ዲቮሽን 275/07፥ አርብ፥ ሰኔ 5/07
(በወንድም አበባዬ )
(በወንድም አበባዬ )
የእግዚአብሄርን ድምፅ በመስማት እንደግ
"በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ.."(ዮሐ10:27)
"አውቅም ዘንድ አሰብሁ" (መዝ 73:16)
"አውቅም ዘንድ አሰብሁ" (መዝ 73:16)
በዚህ ዓለም ስንኖር የእግዚአብሄርን ግልፅ ምሪት የምንፈልግባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። ይህ ደግሞ ከተለያዩ ድምፆች መካከል ትክክለኛውን የእግዚአብሄር ድምፅ መለየትን ይጠይቃል። የጌታ፥ የሰው፥ የሁኔታ፥ የስጋ፥ የሰይጣን....ወዘተ ድምፆች አሉ። እነዚህን የምንለየው ደግሞ በሰማናቸው ጊዜ ድንገት ከተፍ የሚልልን አማራጭ አፈፍ በማድረግ ሳይሆን ቆም ብለን ከጌታ የሆነውን በመመርመር ነው። ይህ ደግሞ ድንገት የሚገለጥልን ሳይሆን የረዥም ጊዜ መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያጠይቅ ነገር ነው።
የስነ መለኮት ምሁራን የእግዚያብሄርን ፈቃድ የተገለጠ እና ያልተገለጠ ብለው ይከፍሉታል። ለምሳሌ ወንድ ሴትን፥ ሴት ደግሞ ወንድን ማግባቱ ፀሎት እና ምሪት የማያስፈልገው ግልጥ ፈቃዱ ነው። ማንን ነው ማገባ የሚለው ግን ስማቸው በመፅሐፍ ቅዱስ ተፅፎ ስላልተቀመጠ ያልተገለጠ እና ፀሎትና ምሪት የሚያስፈልገው ነገር ነው።
ልናገባ ስንል፥ አዲስ ስራ ልንጀምር ስንል፥ ሽርክና ስናስብ፥ አገር ልንቀይር ስናስብ፥ መራቅ እና መቅረብ ስንፈልግ፥ ለማገልገል፥ የከበረውን ከተዋረደው ለመለየት ስንወጣ ስንገባ....ወ.ዘ.ተ. የእግዚአብሄርን ምሪት እንናፍቃለን። አሁን አሁንም አብዛኞቻችን ይተነብያሉ ይገለጥላችዋል ወደ ምንላቸው ሰዎች እንሄዳለን፥ ስልክም እንደውላለን።
የእነዚህን ሰዎች አገልግሎት መጠቀሙ ባልከፋ። ጥያቄው ግን የእግዚያብሄር ቃል እንደ ሚለው እኛ የእግዚያብሄርን ድምፅ እንሰማለን ወይ? የሚለው ነው!!!
እግዚአብሄር ፈቃዱን የሚገልጠው በልዩ ልዩ መንገድ እና ጎዳና እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የእግዚያብሄርን ድምፅም የምሰማው እንዲሁ በልዩ ልዩ መንገድ ነው። የእግዚያብሄር ምሪትም በልዩ ልዩ ሁኔታ ይገለጣል። ከእኛ ዳግም በመንፈስ ቅዱስ ከተወለድን አማኞች ግን የሚፈለግ ዝቅተኛ ተፈላጊ ልምድ እና ልምምድ አለ።
ወገኖቼ እንደ እግዚአብሄር ልጅነታችን ድምፁን ልንሰማ የተገባ ነው። የእርሱ በጎች እንደመሆናችን መጠን የእረኛችንን ድምፅ መስማት የሚጠበቅ ነው። ይህ የሚሆነው ግን ዘወትር በእርሱ ፊት የመገኘት ልምድ ስናዳብር ነው። ቃሉን በማሰላሰል እና በፀሎት የምናሳልፍበት ቋሚ ፕሮግራም ሲኖረን የመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ ይገባናል። ከእርሱ ጋር የምንግባባበት ኮድ እና ፕሮቶኮል እናበጃለን። በሚገባን መንገድ ይናገረናል። እኛም እንሰማዋለን። የእርሱን ድምፅ መስማትም ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ይሆንልናል። ከመሰናከል እና ከመደነባበር እንተርፋለን።
ስለዚህ ለጌታ ጊዜ እንስጥ። የጥሞና ጊዜን እናዳብር። ቃሉን እናጥና፥ እናሰላስል። ፀሎትን የሙጥኝ እንበል። በልዩ ልዩ መንገድ የሚገለጠውን የእግዚያብሄርን ፈቃድ እና ድምፅ በንቃት እንከታተል። በመታዘዝም ይበልጥ ለሚገለጠው ፈቃዱ ራሳችንን እናመቻች።
"እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" (1ኛ ቆሮ 2:12)
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያስው ላይክ ያድርጉ፡፡
No comments:
Post a Comment