ዲቮሽን 264/07፥ ሰኞ፣ ግንቦት 24/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ማምለጫዬ!
የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው። ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ሮጦ ከፍ ይላል። ምሳሌ 18፡10
ጠላት ሊጎዳን እና ሊያጠፋን ሲያስብ የሚጠቀምበት መንገድ ልዩ ልዩ ነው። አንዳንዴ በውድቀት አስመስሎ መልኩን እየቀያየረ በእኛ ላይ ጥቃቱን ሊሰነዝር ይሞክራል። እግዚአብሔር በኛ ላይ ተስፋ የቆረጠ እና ዳግመኛ በሕይወታችን ላይ የማይሠራ አስመስሎ ይተርክልናል። እግዚአብሔር ቢሰራ ኖሮ እስከዛሬ ድረስ አይሠራልህም ነበር? ቢያድንህ ኖሮ እስከዛሬ አያድንህም ነበር? እንባህን ቢያብስ ኖሮ እስካሁን አያብስልህም ነበር? ቢሰማህ ኖሮ እንዲህ ስትሆን ዝም ይላል? ወይም ደግሞ በሀጢያታችን እየከሰሰ፣ በትናንትናችን እየፈረደ፣ የዘራኸውን ላታጭድ ትፈልጋለህ? በሚል መንፈሳዊ መሳይ ጥቅስ ይመታናል።
እነግራችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ግን ውሸት ነው። መጽሐፍ ሲናገር፣ ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል፣ ይነሳማል። ይላል። ስለዚህ፣ ሁሉን ከሚችለው እና ከሚያስችለው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ዳግም መነሳትን መቆም ይሆንልናል። እንዲህ ያለ ነገር ሲከበን፣ ፈጽሞ፣ ፈ.......ጽ.......ሞ ለጠላታችን ከንቱ ልፍለፋ መንበርከክ አይገባንም። ሚኪያስ (7፡ 8) እንዳለው፣ ጠላቴ ሆይ፣ ብወድቅ እነሳለሁና፣ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሐን ይሆንልኛልና፣ በኔ ደስ አይበልህ። ብለን፣ በእውነተኛ ንስሐ ወደ ጌታ እንመለስ። በብርቱ ሩጫ፣ ሮጠን አምልጠን ወደ እግዚአብሔር እንጠጋ፤ የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነውና!!!!
አባት ሆይ፣ አስተማማኝ ማምለጫና መሸሸጊያ ሆነህናልና ተባረክ። ዛሬ፣ አሁን፣ ለኔም ሆነ ለወገኖቼ ወደ አንተ በአዲስ ኃይልና የንስሀ ጉልበት መመለስ ይሁንልን። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ዛሬ እያንዳንዳችንን ወደ ፈቃድህ አስገባን። የጠላታችን ከንቱ ምክር ሁሉ፣ በከበረው በኢየሱስ ስም ለዘላለም የተረገመ ይሁን። አሜን።
No comments:
Post a Comment