Wednesday, July 1, 2015

ግብረሰዶማዊነት – የማይረባ አዕምሮ ውጤት #2



ዲቮሽ 294/07 ረቡዕ፥ ሰኔ 24/07 /
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ግብረሰዶማዊነት የማይረባ አዕምሮ ውጤት #2


ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ጸያፍ ነገር ነውና። እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም የተጠላ ነገር ነውና። በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ (ዘጸ 18፡22-24)።

ብዙ ጊዜ ሰዶምና ገሞራ በግብረሰዶማዊነታቸው ምክንያት እግዚአብሔር እንደቀጣቸውና ምድሪቱን እንዳጠፋ በአማኞች ዘንድም ሆነ በማያምኑት ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ወተትማ ማር ይፈስስባት ከነበረችው ከከነዓን ምድር የተነቀሉ ከነአናዊያን ለምን እንደተነቀሉ ሲሰበክ አብዝተን አንሰማም፡፡ ከነአናዊያን ከምድራቸው ከተነቀሉባቸው ምክንያቶች አንዱ የግብረሰዶማዊነት ኃጢአት ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የግብረሰዶማዊነት ኃጢአት ምድርን ሊያጠፋ እንደሚችልና በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎችን ከምድር ገጽ ሊያጠፋ እንደሚችል ከሰዶምና ገሞራ ሰዎች በተጨማሪ፣ የከነዓናዊያን ከከነዓን ምድር መጥፋት ማስረጃ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከነዓናዊያንን ከምድራቸው አጥፍቶ፣ በከነዓናዊያን ግብረሰዶማዊ እርኩሰት የቆሸሸችውን ምድር አጽድቶ የቃል ኪዳን ሕዝቡ ለሆነው ለእስራኤል ሰጠ፡፡ ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሔር ናትና ከነዓናዊያንን አጥፍቶ እስራኤላዊያንን ቢያስቀምጥበት እግዚአብሔርን የሚጠይቀውም ሆነ የሚከለክለው የለም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር እስራኤላዊያንን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ወደ ከነዓን ሲያስገባ ካስጠነቀቃቸው ነገሮች አንዱ ግብረሰዶማዊነት ነው፡፡ ከነዓናዊያን ወንዶች አንድ ወንድ ከሴት ጋር እንደሚተኛ ያህል፣ ወንድ ከወንድ ጋር የመተኛት ልማድ ነበራቸው፡፡ ወንዶች ከሴት እንሰሳ ጋር በመተኛት ጸያፍ ነገር ያደርጉ ነበር፡፡ ሴቶቹም ከወንድ እንስሳ ጋር በመተኛት ጸያፍ ነገር ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ከምድራቸው በመንቀል አሳደዳቸው፣ አጠፋቸውም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች ከጥንት ጀምሮ ወንዶች ከሴት እንስሳት ጋር እርኩሰት እንደሚፈጽሙ በሐሜት ደረጃ ሲወራ ይደመጣል፡፡ ድብቁ ባህላችን ብዙ ጉዶቻችንን ሸፍኖብን እንጂ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ወንድ ከወንድ ጋር ሴትም ከሴት ጋር የመርከሱ ወሬ በሐሜት ደረጃ ሲነገር ይሰማል፡፡ ስለሆነም ችግሩን የሩቅ፣ ወይም የሌሎች ችግር ብቻ አድርገን እያሰብን ከሆነ ተሳስተናል ማለት ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ለግብረሰዶማነት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ‹‹ተፈጥሮአዊ›› የሆነ የተመሳሳይ ጾታ መሳሳብ (homosexual orientation) ሊሆን ይችላል ሲባል እንሰማለን፡፡ እኔ በማናቸውም ምክንያት የዚህ አስተሳሰብ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ በእኔ አቋም፣ ግብረሰዶማነት ማለት ‹‹የማይገባውን ነገር እንዲያደርግ ተላልፎ የተሰጠ የማይረባ አእምሮ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነት አእምሮ የሚፈጠረው እግዚአብሔር ለሰዎች ሊታወቅ እየፈለገና እየቀረበ ሳለ፣ ነገር ግን ሰዎች እርሱን ለማወቅ ካለመውደዳቸውና ካለመፈለጋቸው የተነሣ የሚከሰት አደጋ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛቸው አድርገው ቢቀበሉና በመንፈስ ቅዱስ ቢጠመቁ ከዚህ እስራት ነጻ ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሆኖም፣ በአገልግሎት ዘመኔ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አልፎ አልፎ አጋጥመውኛል፡፡ ወንድ ሆነው ከሴት ድምጽ ጨምሮ የሴት ጠረን እንኳ የማይወዱ፣ ሴት ሆነው ከወንድ ድምጽ ጨምሮ የወንድ ጠረን የማይወዱ፣ አሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ባህላዊ ጫና ሆኖባቸው ትዳር ሊመሠርቱ ልጅም ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለሥጋ ፈቃዳቸው እርካታ የሚሰጣቸው ለተቃራኒ ጾታ የተፈጠረ ተፈጥሮአዊ አካል ሳይሆን ለቆሻሻ ማስወገጃነት በተፈጠረ አካል በኩል ሲገናኙ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ የወደቁ፣ ትዳራቸው የፈረሰ፣ ወይንም የረከሰ የማውቀው ጥቂት የማይባሉ ምስክርነቶች አሉ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ማንኛውም ጤናማ ሰው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ሲቀራረብ፣ ወይንም አካል ለአካል ሲነካካ እርስ በርስ በአካለ ሥጋ ለማገናኘት የሚገፋፋ ተፈጥሮአዊ የሆነ መሳሳብ አለ፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ መሳሳብ በማንኛውም መንፈሳዊ ሰው ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ መሳሳብ በውስጣችን ያለ ቢሆንም፣ ነገር ግን ራስን በመግዛት መንፈስና በጸሎት እንቆጣጠረዋለን፡፡ ይህ ራስን የመግዛት መንፈስና የጸሎት ሕይወት በውስጣችን እያደገ በሄደ መጠንም፣ ለዝሙት አደጋ ሊያጋልጡን የሚችሉ ነገሮችን ከአካባቢያችን የማስወገዱን ልማድም እናዳብራለን፡፡ በዚህ በዚህ መንገድ በተቃራኒ ጾታ ኃጢአት ከመውደቅ ራሳችንን እንከላከላለን፡፡

በተመሣሣይ ሁኔታ በማናቸውም ሁኔታ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የመሳሳብ (homosexual orientation) ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛቸው አድርገው እንዲቀበሉ፣ የተቀበሉና የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ካሉም፣ ቢጸለይላቸውና በመንፈስ ቅዱስ ቢጠመቁ ከዚህ አጋንንታዊ እስራት ነጻ ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ የክርስትና እምነታችንን በመድረክ ላይ ከሚወረወሩ የተዋቡና የተቀባቡ ቃላት ሳንወስን፣ በልዩ ልዩ አጋንንታዊ እስራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ነጻ ለማውጣትም ብንጠቀምበት መልካም ነው፡፡

ባደጉት ሀገሮች ከፍተኛ የሪቫይቫል ጉባኤዎች የሚያካሂዱና በኮንፍራንሶቻቸውም ላይ ታላላቅ ተአምራቶች የሚያደርጉ ግብረሰዶማዊያን መኖራቸው ደግሞ የዛሬዪቱን ቤተክርስቲያን ፈተና ከምንጊዜውም ይልቅ ከባድ አድርጎታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ባንድ በኩል እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ግብረሰዶማዊነት አጋንንታዊ ነው ብለን ፈርጀን፣ በዚህ እስራት ላይ ላሉት እንጸልይላቸው ስንል፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹የለም፣ ግብረሰዶማዊነት አጋንንታዊ አይደለም፣ እኛም የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› የሚሉ የሐይማኖት መሪዎችና ከፍተኛ እውቅና የተቸራቸው ግለሰቦች መነሳታቸው የዛሬውን ዘመን የከፋ ያደርገዋል፡፡

 ወገኖች ሆይ፣ ግብረሰዶማዊያን አለም አቀፍ የሪቫይቫል ጉባኤዎች በማዘጋጀትና ‹‹ድንቅና ተአምራት፣ ፈውስና አጋንንት ማውጣት›› ሲያደርጉ መመልከት፣ ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ ሆኖም፣ አጋንንት የተመረጡትን እንኳ እስኪያስት ድረስ የብርሃን መልዐክ መስሎ መገለጡ በቅዱስ ቃሉ የተነገረን ነውና ልንደነግጥ አይገባም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ችግሩ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ባደጉት ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የወንጌል አማኝ መጋቢዎችና ዓለማቀፍ ሰባኪዎች በግብረሰዶማዊ ኃጢአት ውስጥ የመኖራቸው እውነታ እየተጋለጠ ሲወጣ በየጊዜው የምሰማው ዜና ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ባደጉት ሀገሮች ታላላቅ ቤተእምነቶች ጭምር ግብረሰዶማዊያን በአብያተክርስቲያኖቻቸው እንዲጋቡ ፈቅደዋል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ስለዚህ ምን እናድርግ? ጌታ ለእኛም እንደ ሞተ፣ ለግብረሰዶማዊያንም ሞቶላቸዋልና ይህንን እንወቅ፡፡ ለዳኑ ሰዎች የምንሰጠውን የክርስቶስን ፍቅር ለእነርሱም ልንሰጥ ይገባል፡፡ ሰዎችን ወንጌልን በመስበክና ወደጌታ በማምጣት የምንጥረውን ያህል፣ ያመኑትን ደቀመዝሙር ማድረግና አማኞቻችን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ መጸለይ ይጠበቅብናል፡፡

ጥያቄ፣

(1) ባል ግብረሰዶማዊነቱን ደብቆ በቤተክርስቲያን ጋብቻ ቢመሠርትና ሚስቱን ከተፈጥሮ ሩካቤ ሥጋ ውጭ ለመገናኘት ቢፈልግ ሚስት ምን ማድረግ አለባት?

(2) በቤተክርስቲያን የመሠረተ ጋብቻ አንዱ የትዳር አባል ግብረሰዶማዊ ሆኖ ቢገኝ ቤተክርስቲያን ምን አይነት አቋም መውሰድ ይኖርባታል?

No comments:

Post a Comment