Sunday, June 7, 2015

አልለቅህም!!!!!!!

ዲቮሽን 270/07 ግንቦት 29/07
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አልለቅህም!!!!!!!

ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰው ጋር ታግለህ አሸንፈሀልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጅ ያዕቆብ አይባልም(ዘፍ 32 28)

በክርስትና መንገድ ላይ፣ አርአያ የምናደርጋቸው የእምነት አባቶች በሙሉ ጨቅጫቆች ናቸው። በትጋት ከእግዚአብሔር ጋር የሚጨቃጨቁ፣ የሚለምኑ የሚታገሉ፣ ካንተ ወደ ማን እንሔዳለን? የሚሉ ሁሉ የተስፋ ቃላቸውን በእጃቸው አስገብተዋል። አንድ አማኝ፣ የህይወቱ መርህ ሊያደርግ የሚገባው እግዚአብሄርን ብቻ ተስፋ ማድረግ ነው። እግዚአብሄር ደግሞ፣ አማኞች ሁሉ ፈጽመው በእሱ እንዲደገፉ ይፈልጋል።

የአማኝ የእምነት ትጋት በፍሬው ይታያል። እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እለት እለት ለማወቅ ይጥራል፣ እንከን የሆነበትን ነገር፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠፋው በማመን ፈቃደኛ ሆኖ እጅ መስጠት ይኖርበታል። ያልቻለውን ነገር ለእግዚአብሄር አደራ እየሰጠ በማንኛውም እንቅስቃሴው ውስጥ ሁሉጊዜ እራሱን እየመረመረ፣ እግዚአብሄርን ደጅ መጥናትና፣ ካልባረክኸኝ አልለቅህም፣ ካላዳንከኝ አልለቅህም፣ ካልፈወስከኝ አልለቅህም፣ ይቅር ካላልከኝ አልለቅህም፣ ብሎ ነገሩን ሁሉ፣ በኤልሻዳዩ እግር ስር ማስቀመጥ መለማመድ ይኖርበታል። ይህ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ሳይሆን፣ በሒደት እያዳበርነው፣ እያሻሻልነው የምንመጣው ጉዳይ ነው።

የዓለምን እውቀት እና ጥበብ፣ የዓለምን ተረትና ምሳሌ፣ የሰዎችን ጥበብ ወይም ውሳኔ፣ ሳናስተናግድ፣ ጌታ እግዚአብሄር ከዚህ ሁሉ በላይ መሆኑን ማመንና ማወቅ፣ ምድራዊውንም ሆነ ሰማያዊውን ህይወታችንን ሰላማዊ ያደርገዋል።

አባት ሆይ፣ ካንተ ጋር ፈጽሞ መጣበቅ ይሁንልን። የሰዎች እውቀት እና ድምዳሜ ዛሬ ከዓእምሯችን ላይ የተፋቀ ይሁን። ሰዋዊ የአኗኗር ስልታችና እና ቀመራችንም ዛሬ፣ ከእኛ ላይ እንደ ቅርፊት ይውደቅና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መመላለስ ይሁንልን። ካንተ በሆነ ጥበብና መገለጥ ሙላን። ሰምተህኛልና ተባረክ።


ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ?

No comments:

Post a Comment