Saturday, May 9, 2015

የመንፈሳዊ ፍሬያማነት ምስጢር

ዲቮሽን 241/07፥ ግንቦት፥ 1/07
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)

የመንፈሳዊ ፍሬያማነት ምስጢር

ለጸሎት የሚያነሳሳኝና በልቤ ላይ በማይረሳ መልኩ ታትሞ የሚገኝ ቃል ኢሳይያስ 27፡5-6 ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ስላጠናሁትና ስላሰላሰልኩት፣ ለነፍሴ መልሕቅ ሆኗል ማለት እችላለሁ፡፡ እጅግ በጣም ግሩም ቃል
ነውና እርሱን ላስቀድም፡፡ እንዲህ ይላል፡-

“…ጕልበቴን ይያዝ፣ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፣ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ” (ኢሳ 27፡5-6)

“ጉልበቴን ይያዝ” የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ “መሸሸጊያው ያድርገኝ” የሚል ትርጉምን እንደያዘ አንብቤአለሁ፡፡ “ጉልበቴን ይያዝ ከእኔም ጋር ሰላም ያድርግ” የሚለው ሐሳብ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረትና ቁርኝት ከሰላማችን ጋር የተያያዘ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ አዎ፣የጌታን ጉልበት በጸሎት በያዝን ቁጥር ሰላማችን እየበዛና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እየተለወጥን መምጣታችን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ታዲያ ከመቼውም ዘመን ይልቅ የእግዚአብሔር ጉልበት በጸሎት መያዝ ያለበት ዘመን ቢኖር፣ የአሁኑ ዘመን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምን ቢባል የክፋት መጠን በኃይል እየጨመረና እያየለ መጥቷልና ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በውጭ ባሉት በማያምኑ ሰዎች ሕይወት ብቻ ሳይሆን፣ ጌታን እናውቃለን በሚሉት መካከልም በገሃድና በብዛት ስለሚታይ ያለውን የክፋት መጠን በኃይል ያጎላዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በክርስትያን ወገኖች መካከል ፍቅርና መዋደድ እጅግ ቀዝቅዟል፡፡ ውሸት፣ ግብዝነትና ራስ ወዳድነት አግጦ ወጥቷል፡፡ ቃል ኪዳንን ማፍረስ፣ አለመተማመንና እርስ በርስ መካካድ በዝቷል ….ሌላም
ሌላም(ዝርዝሩ ረጅም ነው)፡፡ ከዚህም የተነሣ የሰዎች የልብ ስብራት ከመጠን በላይ በዝቷል፡፡ እናም ያለንበቱን ዘመን አስፈሪነት ቋንቋ የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡

አዎ፣ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና” (ኤፌሶን 5፡16) መንፈሳዊ ሕይወታችን ሳይጐዳና ሰላማችን እንደተጠበቀ ለማለፍ፣ የጌታን ጉልበት በጸሎት መያዝ የግድ ነው፡፡ በዚህ አስጨናቂና ትርምስ በበዛበት ዓለም፣ የጌታን
ጉልበት በእምነት ይዘን ሙጭጭ ስንል፣ እንደ ያዕቆብ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” (ዘፍ 32፡26) ስንለውና ጥራት ያለው ጊዜን በፊቱ ደጋግመን ስናሳልፍ፣ መንፈሳችን ይጠነክራል፤ አረማመዳችን ይጸናል፡፡ እምነታችን ያድጋል ስለዚህም በምናየው ነገር መሸበራችን ይወገዳል፡፡ እናም በውጭ ባሉት ዘንድ ሳይቀር የሚታይ መረጋጋት የሕይወታችን መገለጫ ይሆናል፡፡ እንዲህ በጽናት ስንቀጥል፣ ለሌሎች የምንተርፍ የበረከት ሰዎች እንሆናለን፡፡

በዚሁ መጀመሪያ ላይ በተጠቀስኩት ምንባብ መጨረሻ ላይ ያለው የጌታን ጉልበት የመያዝ አስደናቂ ውጤት “በፍሬአቸውም የምድርን ፊት ይሞላሉ” የሚል ነው፡፡ ይህን ውጤት በጥልቀት ሳስበው በጣም ያስደንቀኛል፡፡ እስቲ እናንተ ይህ በተግባር ሆኖ ለሰከንድ በዓይነ ሕሊናችሁ ዕዩት፡፡ ይህ ሲሆን የማይነካ የማኅበረሰብ መዋቅር የለም፡፡ ይህ ሲሆን ብዙ ሰዎች ጉልበታቸውን ለጌታ ያንበረክካሉ፡፡ ይህ ሲሆን ብዙ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግሮች ይወገዳሉ፡፡ ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር በመካከላችንም ሆነ በውጭ ባሉት ዘንድ በሚገባ ይከበራል፡፡

ሐሳቤን ላጠቃለውና ልጨርስ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ያሉት መርሖዎች ተያያዥነት ያላቸው ስለሆኑ፣ እንደ ሰንሰለት የተያያዘ ሂደት አላቸው፡፡ ሂደቱ የጌታን ጉልበት በመያዝ ይጀምርና መጨረሻ ውጤቱ ፍሬ ነው--ምድሪቱን
የሚሸፍን ፍሬ! በግለ ሰብ ደረጃ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከውስጣችን የሚፈለቀቁት ዋናዎቹ ፍሬዎች፡- ጽድቅ፣ እግዚአብሔርን መምሰል፣ እምነት፣ ፍቅር፣ መጽናትና የዋህነት(1ጢሞቴዎስ 1፡11) ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ የፍሬና የበረከት ሰዎች እንድንሆን ከምር ጉልበቱን በጸሎት እንያዝ!!

ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ

No comments:

Post a Comment