Wednesday, April 22, 2015

ከሰው ሁሉ ጋር - በሰላም አብሮ የመኖር ጥበብ!



ዲቮሽን 224/07 ረቡዕ፣ ሚያዝያ 14/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

ከሰው ሁሉ ጋር - በሰላም አብሮ የመኖር ጥበብ!

ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፥ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ፡፡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ (ሮሜ 1218)

አማኝ በበኩሉ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም አብሮ ለመኖር ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ በክፉ ፈንታ ክፉ ባለመመለስ፥ ክፉውን በመልካም በማሸነፍ፥ ከወዳጆችም ከጠላቶችም ጋር በሰላም ለመኖር ዋጋ መክፈል ይጠበቅብናል!

ወገኖች ሆይ፥ ሰላም የሚገኘው በእኛ ቁጥጥር ሥር ባለመሆኑ፥ አንዳንዴ ብዙ ዋጋ ከፍለንም ላይሳካ ይችላል፡፡ በክፉ ፈንታ መልካም እያደረግን፥ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን እያደረግን፥ ጠላታችን ሲራብና ሲጠማ፥ እያበላንና እያጠጣን ብድራታችን ግን ምስጋና ሳይሆን ግልባጩ ሊሆን ይችላል! ቢሆንም፥ በሁኔታዎች ተቆጥተን እጃችንን ለበቀል ማንሳት የለብንም፡፡ በቀል የእግዚአብሔር ነውና፥ ብድራትን ለሚመልስ ጌታ ልንተውለት ይገባል!

ወገኖች ሆይ፥ አማኞች የምሕረት ልጆች ነን! ስለሆነም፥ አማኞች ለምሕረት ቅድሚያ መስጠት ይገባናል! አማኞች የሌሎችን ክፋት እያሰላሰልን ማሳለፍ የለብንም፡፡ ይልቁንም፥ የሌሎቹ ኃጢአት እንዳይበክለን የክፉ ሰዎች ክፋት ጠልፎ እንዳይጥለን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል!

ወገኖች ሆይ፥ "በሰላም ኑሩ" የተባለው፥ "ከሰው ሁሉ" ጋር ነው! ይህም ማለት ብሔርና ቋንቋ፥ ጾታና ሐይማኖት ሳንለያይ ከሁሉም የሰው ልጆች ጋር ማለት ነው!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ የሞተው ለሰው ልጆች ሁሉ ነው! ለአፍሪካዊው፥ ለላቲኖአዊው፥ ለኤዥያዊው፥ ለአውሮፓዊው፥ እና ለአሜሪካዊው ሁሉ ኢየሱስ ሞቶለታል! እኛም ይህን ፍቅር ቀምሰን አይተናልና፥ የሰውን ልጆች ሁሉ ልንወድ ይገባል! የምንችለውን ያህል፥ ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር ልንጥር ይገባል!

No comments:

Post a Comment