Friday, June 5, 2015

ማራናታ

ዲቮሽን 268/07 አርብ፥ ግንቦት 28/07
(በወንድም አበባዬ ቢተው)

ማራናታ

"ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። ..." (1ኛ ጴጥ 4:7)

የጌታ ዳግመኛ መምጣት ትምህርት እና የመጠባበቅ ሕይወት በጽድቅና በቅድስና እንድንኖር ያነቃቃናል።

ለአንዳንዶች የንጥቀት፡የታላቁ መከራ፡የጌታ ዳግም ምጽአት፥ የፍፃሜው ጦርነት፥ የሺህ ዓመት መንግስት፥ የመጨረሻው ፍርድ..... አስተምህሮዎች የስነ መልኮት ምሁራን የፈጠሯቸውና ምንም ትርጊም የሌላቸው እወጃዎች ይመስሏቸውል። በአስተምህሮዎቹ ዙሪያ የተለያዩ ምሁራን የተለያየ አይነት አመለካከት እንዳሏቸው ይታወቃል።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያለው መሰረታዊዉ የነገረ ፍፃሜ አስተምህሮ ግን ጥርጥር ዉስጥ የሚገባ አይደለም። አንዳንዶች ደግሞ በስህተት አስተማሪዎች የድፍረት ትንበያ ምክንያት በዚህ እና በዚያ ሰዓት ይመጣል ብለው በጠበቁበት ጊዜ ስላልመጣ ወደ ቸልተኝነት እና ዘባችነት ተለውጠዋል። ( 2ኛ ጴጥ 3፥3)

ጌታ ግን እንደ ተስፋ ቃሉ ይመጣል!! ሃሌ ሉያ!

አሁን በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉ ነገሮች ሁሉ የጌታን ዳግም ምፅዓት መንገድ የሚያዘጋጁ እና ጥርጊያውን የሚያቀኑ ናቸው። መድረኩ ተመቻቸቷል። መጨረሻው ከምናስበው ይልቅ ቀርቧል። የአለም የምጣኔ ሃብት ቀውስ፡ የፖለቲካው ሥነ ምህዳር፡ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፡ የቴሌኮሙንኬሽን የትራንስፖርት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች አቢዎት...ወ.ዘ.ተ የጌታን ምጽዓት በደጅ መሆን መለከት ነፊዎች ናቸው።

ስለዚህ ወገኖቼ ሆይ የጌታን መምጣት በሚያፋጥን ሕይወት እና አገልግሎት እንመላለስ። እንደዚያ ክፉ ባሪያ የጌታየ መምጣት ይዘገያል ብለን በማሰብ በመምጣቱ ጊዜ በሚያሳፍረን ርካሽ ሕይወት አንመላለስ። (ማቴ 24፥48, ሉቃ 12፥45) ይልቁንም ከመብራታቸው ጋር በማሰሯቸው ዘይት እንደያዙ ልባም ቆነጃጀቶች ሁልግዜ በንቃት እንኑር። (ማቴ 25፥4) ይህም በሙሉ ፀጋ እንድንኖር ከማስቻሉም በላይ በመምጣቱ ጊዜ ክብርን እና ሽልማትን ያስገኝልናል። (1ቆሮ 1፥7, ሉቃ 12፥37)

ጌታ ሆይ ቶሎ ና!

"ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤" (2ኛ ጴጥ 3:11-12)

No comments:

Post a Comment