Saturday, June 6, 2015

መልካሚቱ እጅ



ዲቮሽን 269/07 ቅዳሜ፣ ግንቦት 29/07
(
በዶ/ በቀለ ብርሃኑ)

መልካሚቱ እጅ

ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ ወረድህ” (ኢሳይያስ 643)

ባለፉት ዘመናት በመጽሐፍ ቅዱስና በታሪክ ተከስተው የነበሩ ከአርያም የሆኑ ጉብኝቶች፣ አሁንም በዚህ ዘመን በሚገባ ሊከሰቱ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ መለኮታዊ ጉብኝቶች ጊዜ አላለፈባቸውም! ቢሆንም አንድ ሊታወቅ የሚገባው ነገር፣ ከሰማይ የሆኑ ጉብኝቶች ጌታ ራሱ ባቀደውና በወደደው ሰዓት ነው የሚከሰቱት፤ በፍጹም የሰው እጅ የለባቸውምና፡፡

ታዲያ ጌታ ነፍሱ በወደደችው ሰዓት ከተፍ ሲል፣ ሕይወታችን በማይቀለበስ ሁኔታ ይቀየራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ከላይ የሆነ ለውጥ ያገኛቸውን ሰዎችም አይቼ፣ እጅግ ተደንቄና በኃይል ጓጉቼ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ፣ እኛ ልናቅደውና በፈቃዳችን ልንለማመደው የማንችለው መሆኑ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ነው”(ምሳሌ 161) እንደሚል፣ ከእኛ የሚጠበቀው መንፈሳዊ ጆሮአችንንና ዓይኖቻችንን አንቅተን፣ በጉጉት አሰፍስፈን፣ በቃሉ ውስጥ ሆነን፣ ፊቱን ያለማሰለስ መፈለግ ነው፡፡ በቃ ይኸው ነው ከእኛ የሚጠበቀው!

በነገራችን ላይ እዚህ አስደናቂ የሆኑ የጌታ ጉብኝቶች እንዳያገኙን ምን ከለከለን ብሎ መጠየቅ አግባብ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ልባችን በብዙ ነገሮች ተይዟል፤ ጆሮዎቻችን በሌሎች ረብ በሌላቸው ነገሮች ተደፍነዋል፤ መንፈሳዊ ራቡና ጥማቱ የለንም፤ ጠበቅ አድርጐ የጌታን ፊት መፈለግ አቅቶናል፤ አእምሮአችን በብዙ ነገር ተቀምቷል፤ ሰብሰብ ማለት አልቻልንም፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

መንፈሳችሁን ለማነቃቃት ያህል የእግዚአብሔር መልካሚቱ እጁ ስታገኘን እንዲህ ነው የሚሆነው፡፡ አብሮነቱ ከወትሮው በሚገርም ሁኔታ ይታወቀናል፤ ያለ እሱ የማንረባ ሰዎች መሆናችንን እንገነዘባለን፤ ግሩም የንስሐ ጊዜ ይኖረናል፤ ሕብረታችን ይጠልቃል፤ በተግባር ደረጃ ደግሞ ታዛዦች እንሆናለን፡፡ አዎ ለውጡ ታላቅ ነው፤ እንደ ኢዮብመስማትን በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፣ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ” (ኢዮብ 425-6) እንላለን፡፡ እንደ ያዕቆብእግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ ሰውነቴም ድና ቀረች” (ዘፍጥረት 32:30) የሚል ምሥክርነት ይኖረናል፡፡ ወይምከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ ከንፈሮቻቸው በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ፣ ዓይኖቼ የሠራዊት ጌታ ንጉሡ እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁ”(ኢሳይያስ 6:5) የሚል የትሕትና ቋንቋ ያለ ትግል ከውስጣችን ይወጣል፡፡

በእርግጥ የጌታን ግርማ፣ ኃያልነት፣ ቅድስና እስክናይና አባቶቻችንን ያገኘች መልካሚቱ እጁ እስክታገኘን አስቸጋሪ ሰዎች ሆነን እንቀጥል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እሱን በክብሩ ስናየው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ነው የሚቀየሩት፡፡ ስለዚህ አንድ ነገር እናድርግ! ሙሴን፣ ነህምያን፣ ዕዝራንና ሌሎችንም የእግዚአብሔር ባሪያዎች ትሑትና ታዛዥ አድርጋ ያቆመችው መልካሚቱ እጁ በእኛ ላይ እንድትመጣና የክብር ዕቃዎቹ እንድንሆን ፊቱን እንፈልግ !


ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ?

No comments:

Post a Comment