ዲቮሽን 243/07፥ ግንቦት፥ 3/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
አለበሱት!
የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ (ዘፍ 9፡ 23)
ኖህ በዘመኑ ሁሉ ጻድቅ እና ፍጹም የነበረና አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ፣ የተባረከ ሰው ነበር። እግዚአብሔር እንዳዘዘው የሚያደርግ፣ ለሰው ሁሉ ሞኝነት የሚመስልን ነገር የሚያደረርግ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የልብ አድርስ የነበረ ሰው ነው። በዚያ ግልሙትና በበዛበት ዘመን ተፈልጎ የተገኘ ብቸኛው ጻድቅ ሰው። እግዚአብሔር በመታዘዝ መቶ ዓመት ሙሉ መርከብ ሲሰራ የቆየ፣ ታማኝ!
የሆኖ ሆኖ ግን አንድ ቀን፣ ሁሉም ነገር ካለፈ በኋላ አጉል እና አሳፋሪ ነገር ውስጥ ተገኘ፤ ወይን ጠጣና ሰከረ። በቃ ሰከረ! ምናልባትም እራሱን እስኪስት ድረስ ጥምብዝ ብሎ ሰክሮ ይሆናል። በዚህ ጊዜ፣ ከልጆቹ አንዱ የሆነው ካም፣ የአባቱን ራቁትነት አየ፤ ወጥቶም ለወንድሞቹም ነገራቸው። ሴምና ያፌት ግን አስተዋዮች ነበሩና፣ ያንን ታላቅ እግዚአብሔር ሰው የሆነውን የአባታቸውን እራቁትነት ሊያዩ አልደፈሩም። በዚህም የተነሳ፣ ፊታቸውን ወደ ኋላ አዙረው፣ ገመናውን ሳያዩ፣ የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ።
በኛም ዘመን ብዙ እንደ ኖህ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ነበሩ። ግን ስጋ ለባሽ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ከስንት አንዴ በኃጢያት ወድቀው የተገኙ። ባላሰቡት እና እንገባበታለን ብለው አልመው በማያውቁት ውርደት ውስጥ የተዘፈቁ ብዙ የእግዚአብሔር ታማኝ ልጆች ነበሩ፣ ዛሬም አሉ?
የኛ ምላሽ ምን ሆኖ ይሆን?
ካም እንዳደረገው፣ እጅ ከፍንጅ ተይዛችኋል፣ ብለን ውለታቸውን ሁሉ ረስተን፣ ገመናቸውን አደባባይ ለማውጣት ሮጠን ይሆን? ስንት ሰባኪዎች፣ ነብያት፣ መምህራን እና ዘማሪዎች፣ እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ እና ባለቸው ዓቅም ሁሉ ለጌታ ታማኝ የሆኑትን ወገኖቻችንን፣ በድካማቸው ሰዓት አበረታናቸው? በራቁትነታቸው ሰዓት አለበስናቸው? በሐጢያት ወድቀው ሲገኙ ጸለይንላቸው? ወይስ፣ አዋረድናቸው? ወይስ፣ ከጎናቸው በመቆም አይዟችሁ እያልን፣ ተመልሰው እንዲቆሙ እና እንደገና በጌታ ቤት እንዲኖሩ አደረግናቸው? ምናልባት አስመርረናቸው፣ አባረናቸው፣ ከሰይጣን ጋር ተባብረን በቁስላቸው ላይ ነዳጅ ጨምረን አሳደናቸው ከሆነ፣ በእርግጥ እርም አለብን። መልሱን ለእያንዳንዳችሁ እተወዋለሁ።
አባት ሆይ፣ አንተ መልካምና ጻድቅ የሆንክ፣ በሥራህም እውነተኛ እና የዘላለም ወዳጅ ነህና፣ የወንድምና እህቶቻችንን ገመና ባጋለጥንበት ነገር ሁሉ ይቅር በለን። ማረን። እነሱንም በበለጠ ክብር እና ሞገስ መልስልን። ለወደፊቱም፣ ለሚያገለግሉን ወገኖች ሁሉ፣ በድካማቸው እና በችግራቸው ጊዜ ከጎናቸው የምንቆም አጋሮች አድርገን አድርገን።
በኢየሱስ ስም አሜን!!!!
No comments:
Post a Comment