Sunday, May 10, 2015

በአፍህ አትፍጠን!

ዲቮሽን 242/07፥ ግንቦት፥ 2/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

በአፍህ አትፍጠን!

እግዚአብሔር በሰማይ፣ አንተ በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን (መክብብ፣ 5፡2)

አንዳንድ ጊዜ ካለብን ወቅታዊ ጫና፣ ወይም ካልተመለሱ ጸሎቶቻንን የተነሳ፣ ወይም ደግሞ፣ እግዚአብሔር በሥራ ላይ አይደለም፣ ወይም እግዚአብሔር ትቶኛል፣ ከሚል ከውስጥ ሙግታችን የተነሳ፣ ወይም ደግሞ፣ እናንተ ከምትጨምሩበት ከልዩ ልዩ ሰበቦች የተነሳ፣ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም፣ እግዚአብሔርን ማቃለል፣ ይቀናናል።

የእግዚአብሔር ሀሳብ ግን ፈጽሞ የማይመረመር ነው፤ እንዴት እንደሚሠራም የሚያውቅ እሱ ራሱ ብቻ ነው። በጠበቅነው ጊዜ እና መንገድ፣ ወይም በለመድነው አሠራር እራሱን ላይገልጥ ይችላል። ለአንዱ በመጣበት መንገድ ለሌላው ላይመጣ ይችላል። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን፣ እግዚአብሔር፣ ሰዎችን ሰዎችን ሲፈውስ፣ ሲመክር፣ ሲያድንና፣ ሲታደግ፣ አንድ መንገድ ብቻ አልተጠቀመም።

እነዚህ የምናልፋባቸው መንገዶች ግን ያለ ነገር አይሆኑም፤ እግዚአብሔር ያያቸዋል። ዋናው ቁምነገሩ እኛ ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር ተስማምተን የመኖራችን ምስጢር ነው። እግዚአብሔር፣ ለእኛ ለልጆቹ ያለው ዕቅድ ምንጊዜም መልካም መሆኑን፣ ከእኛ ይበልጥ ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ ስለሚያውቅ፣ ወደ በረከታችንን እና ወደ ተነገረልን ነገር እንዳንደርስ ዋናው የሚጠቀምበት መንገድ አንደበታችንን ነው።

ለዚህም ነው፣ በመክብብ፣ 5፡2 እግዚአብሔር በሰማይ፣ አንተ በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፣ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፣ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ይሁን። በማለት መንፈስ ቅዱስ የሚመክረን።
ስለዚህ ወገኖቼ፣ በአንደበታችን አንፍጠን። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ወደ እያንዳንዳችን ጉዳይ በራሱ መንገድ ይመጣል፤ አይቀርም ይመጣል።

አብ አባት ሆይ፣ ሆድ ሲብሰንና ግራ ሲገባን፣ በአንተ ላይ ብዙ የሥንፍና ቃላት የተናገርንባቸው ዘመኖች ብዙ ናቸው። በዚህም፣ አንተንም ቅር አሰኝተን፣ ሰይጣንንም ደስ እያሰኘን፣ እንዳለ ያልተረዳንባቸው ወቅቶች ብዙ ናቸው። እባክህ፣ ዛሬ፣ አሁን፣ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይቅር በለን። ማረን። ለአፋችን እና ለመንፈሳችን አርነት ሰጥተን በአንተ ላይ፣

እንደወደድን በተናገርንባቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ዛሬ፣ እኔንም ሆነ ወገኖቼን ይቅር በል። እስከዛሬም ስለተሸከምከንና፣ እንዴት እንደምትሠራም፣ እንዴት እንደምታድንም፣ አንተ ራስህ ስለምታውቅ ተመስገን። ሰምተህኛልና ተባረክ።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክ እና ሼር ያድርጉ።

No comments:

Post a Comment