ዲቮሽን 263/07፥ እሁድ፣ ግንቦት 23/07
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
ጉዳት እስክታልፍ
ይህ አጭር ጽሑፍ መዝሙር 57 ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ በግሌ እጅግ በጣም የምወደው ክፍል ነው፤ ሙሉውን በርጋታና በማስተዋል እንድታነቡት ጋብዤአችኋለሁ፡፡
ከሰዎች ጋር ስንኖር መቀራረብ ይኖራል፣ መራራቅም እንዲሁ፡፡ በመቀራረብ የሚመጣ በረከት አለ፡፡ ጉዳትም ይኖራል፡፡ በተጨማሪም ባልጠበቅነው መንገድ የሚመጡ ብዙ ጉዳቶችና ስብራቶች ይኖራሉ፡፡ ከቤት መውጣት እስኪያስጠላንና አፍረን አንገት እስክንደፋ ድረስ የሚያደርገን ፈተና ሊመጣብን ይችላል፡፡ መኖርን እስከመጥላት ልንደርስም እንችል ይሆናል፡፡ በግሌ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ደጋግሜ ማለፌን አልደብቃችሁም፡፡ እነዚያ ገጠመኞች ግሩም የመሠሪያ ጊዜም እንደነበሩ አበስራችኋለሁ፡፡ ይህንን አስመልክቶ ሐዋርያው ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፡-
“ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት፡፡ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።” (ያዕቆብ 1፡2-4)
ንጉሥ ሳኦል ዳዊት በነበረው አስተዋይነት ድልና ስኬት ክፉኛ ቀንቶ ስለነበረ፣ ሊያጠፋው ያልሞከረው ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዳዊት ለረጅም ጊዜ በስደትና በእንግልት አሳልፏል፡፡ ዳዊት ይህንን ቅኔ የተቀኘው ከሳኦል ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ ነበር(1ሳሙኤል 22፡1)፡፡ ይህ ጊዜ ለዳዊት ከባድ የመከራና የኅዘን ጊዜ ነበር፡፡ በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ቀርቷልስ ብሎ የለ? ለዚህ ነው “ማረኝ አቤቱ ማረኝ” (ቁ.1) ብሎ አምላኩን የተማጸነው፤ አስመልጠኝ ማለቱ ነው፡፡ አዎ፣ ዳዊት ከባድ ጉዳት ላይ እንደ ነበር ምንም አያጠያይቅም፡፡
ታዲያ ዳዊት በአምላኩ ላይ የነበረውን መታመንና መሰጠት “ልቤ ጨካኝ አቤቱ ልቤ ጨካኝ ነው” (ቁ.7) በሚል ቋንቋ ገልጾታል፡፡ በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች my heart is fixed የሚል ትርጉምን የያዘ ሐሳብ ሲሆን፣ ዳዊት “አልናወጥም አምላኬን እጠብቃለሁ” ማለቱ ነው፡፡ ለመሆኑ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ የኛስ ምላሽ ምን ይሆን ?
ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፣ በዚህች አጭር ሕይወት ውስጥ ‹‹ጉዳት›› አይቀሬ መሆኑ ሲሆን፣ መጠየቅ ያለበት ነገር ግን “ጉዳት እስኪያልፍ ምን ላድርግ?” የሚለው ይሆናል፡፡ ዳዊት በአምላኩ ላይ የሚደገፍና የጸሎት ሰው ስለነበር “ወደ ሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚብሔር እጮኻለሁ” (ቁ.2) በማለት መደገፊያውና መታመኛው እግዚአብሔር እንደ ሆነ በግልጽ አብስሮናል::
እርግጥ ነው ጉዳት በተለያየ መንገድ ሊከሰት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ የሕይወታችን ዘይቤም ይመስላል፤ ከሱ የሚያመልጥ የለምና፡፡ያቀረብናቸው ሰዎች የልብ ቁስል ሊያመጡብን ይችላሉ፤ ሊከዱን ይችላሉ፡፡ ሊገፉንና ሊጥሉን ይችላሉ፡፡ ደስ የሚለውና ሊታወቅ የሚገባው ነገር ግን እግዚአብሔር በፍጹም ታምነው የተደገፉበትን ሰዎች አይጥልም፡፡ ስለዚህ ወገኖቼ ልጠይቃችሁ፡፡ የታመናችሁትና የተደገፋችሁት ማንን ነው?
ዳዊት“ጉዳት እስክታልፍ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ” (ቁ.1) ብሎ ተናግሯል፡፡ እኛስ በጉዳት ውስጥ ስንሆን ምንድነው የምናደርገው? ዳዊት መከራም ውስጥ ሆኖ በእግዚአብሔር የክንፎች ጥላ በመታመኑ “ከሰማይ ልኮ አዳነኝ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው” (ቁ.3) ብሎ መስክሯል፡፡
በግሌ ያዘንኩባቸውና የተጐዳሁባቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በነዚያ ጊዜያት ደጋግሞ ደርሶልኝ እርሱን የሚመስል አጽናኝና ደጋፊ እንደሌለ በማያሳስት መንገድ ተምሬአለሁ፤ ስለዚህ በድፍረት “ጌታ ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው” እላለሁ፡፡ እናንተስ ?
ጽሑፌን እንደ ገና በጥያቄ ልጨርስ፡፡ ወገኖቼ ጉዳት እስክታልፍ ምንድነው የሚታያችሁ፣ ደግሞስ ምንድነው የምታደርጉት?
No comments:
Post a Comment