ዲቮሽን 240/07 ሚያዚያ 30/07
( በወንድም አበባዬ ቢተው)
( በወንድም አበባዬ ቢተው)
የቃሉ ረሃብ
"ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ፤ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። " (ኤር 15:16)
ከአመታት በፊት.....። ትንሽ የህመም ስሜት ስለ ተሰማኝ ዕረፍት ላይ ነበርሁ። አጥባቂ ባልባልም በቤተ ክህነት ዙርያ ጉድጉድ እል ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ሌሎች አዋልድ መፃህፍትን ማንበብ ይቀናኝ ነበር።
ታዲያ በዚህ በታመምሁ ወቅት ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር ሌላ አላነብም ብየ ወሰንሁና ጀመርሁ። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን አለፍ አለፍ ብየ እያነበብሁ ሳለ የዕብራዉያን መልዕክት ስደርስ በጣም በትኩረት እና በተመስጦ ማንበብ ቀጠልሁ። ምዕራፍ 7 ቁጥር 11 ስደርስ ነገሮች ተቀየሩ።
ታሪኬ ተለወጠ! ሸክሜ ተራገፈ። አየሱስን ለመጀመሪያ ጊዜ በቃሉ ብርሃንነት በመንፈሴ አየሁት። ዳንሁ! ተለወጥሁ! ራሴን ተንበርክኬ እና በዕንባ ተሞልቼ ስፀልይ አገኘሁት! ከዚያን ቀን ጀምሮ ሌላ ሰው ሆንሁ! ጥቂት መከራ ብቀበልም ነፃነቴና ሰላሜ ብዙ ነው።
የእግዚያብሄር ቃል ብርሃን እና ሕይወት ነው። ማንኛዉንም ጨለማ አስወግዶ በብርሃን ይሞላል። ለሚቀበሉት እና ለሚያምኑትም ዘላለማዊ የዕረፍት ሕይወትን ይሰጣል።
ከተገለጠልን ቃል በላይ አንኖርም። ከበራልን የቃሉ ብርሃን በላይ እግዚያብሄርን አናውቀውም፡ አናምነውምም። በልባችን ከሚኖሩት የእርሱ ቃሎች በላይም ፍሬያማ አንሆንም። (ዮሐ 15፥7-8)
ታዲያ ወገኖቼ ይህ የእግዚያብሄር ቃል አላረጀም። ዛሬም በኃይል ይሰራል። በትኩረት ለሚከታተሉት ቃሉን ያስገኘው መንፈስ አሁንም ቃሉን ህያዉና የሚሰራ ያደርገዋል። ያኔ እንደተለወጥንበት ዛሬም ፍፁም የሕይወት ለውጥን ያመጣል። የዉስጥ ማንነታችንን በመመርመር ያጠራናል። (ዕብ 4፥12) አስተሳሰባችንን በማደስ የእግዚያብሄርን ፈቃድ በግልፅ እንድንገነዘብ ያግዘናል። የእግዚያብሄርን ድምፅ በቃሉ እንሰማለን።
ስለዚህ ወገኖቼ ከእግዚያብሄር ቃል ጋር ያለንን ቁርኝት እንፈትሽ። ዕለት ዕለት እንደ ቤርያ ሰዎች በልብ ስፋት እናጠናለን?(ሐዋ 17፥11) በግል ቋሚ የቃል ጥናት ጊዜ አለን? በሕብረት ከወንድሞች እና ከእህቶች ጋር ቃሉን እናጠናለን? ከወገኖች ጋር ስንገናኝ የምንንነጋገረው ቃሉን ነው? በልባችን የሞላው ቃሉ ነው? ምን ያህል ጥቅሶችን በቃላችን ይዘን በልባችን እናሰላስላለን? ከሌሎች መፃህፍት ይልቅ ለመፅሐፍ ቅዱስ ብዙ ትኩረት እንሰጣለን? ምን ያህል ሌሎችን በቃሉ እናፅናናለን?
እስኪ እራሳችንን በማስተዋል እንፈትሽ? እስኪ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በታሪክ የታዩ ታላላቅ የእግዚያብሄር ሰዎችን እንመልከት። ከእግዚያብሄር ቃል ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበራቸው ነበሩ። (መዝ 119፥16 2ጢሞ 4፥13 ሐዋ 6፥4 ) ለግል ሕይወታችን ጥንካሬ እና ፈውስ፡ ለአገልግሎታችን ፍሬአማነት ከቃሉ ጋር ያለን ጥብቅ ሕብረት በጣም ወሳኝ ነው።
እኛም ዛሬ ከራሳችን የሕይወት ለውጥ አልፈን ለሌሎች ልንተርፍ የምንችለው ልክ እንደ ዳዊት "ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባሪያህም ወደደው።"(መዝ 119:140) ማለት ስንችል ነው።
ጌታ ሆይ የቃልህን ረሃብ ጨምርልን! የቃልህ ሱሰኞች አድርገን! የቃልህን ፍች አብራልን! በቃልህ ውስጥ የተሰወረውን ምስጢር በመንፍስህ ግለጥልን! አሜን።
"የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።" (2ኛ ጢሞ 3:16-17)
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፥ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment