Sunday, April 26, 2015

ወደ እግዚአብሔር – እንመለስ!

ዲቮሽን 228/07፣ እሁድ ሚያዚያ 18/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ወደ እግዚአብሔር – እንመለስ!

መንገዳችንን እንመርምር፣ እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤ ዐምፀናል፣ ኃጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም። (ሰቆቃ 3፡40-42)።

ጌታ ተቆጥቷል! እግዚአብሔር ራሱን በቁጣ ከድኗል! እያሳደደንም ነው! ያለ ርህራሄ እየገደለን ነው! በየቦታው ያለ ርህራሄ እየሞትን ነው! በየቦታው እንጮኻለን እንጂ ጸሎታችን እየተሰማ አይደለም! በአሕዛብ መካከል እንደ አተላና ጥራጊ ተደርገናል! ጠላቶቻችን አፋቸውን በእኛ ላይ ከፍተው በጥፋትና በመፈራረስ በችግርና በሽብር እየተሰቃየን ነው!

ንስሐ ካልገባንና ከመንገዳችን ካልተመለስን፣ ካልታደስንም በስተቀር በመላው ምድሪቱ ላይ፣ በመላው ዓለምም ላይ አደጋ መጋረጡ ይቀጥላል፡፡ ምድር እስክትግማማ፣ በመላው ዓለም ላይም የእግዚአብሔር ቁጣ እስከ አፍንጫው ድረስ ሞልቶ እስኪወጣ ይደርሣል፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ በፍጹም ልባችን ወደ ጌታ እንጸልይ፡፡ ስንጸልይ ታዲያ፣ እጆቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓተ አምልኮአችንን ብቻ ሳይሆን፣ ልባችንንም ጭምር ወደ እግዚአብሔር እናንሣ፡፡

የክርስቲያኖች ስደትና ግድያ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል! ይህን አስመልክቶ የተደረገው ጥናትና በዚህ በፈረንጆቹ ዓመት ይፋ የተደረገው ውጤት እንደሚያመለክተው፣ በዓለም ዙሪያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች ስደትና ግድያ ደርሶባቸዋል፡፡


ወገኖች ሆይ፣ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣው ይህ የክርስቲያኖች ስደትና ግድያ፣ ክርስቲያን መሆን ወንጀል በሆነባቸው ሀገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ክርስትና ሕጋዊ እውቅና ባልተሰጣቸው ሀገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ወይንም አናሳ የክርስቲያን አማኞች በሚኖሩባቸው ሀገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ክርስትና የመንግሥታዊ ሐይማኖት በሆነባቸው ሀገሮችም ጭምር፣ አብላጫው የሀገሪቱ ዜጎች ክርስቲያኖች በሆኑባቸው ሀገሮችም ጭምር፣ በዴሞክራሲ ዕድገታቸው ጫፍ ላይ ደርሰዋል በሚባሉ ሀገሮችም ጭምር ነው!

ታውቃላችሁ፣ በዓለም ታሪክ፣ እንደዛሬው ጊዜ፣ ክርስቲያን በሚበዛበት ሀገር ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሲሰደዱና ሲገደሉ ታይቶም ተሰምቶ አይታወቅም!

በሰሜን ኮሪያ ከ700ሺ በላይ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ብቻ በእስር ቤት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በሶሪያ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በኢራቅ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በአረብ ኢሚሬቶች የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በፓክስታንና በአፍጋኒስታን የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በሜክሲኮና በኮሎምቢያ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ!

ወገኖች ሆይ፣

አፍሪካ የዘመናችን አደገኛ ጸረ-ክርስቲያን ምድር እየሆነች ነው! በሶማሊያ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በሱዳንና በኤርትራ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በሱዳንና በናይጄሪያ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! በኢትዮጵያና በኬንያ የተገደሉትንና የተሰደዱትን አስቡ! ከአሊኢትሐድ እስከ አይሲስ፣ ከአልቃይዳ እስከ ቦኮ ሐራም፣ ከኮሚኒዝም እስከ ሼይጣኒዝም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል!

ወገኖች ሆይ፣ ምድራችን በፍጥነት እየወደቀችና እየተደመሰሰችም ነው! በየዕለቱ በዜና መስኮቶች፣ ከሞት ዜና በቀር፣ ከስደት ዜና በቀር፣ ከአደጋና ከመቅሰፍት ዜና በቀር ሌላው ሁሉ ነገር ከዜና ተቆጥሮ ወደማይታሰብበት ጊዜ ውስጥ ገብተናል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው የክርስቶስ ምጽአቱ ስለቀረበ ብቻ ሳይሆን፣ ጌታ ስለተቆጣም ጭምር ነው! እየሆነ ያለው ነገር በዐመጻችን ምክንያት፣ በኃጢአታችንም ምክንያትም ነው፡፡ ጌታ ተቆጥቶናል፣ እኛም ንስሐ አልገባንም፤ እርሱም ይቅር አላለንም።

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር ራሱን በቁጣ ከድኗል! እያሳደደንም ነው! ያለ ርህራሄ እየገደለን ነው! በየቦታው ያለን ክርስቲያኖች ያለ ርህራሄ እየሞትን ነው! ከነዐመጻችን ከነኃጢአታችን በየቦታው እንጮኻለን እንጂ ጸሎታችን እየተሰማ አይደለም! በአሕዛብ መካከል እንደ አተላና ጥራጊ ተደርገናል! ጠላቶቻችን አፋቸውን በእኛ ላይ ከፍተው በጥፋትና በመፈራረስ በችግርና በሽብር እየተሰቃየን ነው!

ወገኖች ሆይ፣ አሁን ጊዜው የመጨረሻውን ጥንቃቄ የምናደርግበት፣ የመጨረሻውን ዝግጅት የምናደርግበት ነው! ጊዜው መንገዳችንን የምንመረምርበት፣ ጊዜው መንገዳችንን የምንፈትንበት ጊዜ ነው! የክርስቶስ ምጽአቱ ቀርቧልና በንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ!


ወገኖች ሆይ፣ ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤ ዐምፀናል፣ ኃጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም። አቤቱ ይቅር በለን፣ አቤቱ መልሰን፣ እኛም እንመለሳለን! አቤቱ በአሕዛብ ዘንድ አተላና ጥራጊ ሆነናልና ማረን! በመጥፋት፣ በመፈራረስ፣ በችግርና በሽብር ተሰቃይተናልና ማረን !

No comments:

Post a Comment