Wednesday, June 3, 2015

ኃጢአት የሌለበት – ይውገራት!

ዲቮሽን 266/07፥ ረቡዕ፣ ግንቦት 26/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)



ኃጢአት የሌለበት – ይውገራት!

መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት። የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ(ዮሐ 8፡4-8)።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ‹‹ክርስቲያን ነን›› ባይ ፈሪሣዊያን ዋነኛ ሥራቸውን የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ሕይወት በአደባባይ ማውገዝ፣ መውገርና መግደል እየሆነ መጥቷል፡፡ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው መድረኮች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በማኅበራዊ ገጾችና በተገኘው ስብሰባ ሁሉ ነቢያትን፣ ፓስተሮችን፣ ሐዋርያትንና ያገኙትን ሁሉ ለማውገዝ፣ ለመውገርና ለመግደል ሲሻኮቱና ሲራኮቱ ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ ፈሪሣዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ ነቢያት ሲነሱ ለምን ተነሱ ብለው ይበሳጫሉ! ሐዋሪያት ሲነሱ፣ ለምን ተነሱ ብለው ይበሳጫሉ! በቤተክርስቲያን ውስጥ ፈውስና ተአምራት ሲሆን በዚህም ይበሳጫሉ! አዳዲስ አጥቢያዎች ተተክለው ብዙ ሕዝብ ወደ እነርሱ ሲጎርፍ፣ ብዙ ሰዎች ሲድን፣ የብዙሐን ቀንበር ሲሰበር ሲያዩ በዚህም ይበሳጫሉ! አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻነሎች ሲከፈቱና አዳዲስ የፕሮግራም ፎርማቶች ወይም አቀራረቦችም ሲተላለፉ ቢመለከቱ በዚህም ይበሳጫሉ! ነቢያት ወደ ኢትዮጵያ ሲጋበዙ በዚህም ይበሳጫሉ…!

ወገኖች ሆይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አገልጋይ ወደቀ የሚል ሐሜት ሲሰማ፣ ፈሪሣዊያን ባንዴ ብድግ ይላሉ፡፡ የተወራው ሁሉ እውነት ይሁን ውሸት ምንም ሳያጣሩ፣ ወሬውን እየተቀባበሉ መልሰው ያናፍሱታል፡፡ አንድ መረጃ በሆነ መገናኛ ብሐሃን በሆነ አጀንዳ ምክንያት የወጣም ቢሆን ጉዳዩ በቅጡ ሳይጣራ እየተቀባበሉ ያናፍሱታል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አንድ አማኝ በድፍረትም ሆነ በስህተት ኃጢአት ሊሠራ ይችላል፡፡ አማኞች የሚሠሯቸው አንዳንድ ኃጢአቶች ከፍ ያለና ከባድም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አማኝ በኃጢአት ወደቀ ብለን ያ አማኝ በአደባባይ ተወግሮ እንዲሞት መንቀሳቀስ ‹‹ፈሪሣዊነት›› እንጂ ‹‹መጽሐፍ ቅዱሳዊ›› አይደለም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የአንድን አማኝ ወይንም አገልጋይ ሕይወት ውድቀቱን አጡዞ በማጉላት በፌስቡክ፣ በጋዜጣና መጽሔት፣ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው መድረኮች ለማውገዝ፣ ለመውገርና ለመግደል መሻኮትና መራኮት ‹‹ፈሪሣዊ›› እንጂ ‹‹መጽሐፍ ቅዱሳዊ›› አይደለም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ‹‹ፈሪሣዊያን›› እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ይዘናታል፣ ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዝዞናል!›› ወገኖች ሆይ፣ ፈሪሣዊያን በባህርያቸው ግመል እየዋጡ ትንኝ የሚያጠሩ ናቸውና፣ የእያንዳንዳቸው የግል ሕይወት በጓዳና በመሥሪያ ቦታቸው ቢመረመር፣ ውስጣቸው የሚሸትት አስከሬን ደብቀው፣ ውጫቸውን በሐውልት የሚያሳምሩ ሸንጋይ ጉረኞች ናቸው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በሀገራችንም የሌሎችን ሰዎች ሕይወት ለማውገዝ፣ ለመውገርና ለመግደል ሲንቀሳቀሱ የምንመለከታቸው ፈሪሣዊያንም የእያንዳቸውን ሕይወት ጠጋ ብለን ስንመለከት ከመድረክ ውጭ ያለው፣ ከአደባባይ ውጭ ያለው፣ ከስብሰባ ውጭ ያለው ሕይወታቸው እንደበሰበሰ ሥጋ የሚሸትት ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ፈሪሣዊያን ስታመነዝር ተገኝታ የተያዘችን ሴት በሕጉ መሠረት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ጌታችን ኢየሱስ እንዲያጸድቅላቸው ሲያመጡ ለፈሪሣዊያኖቹ ምን ብሎ እንደመለሰላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፡፡ ‹‹ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት፡፡›› ከዚህ ንግግር በኋላ ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ፈሪሣዊያኖቹ ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።

ታውቃላችሁ፣ የሌሎችን ሰዎች ኃጢአት ለማውገዝ፣ ለመውገርና ለመግደል የሚንቀሳቀሱ ፈሪሣዊያን የእያንዳቸውን ሕይወት ጠጋ ብለን ብንመለከት ከመድረክ ውጭ ያለው፣ ከአደባባይ ውጭ ያለው፣ ከስብሰባ ውጭ ያለው ሕይወታቸው እንደበሰበሰ ሥጋ የሚሸትት ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ የሀገራችንም ፈሪሣዊያን ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች ድረስ በየመሥሪያ ቤቶቻቸው፣ በየቤተእምነቶቻቸው፣ በየግል ሕይወታቸው ቢመረመር የየራሳቸው ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ አሁን እያደረጉ ያሉትን የሚያደርጉት ይሉኝታና ትልቅነታቸው አስቸግሯቸው እንጂ ሕሊናቸው ማንነታቸውን ያውቀዋል! የእያንዳንዳቸው ማንነት እንደእነርሱ ሁሉ በአደባባይ ቢገለጥ አንድ አንድ እያሉ ከጨዋታ ሰልፍ እየወጡ የሚሄዱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፈሪሣዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ ነቢያት ሲነሱ በዚህም ይበሳጫሉ! ሐዋሪያት ሲነሱ፣ ለምን ተነሱ ብለው በዚህም ይበሳጫሉ! በቤተክርስቲያን ውስጥ ፈውስና ተአምራት ሲሆን በዚህም ይበሳጫሉ! ወጣቶች አዳዲስ አጥቢያ ተክለው ብዙ ሕዝብ ወደ እነርሱ ሲጎርፍ፣ ብዙ ሰዎች ሲድኑ፣ የብዙሐን ቀንበር ሲሰበር ሲያዩ በዚህም ይበሳጫሉ! አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻነሎች ሲመጡ በዚህም ይበሳጫሉ! ነቢያት ወደ ኢትዮጵያ ሲጋበዙ በዚህም ይበሳጫሉ…!

ወገኖች ሆይ፣ ስታመነዝር ተገኝታ የተያዘችን ሴት ጌታችን ኢየሱስ ምን እንዳደረጋት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፡፡ አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት። እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።

ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአተኞች አይፈርድም! ይህም የክርስቲያኖች ሁሉ አስተሳሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአተኞች አይፍረድ እንጂ፣ ኃጢአተኞች በኃጢአታቸው እንዲቀጥሉ አይፈልግም፡፡ ኃጢአተኞች ከኃጢአታቸው ተመልሰው በጽድቅ ሕይወት እንዲመላለሱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስታመነዝር ተገኝታ የተያዘችን ሴት በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣና መጽሔት፣ እንዲሁም በሕዝብ መድረኮች አላዋረዳትም፣ አልተሳደባትም፡፡ ይልቁንም፣ ‹‹እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከእንግዲህ ግን ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ›› ነው አላት።

ወገኖች ሆይ፣ ከኢየሱስ እንማር! በኃጢአተኞች አንፍረድ! እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአተኞች መሞት ባንችል እንኳ፣ ኃጢአተኞች ከኃጢአታቸው ተመልሰው በጽድቅ ሕይወት እንዲመላለሱ ለኃጢአተኞች በመጸለይና በመማለድ የምንችለውን ሁሉ መስዋዕትነት እንክፈልላቸው! እግዚአብሔር የምድራችንን የክርስትና እምነት ይባርክ!

ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ?

No comments:

Post a Comment