Saturday, April 25, 2015

መልካሙ የመታደሻ ዕድል!

ዲቮሽን 227/07 ቅዳሜ፣ ሚያዚያ 17/07
(በዶ/ በቀለ ብርሃኑ)

መልካሙ የመታደሻ ዕድል!

እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም”(ኢሳ 4031)፡፡

ሕይወት ትሠምር ዘንድ፣ ሰው ከአምላኩ ምሕረትን፣ ምሪትን፣ ኃይልን፣ ምክርን፣ ጥበብን ወዘተ ሊቀበል ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ ሕይወት መደዴ፥ እንዲሁም ፍሬ አልባ ነው የሚሆነው፡፡

መኪና ወደ ጋራዥ ለእድሳት እንደሚወሰድ ሁሉ፣ ወደ ጸጋ ዙፋኑ በመምጣት ምሕረቱንና ጸጋውን ልንቀበል ያስፈልገናል፤ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሳናቋርጥ፡፡

የእግዚአብሔር ቃልውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ” (ኢሳ 12:3) የሚለንም ለዚህ ነው፡፡ ታዲያ ወደ ምንጩ መጥተን የመቅዳቱ ኀላፊነት የኛ እንደ ሆነ ክፍሉ በግልጽ ያመለክተናል፡፡

አዎ! በጓዳችን የምንከፍለው የዕለት ተዕለት መስዋዕትነት ይኖራል፤ እስከ ሕይወት ማብቂያ ዘመን ሳያቋርጥ የሚቀጥል የዕለት ተዕለት ተግባር! ኢየሱስ በእርሱ ፊት የምናሳልፋቸው ጊዜያት ወርቃማና የፍሬ ጊዜያት እንደሆኑ ሲናገርማርታ፣ ማርታ፣ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፣ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” (ሉቃስ 1040-41) ብሏል፡፡

ይኼ ክፍል በሚገባ ወደ ውስጣችን ጠልቆ ቢገባ ከብዙ መቅበዝበዝ ያድነናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በግሌ አዘውትሬ የማስበውና የማሰላስለው ክፍል ነው፡፡
ፈዋሽነቱንና ረድኤቱን አምነን ወደ ጌታ ሕልውና ስንመጣ፣ የመጀመሪያው በረከታችን ራሳችንን የማየት ጊዜን እናገኛለን፡፡ በሕይወታችን ያላስተዋላቸውን መሠረታዊ ችግሮች የመረዳትና የመገንዘብም ዕድል ይኖረናል፡፡

የእግዚአብሔር ቃልየተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፣ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ” (መዝ 908) እንደሚል፣ ከሕሊናችን የተሰወሩና ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶችን (እንዳሉም ያላሰብናቸውን) የማየት አጋጣሚው ይኖረናል፡፡

ውስጣችን ያሉ ችግሮችን አወቅን ማለት ደግሞ ገና መድሐኒቱን ሳንወስድ በግማሽ ተፈውሰናል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያማ አድርጉ ከሚለን የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ጋር ተስማምተን የታዘዝነው ስናደርግ፣ ፈውሳችን ሙሉ ነው የሚሆነው፡፡

በጌታ ፊት የምንሆንባቸው ጊዜያት የባከኑ እንደ ሆኑ በፍጹም ልናስብ አይገባም፤ እንዳውም ጥሩ የሕክምና ጊዜ፣ ጥሩ የመሠሪያ ጊዜ እንደ ሆነ እንጂ፡፡ ታዲያ በትሕትና የውስጣችንን ችግሮች ዘክዝከን፣ ነፍሳችን አፍስሰን፣ ከምር በሚፈስ እንባ ጥልቅ ንስሐዎችን ብንገባ፣ የሚመጣው መታደስ ቀላል አይሆንም፡፡ እንዲህ ዓይነት ጊዜዎች ሲበዙልን ነው፣ ለውጣችን የሚበዛው፤ እድገታችንም ብዥታ የማይኖረው፡፡

ራሳችንን ለመመርመር የሰከኑ የጥሞና ጊዜያትን ማመቻቸት አስተዋይነት ይመስለኛል፡፡ ጨክነን ግላዊ ፍተሻ(personal inventory) ማድረግና ከጌታ ጋር ለመሄድ መስማማት ጥበብ ሲሆን፣ ወደ ፈጣሪ ሕልውና እየመጣንኑና እንዋቀስ” (ኢሳ 118) በሚለው መንፈሳዊ መርሕ ሕይወታችን እንዳይጐበኝ ካላደረግን ምልልሳችን ችግር ያለው ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃልበመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፣ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል” (ኢሳ 3015) ብሎ የሚመክረን፡፡

አዎ! የጸጥታ ጊዜ፣ የእረፍት ጊዜ፣ የመመለስና የንስሐ ጊዜያት ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ያኔ ኃይላችን ይታደሳል፣ መንፈሳችን ይጠነክራል፡፡ ያኔ በአዲስ አተያይና ምልከታ፣ ተግዳሮቶቻችን የመግጠም ዕድሎችን እናገኛለን፡፡ መታከትም እስከ ወዲያኛው ይወገዳል፡፡ በታደሰ ሕይወትም የሚሠራው ሥራም ብዙ ፍሬን ያፈራል፡፡ ጌታ ይርዳን!


ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፥ ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment