ዲቮሽን 211/07፥ ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
'ክራ-ላይሶ' – ማረን አቤቱ!
…መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል …. ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም (ዮሐ 10፡11፤ 12፡25)
'ክራ-ላይሶ' (ኪሪዬ ኤሊይሶን) – ማረን፣ አቤቱ ማረን!
ፍርዳችንን የወሰድኸው፣ መስቀልን የተሸከምኸው፣ ከሞትም ኃይል ያወጣኸን፣ ኦ የሞትህልን አድነን፣
ስማልን ጸሎታችንን፡፡ 'ክራ-ላይሶ'!
ታላቅ ሥራህ ተፈጸመ፣ ፍርድ ምሕረቱን አተመ፣ የፍርድ አምላክ ለኃጢአት፣ ከሰጠ በቂውን ቅጣት፣
መሐሪ አምላክ ልጆቹ፣ አደረገን በምሕረቱ፡፡ 'ክራ-ላይሶ'!
እኛ ፍጹም ደካሞች ነን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ አበርታን፣ በምሕረት እጅህ ደግፈን፣ በቅዱስ መንፈስህ
እርዳን፣ ያምላክ ልጆች ያደረግኸን፣ የሱስ ክርስቶስ ሆይ ተመስገን፡፡ 'ክራ-ላይሶ'!
አትራቅብን የሱስ ሆይ፣ ሁልጊዜ ከእኛ ዘንድ ቆይ፣ በፈተና አበርትተህ፣ በትግልም አጠንክረህ፣ በሕይወትም በሞትም ጻር፣
በደምህ ኃይል ሁን ከኛ ጋር(ስብሀት ለአምላክ ፷፩)፡፡
አቤቱ የፍቅርና የምሕረት ጌታ፣ ኪሪዬ ኤሊይሶን – ማረን አቤቱ ማረን!!
አንተ ነፍስህን ለእኛ ለበጎችህ ያኖርኸው፣ 'ክራ-ላይሶ'! አንተ መልካም
እረኛ፣ 'ክራ-ላይሶ'! ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውምና፣ 'ክራ-ላይሶ'! ለዚህ ፍቅር ምላሽ፣ ነፍሳችንን ለአንተ መስጠት አልቻልንምና፣ 'ክራ-ላይሶ'!
አንተ የምሕረት አምላክ፣ 'ክራ-ላይሶ'! አንተ
የኛን በደልና ኃጢአት ተሸክመህ በመስቀል ላይ ሞተሃልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! እንዲህ ያለ መውድድ፣ እንዲህ ያለ ፍቅር ለእኛ ለኃጢአተኞች
አሳይተኻኛል፣ 'ክራ-ላይሶ'!
አንተ የፍቅር አምላክ፣ 'ክራ-ላይሶ'! የበደሉንና የጎዱንን ሁሉ ይቅር ማለት አቅቶናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! ወንድሞች
በኅብረት መቀመጥ አቅቶናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! ነፍሳችንን ለአንተ አሳልፈን ከመስጠት ይልቅ ነፍሳችንን ወድደናታልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! ራሳችንን ለአንተ አሳልፈን ከመስጠት
ይልቅ፣ ራሳችንን ወድደናልና፣ ኪሪዬ ኤሊይሶን!
አቤቱ የፍቅርና የምሕረት ጌታ፣ ኪሪዬ ኤሊይሶን – ማረን አቤቱ ማረን!!
መጋቢያን፣ ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ አስተማሪዎች፣ ወንጌላዊያን፣ ምዕመን አገልጋዩ ሁሉ ራስ ወዳዶች
ሆነን ተገኝተናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! እርስ በርሳችን ከመዋደድ ይልቅ፣ እርስ በርሳችን
በመገፋፋት አጥፍተናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! በምንሠራው ሥራ ለወንጌል እንቅፋት፣ ለመንጋው ስብራት ሆነናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'!
አንዱ የሌላውን በር በመዝጋት፣ አንዳችን የሌላችን ራዕይ በማሰናከል በድለናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'! በጥላቻ ሥራ እየተሠማራን፣
በጥላቻ መንገድ ገብተን እየሄድን እኛ ወድቀን ሌሎችን በመጣል አጥፍተናልና፣ 'ክራ-ላይሶ'!
'ክራ-ላይሶ'! የፍቅርና የምሕረት ጌታ፣ ኪሪዬ ኤሊይሶን – ማረኝ አቤቱ ፈጣሪ፣ እኔም
አውቃለሁ በደሌን!!
ኪሪዬ ኤሊይሶን! ለሀ ሴንተማራይ!
ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment