Sunday, July 5, 2015

ማንን ያገኝ ይሆን!

ዲቮሽን 297/07፥ ቅዳሜ፥ ሰኔ 27/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ማንን ያገኝ ይሆን!

የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ (ኢሳ 6:8)::

በትናንትናው ዲቮሽን ላይ፥ ንጉሡ ዖዝያን ከፍ ከፍ ካለ በኋላ ልቡ እንደታበየና በእግዚአብሔርም ላይ ስንፍና እንደሠራ፥ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በለምጽ እንደቀሰፈው፥ እስከሚሞትም ድረስ በኳራንታይን (የተገለለ ቤት) ውስጥ ተዘግቶበት የውርደት ሞት መሞቱን ተመልክተናል፡፡

ዛሬ ደግሞ፥ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ለነቢዩ ኢሳይያስ ሲገለጥለትና "የምልከው ሰው እፈልጋለሁ" ሲል እንሰማለን ።

ወገኖች ሆይ፥ የእግዚአብሔር ነገር፥ የቤቱ አሠራር ይገርማል! አንዱን ያነሳል ሌላኛውን ይጥላል! ትዕቢተኛውን አዋርዶ የተዋረደውን ያከብራል! የአንዱን ሹመት ሽሮ ሌላኛውን ይሾማል!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታ ሁልጊዜ ሰው እንደፈለገ ነው! እንደ ፈቃዱና እንደ ልቡ ሐሳብ ወጥቶ የሚገባ ሰው እንደፈለገ ነው! የእግዚአብሔር አፍ ሆኖ፥ መልዕክተኛ ሊሆንየተዘጋጀ ሰው እንደገለገ ነው!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታ ሰው ሲፈልግ በሕልምና ራዕይ በማናቸውም መንገድ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊገለጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወገኖች፥ ጌታ ሰው ሲፈልግ "እሺ" የሚልና "አለሁልህ" ባይ ሰው በጣም ይፈለጋል! ለተገለጠ ራዕይ እሺ የሚልና የተዘጋጀ ሰው ሊቀባ ይችላል፡፡

ወገኖች ሆይ፥ የሠራዊት ጌታ ነቢይ እንደፈለገ ነው! የመንግሥቱን ሥርዓት ለሰው ልጆች ሁሉ በድፍረት ሊናገር በእውነት የቆረጠ - በነፍስ በሥጋና በመንፈሱ ሁሉ የተወራረደ እንደፈለገ ነው! ዛሬ ጌታ መጥቶ፥ የሚቀባውንና የሚልከውን ሰው ሲፈልግ ብናገኝ፥ "እነሆኝ አምላኬ፥ እኔ አለሁልህ፥ እኔን ቀባኝና፥ እኔን ላከኝ" ብለን እንመልስ ይሆን? ጥሪው ዛሬ ቢሆን፥ ጥሪው አሁን ቢሆን - ጌታ እሺ የሚለውን ማንን ያገኝ ይሆን?

No comments:

Post a Comment