Thursday, May 28, 2015

ለሱ እንለይ !



ዲቮሽን 260/07 ሓሙስ ግንቦት 20/07
( በወ/ ጌታሁን ሓለፎም )

ለሱ እንለይ

እንግዲህ ወዳጆች ሆይ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ስጋን እና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” 2 ቆሮ 71

ትዝ ይለኛል ከረጅም አመት በፊት በመንገድ ላይ አግኝተውኝ ስለጌታ የመሰከሩልኝ ጴንጤዎች ሊጎበኙኝ ወደቤቴ መጥተው ሳሉ፤ እኔና ጓደኞቼ ፍራሽ ሞልተን ጫት ጎርሰን ቁጭ ብለን ፊልም እንመለከት ነበር፡፡ ያኔ ስንመለከተው የነበረው ፊልም በውነቱ ከሆነ በዚህ ዘመን ባለን አማኞች የፊልም ግንዛቤ እና ትርጉም አንጻር የኃጢያቱ ውፍረት ቢለካ ኖርማል ሊባል የሚችል አይነት የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን በዛን ዘመን ሊጎበኙኝ የመጡትን ጴንጤዎች ሰላም ነስቶአችው ነበር፡፡

ወደ ቴሌቪዥኑ መስታዎት ድንገት ዘወር ባሉ ቁጥር ከሚያዩት ትርኢት የተነሳ ደንግጠው በየሱስ ስም እያሉ ይገስጹ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ በኔ ቤት ተገኝተው እንዲህ አይነቱን ፊልም ለአፍታም ማየታቸው አውኮአቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ከዚህም የተነሳ እኔና ጓደኞቼ እንገረም ነበር ፍጹም እንፈራቸው እናከብራቸው ነበር፤ እንደ ልዩ ሰዎች እናያቸው ነበር በኑሮአቸው እና ባካሔዳችው እንቀናባችው ነበር፡፡ የኛን አወጣጥ እና አገባብ እያየን እንኮነን ነበር፡፡ በእውነት ውስጣችን ይከሰስ ነበር፡፡

ይገርማል ዛሬ ዛሬ አይኖቻችን ኃጥያትን ለማየት አይሳቀቁም፤ ክፋትን ለመስማት ጆሮዎቻችን ግድ የላቸውም፤ እንዲያውም ድሮ ድሮ መጠሪያቸው ከኃጢያት ተርታ የነበሩ ድርጊቶች ዛሬ ከየ እለት ውሎአችን ጋር ተስማምተው አብረውን የሚኖሩና የምንሳሳላችው የምንንከባከባቸው ሊሆኑም ይችላሉ፤

እንደ እሾህ ጥቃቅን የነበሩ እጆቻችንን እና እግሮቻችንን እንዳይወጉን እንጠነቀቅ የነበርን ኃጢያቶች ዛሬ አድገው እና ተልቀው ምርኩዞቻችን አድርገናቸው እና ጨብጠናቸው ጌጦቻችን ሆነው፤ አብረውን ከኛ ጋራ እየኖሩ ናቸው፡፡ እኛም አውቀንም ይሁን ሳናውቅ በቸልተኝነትም ይሁን ነገሩን አቅልሎ በማየት ብዙ የኃጢያት ልምምዶች ውስጥ አለን፡፡ አለማውያን የሚያደርጉት ክርስቲያን የማያደርገው እየተባለ ይለዩ የነበሩ የኃጢያት ደረጃዎች ዛሬ ዛሬ ለመለየት እስኪአስችግሩ ድረስ ተመሳስለዋል፡፡

በየጊዜው ጆሮን ጭው የሚያደርጉና መንፈስን የሚያውኩ ባለም ላይ ለሚከሰቱ የኃጢያት እና የክፋት ስራዎች ብዙም ስፍራና ቦታ አንሰጣቸውም እንደማንኛውም ሰው ጉድ ብለን ከማለፍ ውጭ ለጸሎት እና ለምልጃ ለመቃተት አንዘጋጅም

ብዙዎቻችን አስተውለን እንደሆነ አላውቅም ሰሞኑን አለማችን አንድ አስደንጋጭ ነገረን አስተናግዳለች ይሔውም በአየርላንድ የተከናወነው በህዝብ ድምፅ 62 % ብልጭ አግኝቶ የጸደቀው የሆሞ ሴክሹዋል ጋብቻ ጉዳይ ነው፡፡ በአለም የመጀመሪያዋ ሆሞ ሴክሹዋልን ጋብቻ በህዝብ ድምጽ ብልጫ ያጸደቀች አገር እየተባለች እየተደነቀች ነው፡፡ በመላው አለም ያሉ ሰዶማውያን በአየርላንድ የተከናወነው ድል የወደፊት ብሩህ ተስፋ ፈር ቀዳጅ ነው እያሉ በያደባባዩ ደስታቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡

ለመሆኑ በኛስ ልብ ውስጥ የተፈጠረው ስሜት ምን ይሆን ? ነገሩ ምን ያህል ክብደት ሰጥተነዋል እንደመንፈሳዊያን ምን አይነት እርምጃ እየወሰድን ነው? ወገኖች እንጸልይ በየ አጥቢያ ቤተክርስቲያናችን በአለም ላይ የሚከናወነውን ወቅታዊ ሁኔታ እየተከታተልን ለመፍትሔ በጌታ ፊት እንውደቅ፡፡ እኛም ያለንን እንጠብቅ ከአለም ጋር የተቀላቀለ የኑሮ እስታይል እንዳንለማመድ እንጠንቀቅ

ዛሬም በእግዚአብሔር ፍርሃት ወስጥ ሆነን ከአለም የኃጢያት ስርአት ወጥተን ቀጥተኛና ጽድቅ ያለበትን የጌታን መንገድ ይዘን እንደ ቀደምት አባቶችቻችን ክርስትናን እንሩጥ! ስጋችንን እየጎሰምን ለምኞታችን ሳንገዛ ለጌታ ኖረን እንለፍ፡፡ ይህ እንዲበዛልን የጌታ ፀጋ ክሁላችን ጋር ይሁን አሚን

ይህ ትምህርት ለሌሎች ይጠቅማል ብለው ካሰቡ ሼር እና ላይክ በማድረግ ጌታን ያገልግሉ!

No comments:

Post a Comment