ዲቮሽን 296/07፥ አርብ፥ ሰኔ 26/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ከዖዝያን ውድቀት – እንማር!
ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ
ጊዜ የ16 ዓመት ጕልማሳ ነበረ…እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት…፥
እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ … ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ … በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ…ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥
በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ ፈጥነውም አባርረሩት፥ እርሱም ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ…ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቈርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር (2ዜና 26)
ወገኖች ሆይ፣ ንጉሡ ዖዝያን እንደ ንጉሡ
ሰለሞን ሁሉ፣ ዕድሜው ለንጉሥነት ሳይደርስ ገና የ16 ዓመት ጕልማሳ ሳለ ነበር በታላቁ ሕዝብ በእስራኤል ላይ እግዚአብሔር ያነገሠው፡፡
ዖዝያን በዕድሜው ገና ወጣት ስለነበረና ስለ መንግሥት አመራርም ግራና ቀኙን ለይቶ የማያውቅ ስለነበረ፣ እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ
ልቡን በእግዚአብሔርን ላይ አደረገ፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት፡፡ ዝናውም እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ፡፡ የንጉሡ ዖዝያን ዝነኝነትና በመንግሥቱም ዘመን በመላ ሀገሪቱ ወርዶ
የነበረው ምድራዊ ብልጽግና ከዳዊትና ከሰለሞን መንግሥት ቀጥሎ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነበር፡፡
ወገኖች ሆይ፣ የኛ ማንነትና ልምድ፣ ዕድሜና ጾታችን፣ ዕውቀት ችሎታችን ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ ችግር ሆኖ አያውቅም፡፡ በእግዚአብሔር
የታመነ እምነቱንም እግዚአብሔርን ያደረገ
ሰው፣ እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልቡን በእግዚአብሔር ላይ ያደረገ ሰው፣ ሰማያዊና ምድራዊ ባርኮቶች ሁሉ መቀበል ይችላል፡፡ ከኢያሱ
ወልደነዌ፣ ከንጉሡ ሰለሞን፣ ከንጉሡ ዖዝያን ከሌሎችም መሪዎች የምናየው ይህንን እውነት ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ የስኬታችን ቁልፍ የበረከታችን ምንጭ ተሸሽጎ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ ንጉሡ ዖዝያን ይኼን በማወቁ ወደ
ወደበረከት ማማ ወደ ዝነኝነት ከፍታ ጥሶና ጠርምሶ እንዲወጣ ሆነ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ንጉሡ ዖዝያን
ልክ እንደ ንጉሡ ሰለሞን ገና በልጅነት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ መገደፍ የሚያስገኘውን ስኬት፣ በእግዚአብሔር ፊት ራስን በማዋረድ
የሚገኘውን ክብር ለመርሳት ጀመረ፡፡ በበረታ
ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ! በዚህም ሳያቆም አምላኩን እግዚአብሔርን በደለ – ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ፣ በዚህም ስንፍናው በለምጽ ተቀሰፈ!
ወገኖች ሆይ፣ ትዕቢት ወድቀትን
ታመጣለችና፣ ዖዝያን ስለታበየ ከሥልጣን ወረደ! በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በትዕቢት ለመታየት ሲፈልግ፣ ከሕዝብ
አደባባይ እስከ ገዛ ቤቱ ለመነቀል ቻለ፡፡ ያለዕድሜውና ያለችሎታውም ያከበረውንና የባረከውን ጌታ ዘንግቷልና፣ እስከሚሞትና እስከሚቀበር
ድረስ በተገለለና በተዋረደ ቤት ለመኖር ተገደደ!
ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር
ሰው ሺህ ጊዜ ሺህ ብርታት ቢያገኝ፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ስኬት ቢኖረው ያልተላከበት ሊገባ፣ ያልተፈቀደለትን ሊነካ አይገባም! ያልተላኩበት
መግባት ያልተፈቀደውን መንካት የሚያስከትለውን አደጋ መርሳት አይገባም!
No comments:
Post a Comment