ዲቮሽን 257/07፥ ሰኞ፣ ግንቦት 17/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ትወደኛለህን???
ወዶኛልና አዳነኝ። መዝ 18፡ 19 አንዳንዴ፣ ፈጽሞ በማይመስል ከባድ መንገድ ላይ ስንመላለስ፣ እንደ አማኝ ቶሎ የሚመጣልን ወደ ላይ ወደ ሰማይ በማየት፣ እግዚአብሔርን ትወደኛለህን? እያልን መጠየቅ ነው። ታየኛህለን? ታደምጠኛለህን? ትራራልኛለህን? ታዝንልኛህን? አለህን? እያልን እንጠይቀዋለን። ጥያቄያችን ጤናማና ትክክለኛ ነው። ታዲያ ወደማን እንሔዳን!
ዛሬ አንድ ነገር እነግራችኋለሁ፣ እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ። እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ አለ። እግዚአብሔር እርስቱን ለጠላት ማላገጫ አሳልፎ አይሰጥም።
ጠላቶቻችን፣ “እሰይ! አገኘናቸው፣ እስኪ አምላካቸው ይምጣና ያድናቸው! የታለ አምላካቸው?” ብለው እንዲያፌዙብንንና እንዲሳለቁብን አያደርገንም።
እርግጠኛ ሆኜ እነግራችኋለሁ፣ እግዚአብሔር ወደ እያንዳንዳችን ነገር ላይ ይመጣል። ያድነናል፤ ይታደገናል፤ ለክብሩ ያቆመናል። በክብር፣ በሞገስ ይመጣል።
ጠላቶቻችን እርግጥ ነው ብዙዎች ናቸው፤ በዓይነትም በብዛትም ስፍር ቁጥር የላቸውም። ከበውናል። ግን፣ እነሱ አእላፋት ቢሆኑም፣ አንድ እግዚአብሔር ብቻውን ድምጥማጣቸውን ያጠፋቸዋል። በሐይሉ ስልጣን፣ ባስጨነቁን ነገሮች ሁሉ ላይ ዛሬ እግዚአብሔር ይመጣል፣ ተራራ የሆኑብን ነገሮች ሁሉ ይናዳሉ፣ ከብርቱዎች ጠላቶቻችን ዛሬ እግዚአብሔር ያድነናል።
ምስጢሩ ደግሞ፣ አንድ ነው፣ ወ----ዶ----ና-----ል።
መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ስለመጣው ቃልህ አመሰግንኃለሁ። በእርግጥ ወደህናል፣ አድነህንማልም። ገና ደግሞ እጃችንን በአፋችን ላይ እስክንጭን ድረስ፣ ታድነናለህና ተመስገን። ስለማያረጀው ቃልህ፣ ስለማይደክመው ጉልበትህ፣ ስለማይመረመረው ፍቅርህ አብዝቼ–አብዝቼ አመሰግንሃለሁ። ግሩም የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፣ ተመስገን።
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል። እንግዲያውስ እባክዎ ላይክ እና ሼር ያድርጉ? ጌታ ይባርክዎ።
No comments:
Post a Comment