Thursday, June 11, 2015

አንዲት ነገር – እሻለሁ!



ዲቮሽን 274/07 ሐሙስ ሰኔ 4/07
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

አንዲት ነገር – እሻለሁ!

እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ (መዝ 274)

ወዳጄ ሆይ፣ ከእግዚአብሔር አንዲት ነገር ብቻ እንዲለምኑ ቢጠይቁ፣ ጌታን የሚጠይቁት ስለምንድነው? በሕይወትዎ ዘመን ሁሉ ከምንም ነገር በላይ አጥብቀው የሚፈልጉት ነገር ምንድነው?

ወገኖች ሆይ፣ የአንዳንዶች ልመና፣ ጥያቄና መሻት ምግብ ስጠኝ፣ መጠለያ ስጠኝ፣ ትዳርና ልጅ ስጠኝ፣ ሀብት፣ ክብርና ዝና ስጠኝ፣ ዕውቀት፣ ግርማና ሞገስ ስጠኝ፣ ይህን ስጠኝ፣ ያንን ስጠኝ፣ ስጠኝ፣ ስጠኝ፣ ስጠኝ ነው፡፡ ነገር ግን ወገኖች ሆይ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ጊዜያዊ፣ ኃላፊና ጠፊ ናቸው፡፡

ታውቃላችሁ፣ የዳዊት ልመና፣ ፍላጎትና ጥያቄ በቃ አንድ ነገር ብቻ ነው! ይህም፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት መኖር ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የድነታችን ምሽግ፣ ለሕይወት ዋስትና፣ ከለላ መከታ፣ መደበቂያ ዋሻ፣ መከላከያ ጋሻ፣ የእግዚአብሔር መገኛ ውበትና ደስታ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የማይደፈር ዓለት፣ የማይነካ እሳት፣ የማይፈርስ ምሽግ፣ የጸና ግንብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የደስታና ሐሴት፣ ሰላም መረጋጋት፣ የሀብት የበረከት፣ የድልና ስኬት፣ የመውጣት የማለፍ የመከናወን ቤት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የዝና የክብር፣ የግርማ የሞገስ፣ የከፍታ የዕድገት፣ የድንቅ የምልክት፣ የፈውስ የተአምራት ቤት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የእውቀትና ጥበብ፣ መረዳት፣ ማስተዋል የልዕቀትም ቤት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የቅኔ ዝማሬ፣ ምስጋና ውዳሴ፣ የእልልታ ሽብሸባ፣ የጭብጨባ ቤት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የሹመት ሽልማት፣ የማዕረግ፣ የኒሻን፣ የሜዳሊያ ቤት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ቤት የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የክብሩ መገኛ፣ የኃይሉ መገለጫ፣ የመንፈሱ ደስታ፣ ፍቅርና እርካታ፣ ሌላውም ሌላውም ሁሉ በአንድ ተጠቃልሎ የሚገኝበት ቤት ነው!

ወዳጄ ሆይ፣ መዝሙረኛው ዳዊት የተረዳው ይህንን እውነት ነው! በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፣ ከላይ የቀረቡት፣ ያልቀረቡም ሁሉ እንዲህ ተጠቃልለው ማግኘት እየተቻለ፣ የሰው ልጅ መባዘን፣ የሰው ልጅ መባከን የሚያሳዝን ነው! ይህን ምንጭ ትቶ፣ በሌላ አቅጣጫ በረከት ፍለጋ መባከን መቅበዝበዝ የሚያሳዝን ነው! 

የሁሉ ነገር ምንጩ እዚህ ላይ እያለ፣ ከአጋምና ከእሾኽ ከጨጎጊት መካከል የወይን ፍሬ ለማግኘት መከራ ፍዳውን ጠዋትና ማታ ሲጋት ለሚውለው አወይ ለሰው ልፋት! አወይ ለሰው ድካም!

ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment