Wednesday, June 10, 2015

ይቀናልሃል – ይከናወንልሃልም!



ዲቮሽን 273/07 ረቡዕ፥ ሰኔ 3/07
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ይቀናልሃል – ይከናወንልሃልም!

የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም (ኢያሱ 18)

ጆሮ ያለው ይስማ፣ ልብ ያለው ልብ ይበል!

ሰማያዊ ባርኮቶችና ምድራዊ ባርኮቶች ሁሉ የሚቀዱበት ምንጭ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የሥጋና የነፍስ የመንፈስ ባርኮቶች፣ የድልና ስኬት የብልጥግናና ሀብት፣ የጥርመሣ በሮች፣ የዕውቀትና ጥበብ፣ የኃይል የማስተዋል፣ የግርማና ሞገስ፣ የከፍታና ዕድገት የማናቸውም ነገር መነሻ መድረሻው፣ ምንጩ ውቅያኖሱ እግዚአብሔር ራሱ፣ የእግዚአብሔርም ቃል ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ የእርስዎ አጠቃላይ ሁኔታ የሚወሰነው ሰዎች እንደሚያዩት፣ ሁኔታው እንደሚነግረዎትም ሆነ እርስዎ ራስዎትን በሚመዝኑበት ሳይሆን፣ የእርስዎ ዕጣ ፈንታ ሐሴትና ደስታ ያለው ሁሉን በሚችለው በእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ ትንፋሽዎንና መንገድዎን በእጁ የያዘ ጌታ፣ ከእርስዎ ጋር ከሆነ ዙሪያዎትን የሚከብብ አስፈሪ ነገር ባይጠፋም በፊትዎ የሚቆም ምንም ኃይል የለም! እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ካለ የሚንጫጫ ባይጠፋም የሚቃወምዎት የለም!

ወዳጄ ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በተጣበቁ መጠን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በጠበቁ መጠን፣ ቃሉን ጠዋትና ማታ ባሰላሰሉ መጠን፣ በሚሄዱበት ሁሉ አምላክዎ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር መሆኑን ይህንን ይወቁ፣ ይህን ያሰላስሉ!  

ወዳጄ ሆይ፣ በሚሄዱበት ሁሉ አምላክዎ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ከሆነ በሚሄዱበት ሁሉ እንዲቀናልዎ እንዲከናወንልዎም ጠንቅቀው ይወቁ! በሚሄዱበት ሁሉ አምላክዎ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር መሆኑን ጠንቅቀው ካወቁ፣ እንግዲያውስ መፍራትና መስጋት መደንገጥ አቁመው የድል የጥርመሣ የምስጋና ዜማ ማብሰር ይጀምሩ!

‹‹በውሃ ላይ ሄዶ አሳይቶኛል – አሳይቶኛል
ታዲያ እኔ እንዳልሄድ ምን ያስፈራኛል – ምን ያስፈራኛል፣
በውሃ ላይ መሄድ እርሱ ከቻለ – እርሱ ከቻለ፣
በራሱ ተማምና አንተም ና ካለ – አንችም ነዪ ካለ፣
አልፈራም እኔ አልፈራም – አልፈራም እኔ አልፈራም!››

No comments:

Post a Comment