Tuesday, April 21, 2015

አብያተ ክርስቲያናት – በሰላም እንዲኖሩ!



ዲቮሽን 223/07 ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 13/07 /
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


አብያተ ክርስቲያናት በሰላም እንዲኖሩ!

በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር። (የሐዋ 931)

ታውቃላችሁ፣ በይሁዳ ሁሉና በገሊላ እንዲሁም በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ሊያገኙ የቻሉትና በቁጥርም ሊበዙ የቻሉት በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው! አንደኛው፣ የቤተክርስቲያንን ሰላም ይነሣ የነበረው አሳዳጁ ሳውል ወደ ጌታ መምጣቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ ደቀመዛሙርትን ሲያሳድዱ የነበሩ የአይሁድ መሪዎች በራሳቸው ችግር ላይ ስለወደቁ ነው! ሦስተኛው ደግሞ፣ በስደቱ ምክንያት፣ ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች የተበተኑ ደቀመዛሙርት፣ ቃሉን እየሰበኩ በመዞራቸውና ታላቁን ተልዕኮ መፈጸም በመቻላቸው ነው።

ወገኖች ሆይ፣ ሳውል ወደ ጌታ በመጣበት ወቅት ሀገሩን ይገዛ የነበረው የሮማ ንጉሥ ጥቤሪዮስ ሞተ፡፡ እርሱን ቀጥሎ የነገሠው ካሊጉላ በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ የራሱን ሐውልት አስቀርጾ ለማቆም ተነሣ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የአይሁድ መሪዎች ደቀመዛሙርትን ማሳደድ አቁመው፣ ፊታቸውን ወደ ራሳቸው ችግር በመመለሣቸው ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእውነተኛ የክርስቶስ ተከታይነት ዋናው ምልክቱ ክርስቶስን መንገድ መከተልና የሐዋሪያቱን ምሣሌ መከተል ነው፡፡ ይህም፣ እየተጠሉ፣ እየተወገዙ፣ እየተሰደቡ፣ እየተደበደቡና እየተሰደዱ፣ ነገር ግን ወንጌልን በፍቅር መስበክ ነው፡፡ እየቆሰሉና እየደሙ፣ እየተሰቀሉና በድንጋይ እየተወገሩ፣ ነገር ግን ወንጌልን በፍቅር መስበክ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእውነተኛ የክርስቶስ ተከታይነት ጠላቶቻችንን መውደድ፥ የሚረግሙንን መመረቅ፥ ለሚጠሉን መልካም ማድረጉ፥ ለሚያሳድዱንም መጸለይ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስን አስቡ! በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሐሰት ምስክር ያቆሙ፣ ምንም ሳያጠፋ ሰቅለው የገደሉት፣ የአይሁድ መሪዎች ናቸው! ቅዱስ እስጠፋኖስንም አስቡ! እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ይህንን ቅዱስ ሰው፣ ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ የነበረውን ይህንን ጻድቅ ሰው፣ ያለበደሉና ያለ ምንም ጥፋቱ ወግረው የገደሉት ሳውልን ጨምሮ የአይሁድ መሪዎች ናቸው!

ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ኢየሱስን ሰቅለው የገደሉ፣ እስጠፋኖስንም በድንጋይ በመውገር ሰማዕት ያደረጉ፣ በደቀመዛሙርቱም ላይ ስደት አቀጣጥለው ወደየአቅጣጫው የበታተኑ፣ የአይሁድ መሪዎች ናቸው! እነዚህ መሪዎች በራሳቸው ጉዳይ በመጠመዳቸው፣ አሳዳጁም ሳውል በደማስቆ መንገድ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ስለተገናኘ፣ ወደየአቅጣጫው የበታተኑቱም በየሄዱበት ሁሉ ወንጌል እየሰበኩ በመዞር፣ ታላቁን ተልዕኮ ለመፈጸም ስለቻሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት እፎይታ አገኙ!

ታውቃላችሁ፣ የሐይማኖት መሪዎች በቤተክርስቲያንን ላይ የሚያቀነባብሩት የስደት  ዘመቻ እስካልቆመ ድረስ፣ አሳዳጆቻችን ጌታን ተቀብለው እስካልዳኑ ድረስ፣ ታላቁ ተልዕኮ እስካልተፈጸመ ድረስ፣ በአብያተ ክርስቲያናት እፎይታና ሰላም ሊኖረን አይችልም!

ታውቃላችሁ፣ በአብያተ ክርስቲያናት ታላቁን ተልዕኮ ካልፈጸሙ በቀር፣ ለሰው ልጆች ሁሉ እየመሰከሩ ደቀመዛሙርት ካላፈሩ በቀር፣ እፎይታ ሊያገኙ፣ መጽናናት ሊያገኙ፣ በቁጥር ሊበዙና በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበት ሌላ መንገድ የለም!

No comments:

Post a Comment