ዲቮሽን 265/07፥ ማክሰኞ፣ ግንቦት 25/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
የያቤጽ
– ተማጽኖዎች!
ያቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ
እናቱም። በጣር ወልጄዋለሁና ብላ ስሙን፦ ያቤጽ ብላ ጠራችው። ያቤጽም። እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው እጅህም ከእኔ
ጋር ትሁን እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው(1ዜና 4፡9-10)።
‹‹ያቤጽ›› በእናቱ ተሰይሞ በመላው የሀገሩ
ሕዝብ ዘንድ የሚታወቀውን ‹‹የጣር ልጅ›› የሚለውን ክፉ ስም መለወጥ ችሏል፡፡ በእናቱ ላይ ያስከተለውን ጣርና ሕመም፣ ሙሉ በሙሉ
መለወጥ በመቻሉ ያቤጽ ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ለመሆን በቅቷል! ይህም ሊሆን የቻለው ጌታን አጥብቆ በመማጸኑ ነው! ከተማጽኖው የተነሣም ከጣር ወደ ክብር ሊሸጋገር ችሏል!
ወገኖች ሆይ፣ እኛም በሰዎች የተሰጠንን
ክፉ ስያሜ ጌታን በመማጸን፣ ልናስወግደው እንችላለን፡፡ በጣር ተወልደንም ቢሆን፣ በጣር አድገንም ቢሆን፣ ጌታን የሙጥኝ ብንል፣
ክፉ መጠሪያችንን ከላያችን ላይ አሽቀጥረን ጥለን፣ የምደር ኑሮአችንን በክብር መደምደም፣ በበረከት መፈጸም በእውነት እንችላለን!
ወገኖች ሆይ፣ አራቱ የ‹‹ያቤጽ›› ተማጽኖዎች
እነሆ!
(1) አቤቱ፣ መባረክን ባርከኝ
የእውነተኛ በረከት ምንጩ ከላይ ከእግዚአብሔር
ነው! የእግዚአብሔር በረከት ደግሞ የሰውን ልጆች ባለጠጋ ታደርጋቸዋለች (ምሣ 10፡22)፡፡
እግዚአብሔር ድሃ ያደርጋል፤ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፣
ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል(1ሳሙ 2፡7)፡፡
ስለሆነም በእውነተኛ በረከት ሊባርከን የሚችለውን ጌታ በጸሎት ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡
(2) አገሬን አስፋው
እውነተኛ አማኝ ‹‹የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል››
ማለትን የተማረ መሆን ይገባዋል(ፊልጵ 4፡11)፡፡ ደግሞም አማኝ ‹‹በጠበበው ደጅ መግባት›› የተረዳ መሆን ይገባዋል(ማቴ 7፡13)፡፡
ሲባል ግን፣ ያለው ለማስፋት፣ የያዘውን መጨመር አይገባውም ማለት አይደለም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ‹‹የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል››
ማለት እና ‹‹በጠበበው ደጅ መግባት›› ማለት፣ ‹‹ባሉበት መቆም›› ማለት አይደለም፡፡ እውነተኛ አማኝ የያዘውን እያጣጣመ፣ ነገር
ግን ጌታ ወዳየለት ቦታ ለመድረስ፣ ገደብና ድንበር በመጣስ፣ የተዘጋጀለትን ምድር ጨርሶ ለመውረስ የቆረጠ መሆን ይኖርበታል!
ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ያየልንን ከመውረስ
ከሚከለክል ከጠባብ ራዕይ፣ ከጠባብ አመለካከትና ከጠባብ አስተሳሰብ እንውጣ! የጌታን በረከት ከመውረስ ከሚያግዱን ከማናቸውም ጠባብ ፍስልፍና እንውጣ!
(3) እጅህ ከእኔ ጋር ትሁን
የእውነተኛ አማኝ ስሙ በመልካም የሚቀየረው፣
ከሥጋ ወገኖቹ ይልቅ የተከበረ ለመሆን የሚበቃው፣ ጌታ ወዳየለት ቦታ መድረስ የሚችለውና፣ ገደብና ድንበር በመጣስ፣ የተዘጋጀለትን
መውረስ የሚችለው የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስትሆን ብቻ ነው! ታሪክ የምትለውጥ – ድንቅን የምትሠራ የእግዚአብሔር እጅ፣
በእኛ ላይ ስትመጣ
የማይነቀል አጥር፣ የማይሰበር ቅጥር፣
የማይለወጥ ነገር፣ የማይወረስ ምድር ፈጽሞ አይኖርም!
(4) እንዳያሳዝነኝ ከክፋት ጠብቀኝ!
አንዳንዴ በገዛ እጃችን የገዛ ልባችንን
የሚሰብር ነገር እንነካካለን፡፡ አውቀን ሆነ ረስተን፣ ሆን ብለን ይሁን ዘንግተን፣ ከሆነ በኋላ የሚኮንነንን እንፈጽማለን፡፡ በድፍረት
ይሁን በስህተት፣ ውሎም ሆነ አድሮ ልብን የሚያሳዝን፣ ነፍስን የሚያሳድፍ ነገር እንሠራለን፡፡ በእሳት በመጫወት፣ ተንጋልለን በመትፋት፣
አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆነን እንገኛለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ስም የለሽ ስማችን እንዲቀየርልን፣
ክብር የለሽ ኑሮአችን እንዲለወጥልን፣ ጌታ ወዳየልን አድራሻ ለመድረስ ኬላና ድንበሩን ጥሰን ጠረማምሰን መውረስ እንድንችል፣ የአምላካችን
እጅ በእኛ ላይ ትሁን፡፡ በገዛ እጃችን ክፉ ነገር ዘርተን ሐዘን ሥቃይና ጉዳት ማጨድ እንዳይከተል ጌታ ይጠብቀን!
No comments:
Post a Comment