Friday, April 10, 2015

'ተጠማሁ' – 'ተፈጸመ'!



ዲቮሽን 212/07 አርብ፣ ሚያዝያ 2/07 /
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


'ተጠማሁ''ተፈጸመ'!

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ … ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ(ዮሐ 19፡28-30)

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው በሕግና በነቢያት የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ለመፈጸም ነው፡፡ በዚያ በመስቀል ላይ ጣርና ስቃይ ላይ እንኳ ሆኖ፣ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ያሳይ የነበረውን ማመን እንችላለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በመዝ 69፡21 ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ተብሎ ስለእርሱ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ፣ ‹‹ተጠማሁ›› አለ። በመስቀል ላይ በነፍስ ጣር የሚሰቃይ ሰው እንዲጠጣና ደንዝዞ ሕመሙን እንዲረሳ ይሰጥ የነበረው ከርቤ የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ በሒሶጵ ቅጠል አቀመሱት፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕመምና ጣሩን እንደወረደ ተቀብሎ መሞት እንጂ፣ በማደንዘዣ ደንዝዞ ሕመሙን ረስቶ መሞት አልፈለገምና፣ ያቀረቡለትን ሕመም አደንዛዥ ወይን አልጠጣውም(ማር 15፡23)፡፡ ነገር ግን ለሕጉ መፈጸም ያህል ብቻ ቀምሶ ትቶታል፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድነትና ለመጻሕፍቱ መፈጸም ሲል፣ የራሱን ጣርና ስቃይ ከማስታገስ፣ ከማደንዘዝና ከመርሳት ይልቅ፣ ጣርና ስቃዩን እንደወረደ ተቀብሎ ለመሞት ምርጫው አደረገ፡፡ ይህም ፍቅር ግድ ብሎት ነው! የሰው ልጆችን ኃጢአትና፣ ኃጢአት ያስከተለውን መርገም ሁሉ እንደወረደ ተሸክሞ በመስቀል ላይ ሞተ! በዚህም የተጻፈው ሁሉ ተፈጸመ!

ወገኖች ሆይ፣ ጌታችን በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ኃጢአት በመሞቱ፣ የተጻፈው ሁሉ መፈጸሙን አውጇል! ይህም ማለት በሰው ልጆች ላይ የነገሰው ኃጢአት ተገረሰሰ፣ መርገም ተወሰደ፣ ዕዳ ተከፈለ፣ ፍርድ ተለወጠ…ማለት ነው!

ታውቃላችሁ፣ በመስቀሉ ላይ የታወጀው አዋጅ ‹‹ተፈጸመ›› የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት በቤዛነት ሥራ ውስጥ፣ ኃጢአት ያስከተለው ማናቸውም መዘዝ ተደምስሷል! በቤዛነት ሥራ ውስጥ፣ ኃጢአት ያስከተለው የበሽታ፣ የሕመምና መንፈሳዊ ሞት ዘመን ተፈጸመ!

ታውቃላችሁ፣ ጌታን ስንቀበል በነፍሳችን ብቻ ሳይሆን በሥጋችንና በመንፈሳችንም ጭምር ድነት ተፈጽሟል! የድነት ትርጉሙ በመስቀሉ ላይ በተሠራው የቤዛነት ሥራ፣ በሰው ልጆች ላይ ነግሦ የነበረው የዲያብሎስን ሥራ ሁሉ ፈረሰ ማለት ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ድነት መንፈሳችንን ብቻ ሳይሆን የአካላችንንና የአእምሮአችንን ነጻ መውጣት አብሮ ይጨምራል! ይህን እውን ለማድረግ፣ ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ የተቀበለው ስቃይ ፍጻሜ አግኝቷል! በመስቀሉ ላይ ‹‹ተፈጸመ›› ተብሎ የታወጀው አዋጅ ይህንን ይመስላል!

 ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment