Thursday, April 23, 2015

ዘመኑን በማወቅ – የሚገባንን እናደርጋለን!


ዲቮሽን 225/07 ሓሙስ ሚያዚያ 15 /07
(በወንድም ጌታሁን ሓለፎም)

ዘመኑን በማወቅ – የሚገባንን እናደርጋለን! 


"እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች 200 ነበሩ" (2 ዜና 1232)

እንደሚታወቀው ባለፉት ቅርብ ሳምንታት በደቡብ አፍሪካ ጎዳናዎች ላይ "የውጭ ሃገር ሰዎች ሓገራችንን ወረሩት፤ ኢኮኖሚያችንን ተቆጣጠሩት" በሚል ተልካሻ ሰበብ፣ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ በገጀራ ሲከተክቱ እና ቁዋጥኝ በሚያካክል ዲንጋይ ሲጨፈጭፉት፣ ወገኖቻችንን በእሳት ሲያጋዩ እና እንደጡዋፍ ሲያነዱት በሚዲያ አይተን ደነገጥን፡፡

በአምሳሉ ከተፈጠረ ከእግዚአብሔር ፍጡር ይደረጋል ተብሎ የማይጠበቅ እና የማይታሰብ አጋንንታዊ እና ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ ድንገት በሚዲያ አይተን፣ ድንጋጤያችን እና ሃዘናችን ሳይታገስ፣ በቅርቡ ደግሞ በሃይማኖት ሰበብ ሰይፍ ስለው መግደያ አዘጋጅተው የሰውን አናት በጥይት እየበሱና የወገኖቻችንን አንገት በካራ እያረዱ ለአምላካቸው የሚሟገቱ፣ አምላካቸውን ሊያድኑት፤ አምላካቸውን ከጥቃት ሊያስጥሉ በረሃ ለበረሃ ደም ለማፍሰስ የሚባዝኑ በተለያዩ የአውሬው መልእክተኞች በተከታታይ በወንድሞቻችን እና እህቶችሃችን ላይ ያደረሱትን የግፍ እልቂት የአለም ሚድያ ከዳር እስከ ዳር ሁሉ እስኪጠግበው ክፋታቸውን እና ጭከናቸውን አይተናል ልባችንም ደምቶአል፡፡

መቸም የሰው ልጅ በአለም ዙሪያ ክብሩን አጥቶ በተለያየ ምክኒያት እየሞተና እየተሰቃየ፤ እንደ ጉድፍ በየ ቦታው እየተጣለ በከፍተኛ ውርደት ውስጥ ያለ ቢሆንም፤ የሰሞኑ ሁኔታ ግን ለየት ይላል ዘግናኝም ነው ብዙዎቻችን እገሌ ሞተ ሲባል ስንሰማ የነበርን ሞት ምን እንደሚመስል ፊለፊት አየነው፡፡

ወገኖቼ ለመሆኑ በአለም ላይ ምን እየተከናወነ ነው? የአለም ሁኔታስ ወዴት እያመራ ነው?

በየቦታው እና በየስፍራው የሚሰማው የጣር ድምጽ ምንን ያመለክታል? ይሄ ሁሉ ግርግር እና ክፋት በአለማችን በተከታታይ መፈጠሩ፣ ገዳዩ የወደደውን እያደረገ የሚከለክለው መታጣቱ አለም የምትዳኝበት ስርአት አለመኖሩ ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ውጥንቅጥ ምንን ያመለክታል? እኛስ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ምን አይነት ሃሳብ በውስጣችን ተፈጥሮአል? እኔ ሲመስለኝ ምድረ ክርስቲያን አሁን የምንመዘንበት የምንፈተሽበት ወቅት ላይ ሁኔታው አምጥቶናል ብየ አስባለሁ፡፡

ቃላችን፤ ትምህርታችን፤ አገልግሎታችን ሚዛን ላይ የተንጠለጠለ ይመስለኛል፡፡ ሚድያው የወንድሞቻችንን ሞት ይዞ ቢመጣም የያንዳንዳችንን ሁኔታ እና አመለካከት ስለ ክርስትናችንም ያለንን አቁዋም እንዲሁም ይዘት እኩል አሳጥቶብናል፡፡

ያንዳንዶቻችን ሁኔታ፤ ድንጋጤና ተስፋ መቁረጣችን፤ ነገራችን እዚሁ ምድር ላይ እንዳለ፤ በላይ በሰማይ የዘላለም ህይዎት የሚባለው ጉዳይ ተስፋ ብቻ እንጅ እውነት እንዳልሆነ እስኪመስለን ድረስ የሞት ፍርሃት ጥላ በላያችን ላይ እንዳንዣበበብን ያስታውቃል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን ማድረግ እንደሚገባን ቆም ብለን ልናስብ ያስፈልጋል፡፡ ከደነገጠው ጋር መደንገጥ ከተሸበረው ጋር መሸበር የሚያስፈልገን አይመስለኝም እርግጥ ነው ከሚያዝኑት ጋር እናዝናለን፡፡ ነገር ግን የማጽናናት ቃል በዚህ ሰአት ከኛ ይፈለግብናል፡፡ ተስፋ የቆረጠውን አይዞህ ለምስኪኑ ተስፋ አለው ልንለው፤ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ያለውን አይዞህ ልንለው ያስፈልጋል፡፡ ከመቼውም ወቅት ይልቅ አሁን ወንጌልን በጨለማ እና በሞት ጥላ ቀንበር ውስጥ ላሉት የምንናገርበት ወቅት ላይ እንዳለን ግልጽ ይመስለኛል፡፡

እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ጊዜን ወቅትን፤ ሁኔታን የሚመረምሩ ጥበብ እና ማስተዋል የነበራቸው 200 የሚያክሉ የይሳኮር ልጆች ለዳዊት ነበሩት፤ እንደጊዜው እንደሁኔታው ወቅታዊውን ነገር ዳዊት እንዲያደርግ የሚመክሩ ጥበበኞች ሰዎች በዙሪያው ነበሩት፡፡ ዛሬም ቤተክርስቲያን በዚህ ወቅት ማድረግ የሚገባትን እንድታደርግ የሚመክሩ መሪዎች፤ ፓስተሮች፤ ነብያቶች እና ወንጌላውያኖች እንዲሁም አስተማሪወች ያስፈልጉዋታል፡፡
 
እባካችሁ ወገኖች ተስፋ እንደሌለው ሰው አንሁን የክርስቶስን የማዳን ወንጌል ይዘን ለፍጥረት ለማድረስ እንጨክን የኛ ወንጌል የሰላም ነው፤ ወንጌላችን የፍቅር ነው፤ ወንጌላችን የምህረት እና የርህራሄ እንዲሁም የይቅርታ ነው ይህን ደግሞ አላደረስንለትም እንጂ ሰላም እና እረፍት አጥቶ የሚባዝነው ፍጥረት ይፈልገዋል፡፡ ህይወት የሆነውን ክርስቶስ እየሱስን እንዲበዛላቸው ለሰዎች እንናገር፡፡ ለሟች ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ጌታ ይስጣቸው፡፡ ጌታ ይባርካችሁ !


ይህ መልእክት ባርኮታል? እንግዲያውስ ሌሎችም እንዲባረኩ ሼር እና ላይክ በማድረግ ጌታን ያገልግሉ፡፡

No comments:

Post a Comment