ዲቮሽን 233/07 አርብ፥ ሚያዚያ 23/07
(በወንድም አበባዬ ቢተው)
(በወንድም አበባዬ ቢተው)
የዕረፍት ሕይወት
"እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ" (ዕብ 4፥9-11)፡፡
እግዚአብሄር ዕረፍት በሌለበት ከንቱ እና የመቅበዝበዝ ሕይወት እንድንኖር አይወድም። አዕምሮን ሁሉ በሚያልፍ ሰላም እና በመንፈስ ቅዱስ በሆነ ደስታ እንጅ (ፊልጵ 4፥7፥ ሮሜ 14፥17)፡፡ ይህም በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ እና በየጊዜው ከሚለዋወጠው ዓለም ጋር አብሮ የሚለዋወጥ ሕይወት ሳይሆን፥ ከኤልሻዳዩ እግዚአብሄር የወጣ አሸናፊ ሕይወት ነው።
የዕረፍት ሕይወት ከሁኔታዎች ከፍ እና ዝቅ ማለት ጋር ፈፅሞ አይያያዝም። የዕረፍት ሕይወት በሀብት አይገኝም። የዕረፍት ሕይወት በገንዘብ አይገኝም። የዕረፍት ሕይወት በዕውቀት ብዛት አይገኝም። የዕረፍት ሕይወት አገር እና የስራ ቦታ በመቀየር አይገኝም።
በአጠቃላይ የዕረፍት ሕይወት በተለያዩ ዉጫዊ ነገሮች መሟላት አይገኝም። የዕረፍት ሕይወት ምንጭ እግዚአብሄር ነው። መንገዱም እርሱን ማመን እና መታዘዝ ነው። በየደቂቃው ከውስጥም ከውጭም ክፉ እና አስፈሪ ወሬ በሚሰማበት በዚህ ክፉ ዘመን ፀንተን የምንኖረው
ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን የዘላለም የዕረፍት ሕይወት አጥብቀን ስንይዝ ነው።
ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን የዘላለም የዕረፍት ሕይወት አጥብቀን ስንይዝ ነው።
እግዚአብሄር አልተለወጠም፥ አይለወጥምም። እንዲሁ የሰጠን ሕይወትም የሚለወጥ እና የሚሸነፍ ተራ ሕይወት አይደለም። ይልቁንም አሸንፎ የሚወጣ ድል ነሺ ነው።
ስለዚህ ይህንን ዲቮሽን የምታነቡ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ምንም እንኳ ጊዜው ክፉ ቢሆንም ከእግዚአብሄር የተቀበልነው ሕይወት በሰላሙ እና መልካሙ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአስፈሪውም ጊዜ በዕረፍት የሚያኖር፥ የሚያሻግር እንደሆነ ላሳሰባችሁ እወዳለሁ።
የተቀበልነውን የዕረፍት ሕይወት በዕምነት እንለማመድ። በንስሐ መንገዳችንን በማስተካከል፥ በፀሎት፥ በምልጃ እና በምስጋና እንመላለስ።
ወደ ሙሉ ዕረፍት እና ሰላም የምንገባበት ጊዜ ቀርቧልና! "ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና" (2 ተሰ 1:6-7)፡፡
No comments:
Post a Comment