጽሐፍ ይገኝ የነበረው በጸሐፊው በዕዝራ እጅ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰፊው የእስራኤል ሕዝብ ለመጽሐፉ ባይተዋር፥ ለሕጉ እንግዳ ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ የዘቀጠ ነበር፡፡ ይህም መንፈሳዊ ዝቅጠት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስረት ለማስከተል ቻለ!

ወገኖች ሆይ፥ ዕዝራ ከነህምያ በፊት 15 ዓመት ቀድሞ ወደ እስራኤል ምድር የተመለሰ ቢሆንም፥ ከነበረው የውጭና የውስጥ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች የተነሳ በእጁ ከሚገኘው መጽሐፍ ሕዝቡን ማስተማር አልቻለም፡፡ ከዚህም የተነሳ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ከአሕዛብ ልማዶች ጋር ለመቀላቀልና ሊበረዝም ቻለ፡፡

ታውቃላችሁ፥ መጽሐፉ የሚገኘው በፕሮፌሽናል ጸሐፊው በዕዝራ እጅ ብቻ ነውና፥ ተራው የእስራኤል ሕዝብ ከመጽሐፉ እውቀት ሳይጠቀም ቀረ!

ታውቃላችሁ፥ ቃሉ በፕሮፌሽናሎች እጅ ብቻ ሲሆን አደጋው ብዙ ነው! ፕሮፌሽናሉ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ እንደነበር የተጻፈ ቢሆንም (ዕዝራ 7:10) ይህ ዓይነት ዝግጅት አስፈላጊ ቢሆንም፥ ነገር ግን ተግዳሮቶችን ጥሶ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ማስተማር ካልቻሉ በዕዝራ ዘመን በሕዝቡ የደረሰው መንፈሳዊ ውድቀት መምጣቱ አይቀርም!

ወገኖች ሆይ፥ ዛሬም በቤተክርስቲያን የሐይማኖታዊ ፕሮፌሽናሊዝም ችግር በየቤተእምነቱ ብቅ ብቅ እያለ ነው! በተለያዩ ተቋማት ቃሉን የተማሩ፥ ስነ አፈታቱን፥ ስነ አስባበኩን፥ ስነ ታሪኩንና ስነ ዐውድ ወጎቹን "አውቀናል" የሚሉ፥ ነገር ግን ባወቁበት ዕውቀት ወደ ሕዝቡ ወርደው ለማገልገልና "ቃሉን ለመግለጥ" አቅም የሌላቸው መንፈሰ ድኩማን በየቦታው ሞልተዋል!

ወገኖች ሆይ፥ ዲፕሎማና ዲግሪ ማስተርስ ዶክትሬቱን፥ በጫንቃቸውና በጭንቅላታቸው ላይ ደራርበው የጫኑ፥ ነገር ግን ሕዝብን ለማስተማር መንፈሳዊ አቅም ጉድለት ያለባቸው፥ መንፈሰ ድኩማን በየስፍራው አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፥ አሁን ለምንገኝ ለዚህ ዘመን ሰዎች ቃሉን ገልጦ ከማስተማር ይልቅ፥ በተቀባ ስብከት የመንፈስ ቅዱስን ብርሃን በሥልጣን ከማብራትና የቃሉን መልዕክት ከመናገር ይልቅ፥ የጥንት ዘመን ልማድ - የድሮ ወግ ባህል እንዳይነካና እንዳይሸራረፍ ጥበቃ የቆሙ፥ የታሪክ ጠበቆች፥ የድሮ ዘበኞች፥ የኛ "ፕሮፌሽናሎች" በየቦታው ሞልተዋል!

ታውቃላችሁ፥ በብዙ ቦታዎች ላይ ሲታይ፥ በርካታ ሐይማኖታዊ ፕሮፌሽናሎቻችን ያነበቡትን ከመደጋገም በቀር፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ከመጻሕፍት ገጾች ከማጣቀስ በቀር፥ ቃሉን ገልጠው ለማስተማር አቅም የሌላቸው አቅመ ደካሞችና መንፈስ ድኩማን ናቸው!

ወገኖች ሆይ፥ ታውቃላችሁ፥ ታሪኩን ባናውቀው፥ ዐውዱንም ባናውቀው፥ ቋንቋ ሰዋሰዎውን መርምረን ባንደርሰው፥ ነገር ግን የተገለጠልንን የእግዚአብሔር ቃል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ገላልጠን ብንሰብከው፥ ሕዝባችን ለጌታ ወድቆ እንዲሰግድ፥ ከተሳሳተበት መመለስ እንዲችል፥ ወደ ንስሐና ወደ ነፍስ ፍስሐ፥ እንዲሁም ወደ ፈውስና ወደ ታላቅ ሥራ ሊመጣ ይችላል!

No comments:

Post a Comment