Monday, April 20, 2015

እንደሚታረዱ በጎች – ተቆጠርን!

ዲቮሽን 222/07 ሰኞ፣ ሚያዝያ 12/07 /
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


እንደሚታረዱ በጎች – ተቆጠርን!

ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው (ሮሜ 8፡36)

በየቀኑ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንገጣጠማለን! በየቀኑ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንተያያለን! በየቀኑ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እንፋጠጣለን!

ወገኖች ሆይ፣ በየቀኑ እንደሚገደሉ ሰዎች፣ እንደሚታረዱ በጎች ነን! በየቀኑ እንደሚሰበር ሸክላ ነን! በዚህ ዓለም ሳለን በየቀኑ መከራ አለብንና፣ በየቀኑ እንገፋለን፣  በየቀኑ እንወድቃለን፣ በየቀኑ እንሰደዳለን፣ በየቀኑ ለሞት ተላልፈን እንሰጣለን!

ታውቃላችሁ፣ በየቀኑ እንደሚገደሉ ሰዎች፣ እንደሚታረዱ በጎች ብንሆንም ከክርስቶስ ፍቅር ግን የሚለየን የለም!

ታውቃላችሁ፣ መከራ–ጭንቀት ቢሆን፥ ራብ–ራቁትነት ቢሆን፥ ፍርሃትና– ስደት ወይንም ሰይፍ ቢሆን ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም!

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር መርጦናልና፣ መከራ፣ ፈተናና ሞት ቢኖርም፣ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን!

ወገኖች ሆይ፣ እየተገፋንም–እየወደቅንም፣ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን! እየተሰበርንም–እየተበተንንም፣ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን! እየተጠላንም–እየተሰደድንም፣ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን! እየተገደልንም–እየታረድንም ከአሸናፊዎች እንበልጣለን!

ታውቃላችሁ፣ የኢየሱስ ሕይወት በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን (2 ቆሮ 4፡11)። ይኼ ነው ምስጢሩ! የኢየሱስ ሕይወት በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን የምንዞር ሰዎች ነን!

ወገኖች ሆይ፣ በዓለም ሳለን መከራ አለብን! ቢሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን አሸንፎታል(ዮሐ 16 33)፡፡ ስለሆነም አይዞን!

ወገኖች ሆይ፣ ቢገባንም ባይገባንም፣ በእኛ ላይ በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ፣ በሚያጋጥሙን ፈተናዎችና መከራዎች ሁሉ፣ በእኛ በደካሞቹ የጌታ የእውቀቱ ሽታ እየተገለጠ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ቢገባንም ባይገባንም፣ የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን፣ ይህን ታላቅ መዝገብ በእኛ በሸክላ ዕቃዎቹ ውስጥ በማድረግ የእውቀቱን ሽታ እየተገለጠ ነው!

ሃሌሉያ! በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን (2 ቆሮ 2 14)

---------

ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

No comments:

Post a Comment