Wednesday, April 8, 2015

ሞኝነትና - የእግዚአብሔር ኃይል!

ዲቮሽን 210/07 ረቡዕ መጋቢት 30/07 /
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ሞኝነትና - የእግዚአብሔር ኃይል!

የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና (1 ቆሮ 118)

በእንጨት ላይ ተስቅሎ መሞት የእርግማን ሞት ነው፡፡ ይህ ዓይነት ሞት የመጨረሻው ክፉ ወንጀለኛ የሚቀጣበት ሞት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ታዲያ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞቱ በዚህ በሕግ የተረገመና በማኅበረሰቡም የተወገዘ ሰው ተደርጎ እንዲቆጠር አድርጎታል፡፡ ይህን ዓይነት ሞት የሞተን ሰው መልካምነት መናገር፥ የዚህ ዓይነቱን ሞት የሞተን ሰው ገድል መተረክ እጅግ አሳፋሪና ሞኝነት ነበር፡፡

ወገኖች ሆይ፥ በእንጨት ተሰቅሎ መሞት እጅግ አሳፋሪ ሞት ነው! በእንጨት ተሰቅሎ የሞተን ሰው መስበክ ደግሞ ከአሳፋሪነትም አልፎ ሞኝነት ነው! ይህ ግን ለማያምኑበት ብቻ ነው! የሚያምኑበት ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው!

ታውቃላችሁ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ይህን አሳፋሪ ነገር፥ ሞኝነት የሚመስለውን ነገር ሳያፍሩበት የተሰቀለውን ክርስቶስን በድፍረት ሰበኩ! በዚህ ስብከታቸው አምነው የሚድኑ የእግዚአብሔርን ኃይል ሲቀበሉ፥ የማያምኑ ደግሞ ይሳለቁበታል!

ታውቃላችሁ፥ የመስቀሉ ቃል ስብከት በሰው የተናቀ የደካሞች ሥራ፥ ተራ ነገርና ምናምንቴ ነገር ተደርጎ ሲወሰድ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እጅግ የተመረጠ፥ የጥበብ ሁሉ ቁንጮ፥ የኃይል ሁሉ ቁንጮ የሚያስመካ ነገር ነው!

ወገኖች ሆይ፥ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንስበክ! ወግኖች ሆይ፥ ስብከታችን እኛን ያማከለ፥ ወግና ልማዳችንን ያማከለ ሳይሆን የመስቀሉን ሥራ ያማከለ ይሁን!

ወገኖች ሆይ፥ መስቀሉን ለመስበክ ፈጽሞ አንፈር! ለሚድኑት ሕይወት፥ በጨለማ ላሉ ብርሃን፥ ላዘኑ መጽናናትየሚሰጠውን ይህንን የመስቀሉን ቃል ሳናፍርበትና ሳንሸማቀቅበት ልንሰብከው ይገባል!


ትምህርቱ ጠቅሞታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment