Wednesday, May 27, 2015

መካሪዬ!!!!!



ዲቮሽን 258/07 ማክሰኞ፣ ግንቦት 18/07
(
በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

መካሪዬ!!!!!

የመከረኝ እግዚአብሔርን እባርካለሁ መዝ 167

በህይወት ጉዞ ላይ በሚያጋጥሙን ውጣ ውረዶች እና በእለት እለት እንቅስቃሴያችን ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ የሚያጋቡን ሁኔታዎች ይኖራሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ ለኛ ጥሩ የሚመስለንና በእግዚአብሔር ዓይን ግን መልካም ያልሆነን ውሳኔ ለመወሰን ልንገደድ እንችላለን። ሁኔታዎች ሲጠሙብንና ሲከብዱብን በፊታችን ያገኘነውን ነገር ይዘን ልንሔድ እንችላለን። ወይም ደግሞ፣ አንደበታችንን ልናስትና እግዚአብሔርን ልናማርር እንችላለን። ወይም ደግሞ መውጫ ከሌለው አስጨናቂ ጉድጓድ ውስጥም ልንገባ እንችላለን። አንዳንዴ ከባድ ሁኔታዎች እና ድንጋጤዎች ሲከቡን የተለያዩ ዓይነት መላ ምቶችን እንሰነዝራለን።

በዚህ ወቅት ግን ቆም ብለን እግዚአብሔርን ልናስብ ይገባል። እግዚአብሔር ምን ይለኛል? እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ላይ ያለው ሐሳብ ምንድነው? እግዚአብሔር ምን ብሎኛል? እና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ወደ መጽሐፍ ቅዱሳችን እና ወደ ጸሎት መመለስ አለብን። ያን ጊዜ፣ ትክክለኛ እና እንከን የሌለው ምክር፣ አዋጭ እና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ከመንፈስ ቅዱስ እናገኛለን።

ለዚህም ነው ዳዊት ሲናገር፡የሚመከረኝ እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ በሌሊት እንኳን ልቤ ቀናውን ያመላክተኛል መዝ 16 7 ሲል የሚናገረው።

በሌሊቶቻችን ላይ፣ በጨለማዎቻችን ላይ፣ በድንግዝግዞቻችን ላይ፣ እግዚአብሔር ምንም ሳይደነግጥና የኛም ጨለማና ድንግዝግዝ ሳያስፈራው፣ ተራራ የሆነብን ነገር ሳያስበረግገው፣ ትክክለኛውን ምክር ይመክረናል። በእግዚአብሔር ምክር ውስጥ ደግሞ የዘላለም እቅዱ፣ ቸርነቱና ፍቅሩ አለ፤ እግዚአብሔር በምክር ግሩም ነውና!

አባት ሆይ፣ ከስሜታዊነት የተነሳ ድንገተኛ ምክርን ከጠላት እንዳንሰማ እስከዛሬ ድረስ ጠብቀህናልና ተባረክ። ለቀሪው ዘመናችንም የጠላታችን ምክር በኢየሱስ ውድ ስም ከንቱ ይሁንና፣ ያንተ ምክር በልባችን ላይ ተደላድሎ ይቀመጥ። መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ስትመክረን፣ ስታስተምረን የምናደምጥበትን መንፈሳዊ ጆሮዎቻችን ዛሬ ይከፈቱ። ሰምተህኛልና ተባረክ፤ በኢየሱስ ስም አሜን።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ።

No comments:

Post a Comment