Tuesday, June 9, 2015

መንፈስ ቅዱስን - መሳደብ!

ዲቮሽን 272/07 ማክሰኞ፥ ሰኔ 2/07
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

መንፈስ ቅዱስን - መሳደብ!

እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም (ማቴ 1231)

ወገኖች ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ "እላችኋለሁ" የሚለው ወይም "እውነት እውነት እላችኋለሁ" በማለት ንግግር የሚጀምረው፥ ቀጥሎ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ሰዎች ሰምተው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያደርጉ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ማለት መንፈስ ቅዱስ የፈጸመውን የድኅነት ሥራና ድንቅና ተአምራት ለሰይጣን መስጠት ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ማለት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለድሆች ወንጌል ሲሰበክ፥ ለታሰሩት መፈታት ሲሆን፥ ለእውሮች ማየት ሲሆን፥ የተጠቁት ነጻ ሲወጡ፥ የተወደደችው የጌታ አመት ሲሰበክ - ይኼ ሁሉ ሥራ ከአጋንንት ነው ማለት፥ ይኼን ሁሉ ነገር ከሰይጣን መፈረጅ ነው!

ወገኖች ሆይ፥ ክርስትና ሲያረጅ ሐይማኖት ይሆናል፡፡ ክርስትና ሲያረጅ የአምልኮን መልክ ይዞ ኃይሉን ግን ይክዳል! ክርስትና ሲያረጅ የወደቀን ማንሳት፥ የጠፋን መመለስ፥ የታመመን ማዳን፥ የታሰረን መፍታት፥ አጋንንትን ማውጣት፥ ድንቅና ተአምራት ተረት ተረት ይሆናል! ክርስትና ሲያረጅ ወንጌልን በመስበክ ሰዎችን ለማዳን አቀበት ይሆናል፡፡

የክርስትና ማርጀት ሐይማኖተኝነቱ፥ የክርስትና ማርጀት ልዩ መገለጫው፥ ዋና ምልክቱ መንፈስ ቅዱስን መስደብ፥ በእርሱም ላይ ክፉ ቃል መናገር ይሆናል፡፡ የክርስትና ማርጀት ሐይማኖተኝነቱ፥ የክርስትና ማርጀት ልዩ መገለጫው፥ ዋና ምልክቱ በክርስቶስ ኢየሱስ በከበረው ስሙ የሚገኘውን ኃይል እውቅና ከልክሎ፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለተሰራው ሥራ እውቅና ከልክሎ መቃወም መሳደብ ቃል መናገር ይሆናል፡፡

ወገኖች ሆይ፥ "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም(.32)"


ወገኖች ሆይ፥ ሰዎች በሰዎች ላይ ስለሰሩት ኃጢአት፥ ሰዎች በሰዎች ላይ ስለሰሩት ክፋት ሰዎች በሰዎች ላይ ስለተናገሩት ቃላት ምሕረትና ስርየት ከጌታ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ስለተናገሩት ቃላት፥ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ስለሰሩት ኃጢአት በምድር ላይ ቢሆን ወንይም በሚመጣው ዓለም ስርየትና ይቅርታ ምሕረትና ሕይወት የማይታሰብና የማይገኝ ይሆናል! ስለሆነም መንፈስ ቅዱስን ከመሳደብ አንደበታችን ይጠንቀቅ! በመንፈስ ቅዱስ ላይ ቃልን ከመናገር ምላሳችን ይቆጠብ!

No comments:

Post a Comment