Tuesday, July 14, 2015

እንበዛለን፣ እንጸናለን!!!!



ዲቮሽን 308/07 ረቡዕ ሐምሌ 8/07 /
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

እንበዛለን፣ እንጸናለን!!!!

ነገር ግን እንዳስጨነቋቸው መጠን እንዲሁ በዙ፣ እጅግም ጸኑ። ዘጸአት 1 12

ድካም ሲያስጨንቀን፣ ስንፍና ሲከበን፣ አለማመን ሲያይልብን፣ መኖር ሲታክተን፣ . . . ጠላታችንም ይሕን አውቆ ቀንበሩን ሊያሸክመን ሲታትር፣ ጠዋትና ማታ ወደ እግዚአብሔር ማልቀሳችን አይቀሬ ይሆናል።

ሐጢያት አየሩን ተቆጣጥሮት፣ እኛም የሐጢያት ተሳታፊዎች ስንሆን፣ ጭንቀታችን ወደር አይኖረውም።ወየው! ዛሬ ጠፋሁ፣ ዛሬ አለቀልኝብለን ከዓመጻ ሕብረት መለየት አቅቶን ስንፍጨረጨር፣ አልፎ ተርፎም በጠላት ወጥመድ ውስጥ ስንገባ፣ ሐዘንና ስጋት፣ መሳቀቅና ውርደት ሲደርስብን፣ ምንም ፍሬ የማናፈራ፣ እግዚአብሔርንም ያሰደብን መስሎን፣ከእንግዲህስ ጌታ ነፍሴን ቢቀበላት?” የምንልበት ጊዜ በርካታ ነው።

ጌታ ሆይ፣ እጅህ ወዴት አለች? ያንተም ስም መሰደቡ ነው፣ ስንል፣ ለእግዚአብሔር ቤት የለፋነው ነገር ሁሉ ፍሬ ያላፈራ ሲመስለን፣ ጸሎታችን ሁሉ ወደ ሰማይ ያልደረሰ ሲመስለን፣ አቤት! ያን ጊዜ የእኛ ለቅሶ፣ የጠላታችን ደግሞ ደስታ ልዩ ነው።

ግን ወገኖቼ፣ እያንዳንዷ ዘለላ እንባችን፣ እያንዳንዱ የጠላታችን ስላቅና ደስታ በኢየሱስ መዝገብ ውስጥ ተይዛ፣ እንዴት እና መቼ እንደሆነ እንኳን ባላወቅነው ሁኔታ፣ አምላካችን ለበቀል ይመጣል።

ይጠፋሉ ስንባል፣ በእርግጥ እንበዛለን፣ ጌታን ትተው ወደዓለም ይገባሉ ሲባል በእጥፍ ድርብ ቅባት እንጸናለን። እመኑኝ፣ እግዚአብሔር ይመጣል። ያውም፣ ምድርን እያንቀጠቀጠና እያናወጠ፣ የተራሮችን መሠረቶች እያነቃነቀና እጅግ እየተቆጣ፣ ጌታ ይደርስልናል። ከቁጣው ጢስ እየወጣ፣ ከፊቱም የሚበላ እሳት እየነደደ፣ ፍላጻውን እየላከ፣ ያስጨነቁንን እየበተነ በእርግጥ ይመጣል። ከብርቱዎች ጠላቶቻችን፣ ከሚጠሉንም ሁሉ ያድነናል። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፣ ተብሎ እንደተጻፈ፣ አንድ ብቻውን ሆኖ፣ ወደ ሰፊ ስፍራ ያወጣናል።

እመኑኝ፣ ገና እንበዛለን፣ ገና እንጸናለን፣ ገና እናፈራለን።

አባት ሆይ፣ ግሩም ስለሆነው ቃልህ አመሰግንሀለሁ። ስለእያንዳንዳችን ተሟግተህ፣ አሸንፈህ፣ አሸናፊ ስለምታደርገን፣ ውድዬ፣ ክብሩ ሁሉ ላንተ ብቻ ይሁን። ሰምተህኛልና ተባረክ።
------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 / ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 58 ቀን ቀርቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment