Tuesday, July 7, 2015

ክርስቶስ ሲሰበክ– ደስ ሊለን ይገባል!



ዲቮሽን 300/07 ማክሰኞ፥ ሰኔ 30/07 /
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ክርስቶስ ሲሰበክ– ደስ ሊለን ይገባል!

አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል… ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥  ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል(ፊልጵ 1፡15-18)።

ወገኖች ሆይ፣ ክርስትና ክርስቶስን መምሰል፣ የክርስቶስን ሕይወት መስበክ ነው፡፡ ክርስቶስን መስበክ ስንል ደግሞ ከድንግል እናቱ ከቅድስት ማርያም ሥጋ ነስቶ መወለዱን፣ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት በቃልና በሥራ መስበኩን፣ በመስቀል ላይ ስለኃጢአተኞች መሞቱን፣ መቀበሩን፣ በክብር ከሞት መነሳቱንና ወደ አባቱ ማረጉን፣ በመጨረሻውም ቀን በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ተመልሶ ምጽአቱን … ለሰዎች መናገር ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ይህ ስብከት በየቦታው እየተሰበከ ነው፡፡ በየፕሮቴስታንቱ፣ በየኦርቶዶክሱ፣ በየካቶሊኩ፣ በቁንጽል ቢሆን በየመስጊዱ እንኳ ስለ ክርስቶስ ይሰበካል፡፡ ይሁንና፣ ሰባኪዎቹ ስለ ክርስቶስ ሲናገሩ የተለያዩ ምክንያት ይዘው ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዶች ስለ ክርስቶስ ሲናገሩ ወይም ሲያወሩ የምንሰማው ከቅንአትና ከክርክር መንፈስ ተነስተው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ዓላማ፣ ለገዛ ሐይማኖታቸው ጥቅም ሲሉ፣ በቅን አሳብ ሳይሆን ቅንነት በጎደለው መንገድ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። እነዚህ ሰዎች በእውነተኛ የክርስቶስ መስካሪዎችና ተከታዮች ላይ መከራ ለማምጣት ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ታውቃላችሁ፣ በዚህም መንገድ ቢሆን ሰዎች ይድናሉ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አንዳንዶች ደግሞ፣ ከቅን አሳብ እና ከፍቅር ተነስተው ክርስቶስን ይሰብካሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ታላቁ ተልዕኮ አምነው ተቀብለው፣ የሰው ልጆች ሁሉ እውነቱን እንዲያውቁ፣ ድነት እንዲያገኙ ወንጌል ይሰብካሉ፡፡ በዚህም ብዙዎች ጌታን ያገኛሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ በቴሌቪዥን ይሁን በመጽሔት፣ በፌስትቫል ይሁን ኮንፍራንስ፣ በአዳዲስ አጥቢያም ይሁን በዕድሜ ጠገቦቹ፣ ለገዛ ጥቅምም ይሁን፣ በማናቸውም ምክንያት ክርስቶስ ሲሰበክ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ይህንን ክርስቶስ ሙስሊሙ ቢሰብከው፣ ኦርቶዶክስ ቢሰብከው፣ ካቶሊክ ቢሰብከው፣ ባፕቲስቱ ቢሰብከው፣ ሉተራኑ ቢሰብከው፣ ሜኖናይት ቢሰብከው፣ ሜቶዲስት ቢሰብከው፣ ናዛሪን ቢሰብከው ማናቸውም ቢሰብከው – ደስ ሊለን ይገባል!

ታውቃላችሁ፣ ማንም ሰበከው ማንም የክርስቶስ ስም ሲሰበክ ስሙ ኃይል አለውና – ደስ ሊለን ይገባል! ከብዙ ሐይማኖታዊ ቅንአትና ክርክር ልማድና ወጎች መሀል፣ ከብዙ ፍልስፍናዊ ቅዠቶችና መላምቶች መሀል፣ ከብዙ ፖለቲካዊ ዲስኩሮችና ፕሮፓጋንዳዎች መሀል፣ ጥቂት የተነገረ የክርስቶስ ስም ኃይል አለውና – በዚህ ደስ ሊለን ይገባል!

-------------------

ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ላይ ይጠናቀቃል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ዲቮሽኑን የሚከታተሉ 15000 በላይ ሰዎች ከመላው ዓለም ማፍራት ተችሏል፡፡ ዲቮሽኖቹ፣ ሰዎች ወደጌታ እንዲመጡ፣ በርካታዎቹም ከውድቀታቸው እንዲነሱና ከስብራታቸው እንዲጠገኑ፣ በርካታዎቹም እንዲታነጹ … ምክንያት ሆነዋል፡፡ ክብሩን ሁሉ ጌታ ይውሰድ፡፡

እነዚህን ዲቮሽኖች ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ ላይ ለማሳተምና መስከረም 2008 ዓ.ም. ላይ ለአንባቢዎች ለማድረስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሀገራችን ታሪክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና አንድም ቀን ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ ለአንባቢዎች ይቀርብ የነበረውንና በርካታ ነጻ አስተያየቶች ሲሰጡበትና በርካታ ቅዱሳን ሲጸልዩለት ቆይተዋል፡፡

ይህን ታሪካዊ መጽሐፍ፣ የማሳተሚያ ወጭ በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ፣ ወይም ገፆች በመግዛት በመጽሐፉ ላይ የድርጅታችሁንና የአገልግሎታችሁን ዓላማዎች ለአንባቢያን ማስተዋወቅ የምትፈልጉ፣ ምርቶቻችሁንና ማናቸውንም አገልግሎታችሁን በማስታወቂያ ማስተላለፍ የምትፈልጉ በሀገር ውስጥና ውጭ የምትገኙ ወገኖች ሁሉ ባሉን ውስን ገጾች ውስጥ አስቀድሞ በመያዝ ራዕዩን መደገፍ ትችላላችሁ፡፡ ለተጨማሪ መረጃ፣ በሞባይል 911-678-158 መደወል ይቻላል፡፡

ዓመቱን ሙሉ አብራችሁን ለነበራችሁ ወገኖች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በዲቮሽኑ መቆም ልባችሁ ለሚያዝንብን ወገኖች ደግሞ ከፍ ያለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡ ፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ

No comments:

Post a Comment