ዲቮሽን 221/07፥ እሁድ፣ ሚያዝያ 11/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ምጽአተ ኢትዮጵያ!
ሰሞኑን በሳውዝ አፍሪካ ባሉ ኢትዮጵያዊያን
ወገኖቻችንና በመጤው ኮሚኒቲ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆም፣ መላው ዓለም በጸሎትና በሰላማዊ ሰልፍ እየጮኸ ያለበት ጊዜ ነው!
ሳውዝ አፍሪካ አልን እንጂ በየመን የተቀጣጣለው አመጽ የብዙሐን ወገኖቻችን ሕይወትም አደጋ ላይ ነው፡፡ ከወራት በፊትም በሳዑዲ
አረቢያና አካባቢው ይኖሩ በነበሩ ወገኖቻችን ላይ፣ እንዲሁም በመላው ዐረብ አገራት በሕዝባችን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን
ጥቃት እናውቃለን፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ይህች አገር ኢትዮጵያ ሁሉ
ነገሯ ያስገርማል! ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በሁሉም የዓለም አገሮች ማለት እስከሚቻል ድረስ ተበትነው ይገኛሉ፡፡ የመበተናቸው ምክንያት
የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ የትምህርት፣ ወይንም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚገርመው ነገር በአብዛኛው አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን አይወደዱም
ወይም አይከበሩም ማለት ይቻላል! ይህ ሁኔታ ይገርመኛል!
ወገኖች ሆይ፣ በእኛ ላይ ብዙ ኢሰብዓዊ
ጥቃቶች ከሚያደርሱብን አገሮች አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ብዙ ውለታ የዋለችላቸው አገሮች መሆናቸው ደግሞ ይገርመኛል! ሁሉም ጎረቤቶቻችን፣
ለእኛ ውለታ ቢሶች ናቸው! የደቡብ አፍሪካዊያኖቹ ውለታ ቢስነትም ከሌሎቹ የተለየ አይደለም!
ወገኖች ሆይ፣ አውሮፓዊያንን አስቡ! አሜሪካኖቹን
አስቡ! ላቲኖቹንም አስቡ! አዥያዊያንን አስቡ! እስራኤልን ጨምሮ መሐከለኛው ምሥራቃዊያንን አስቡ! አፍሪካዊያኖቹንም አስቡ! ብዙዎቹ
ለኢትዮጵያ መልካም አስተሳሰብ የላቸውም!
ታውቃላችሁ፣ እንደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ
እስራኤላዊያንም እንደዚህ ነበሩ! በየደረሱበት ቦታ ሁሉ ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው!
ወገኖች ሆይ፣ አሶራዊያን የሰሜኑን የእስራኤል
ክፍለግዛት በጦርነት አውድመው፣ አስሩን የእስራኤል ነገዶች በየአቅጣጫው ተበትኖ እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡ ባቢሎናዊያን ደቡቡን የእስራኤል
ክፍለግዛት በጦርነት አውድመው፣ ሕዝቡን ማርከው ወስደዋል፡፡
ታውቃላችሁ፣ በአርጤክስስ ዘመነ ግዛትም
መላው እስራኤላዊያን እንዲደመሰሱ አዋጅ ወጥቶባቸዋል፡፡ የናዚው ሒትለር በእስራኤላዊያን ላይ የደረሰውን እልቂት አስቡ! መላው አረቦች
ዛሬም ድረስ በእስራኤላዊያን ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ አስቡ!
ወገኖች ሆይ፣ እስራኤል ይደርሱባት በነበሩ
ጥቃቶች ምክንያት እስክትፈራርስና እስክትጠፋ ድረስ እንደሀገር መቆጠሯ እስኪቀር ድረስ የሆነባቸውን አስቡ!
ታውቃላችሁ፣ እስራኤላዊያን በሚኖሩባቸው
ሀገሮች ሁሉ ይደርሱባቸው የነበሩ ጥቃቶች ሲበረታባቸውና ሲያንገሸግሻቸው፣ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ወደ ገዛ ሀገራቸው
ለመመለስና የፈራረሰችውን ሀገራቸውን ለመገንባት ውሳኔ አደረጉ! ይህም ምጽዐተ አስራኤል እየተባለ የሚጠራው ዓለማቀፋዊ ንቅናቄ ነው!
በብዙ መስዋዕትነትም ሀገራቸውን መገንባትና በዓለም መንግሥታት ዘንድ የተፈራችና የበለጸገች ሀገር መገንባት ቻሉ!
ታውቃላችሁ፣ የኢትዮጵያዊያም ሁኔታ እንዲህ
ይሆናል! ኢትዮጵያዊያን በተበኑባቸው ዓለሞች በአብዛኛው ለወገኖቻችን እየተመቸ አይደለምና ምጽዐተ ኢትዮጵያ መሆን ይጀምራል!
ወገኖች ሆይ፣ አገራችን ኢትዮጵያ በብዙ
መሠረተ ልማቶች እየተለወጠች ነው! በየወቅቱ የምንሰማቸው ሀገር አቀፋዊና ዐለም አቀፋዊ ሪፖርቶች የአገራችንን አዲሷ የአፍሪካ ኃያል
ሀገር ወደመሆን እየደረሰች መሆኗን እየመሰከሩ ናቸው፡፡ ከዚህም ከዚያም አካባቢ የሚደመጡ ሰንበላጣዊ ወጦቢያዊ ድምጾች ቢኖሩም፣
ሀገራችን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እየተለወጠች ነው!
ወገኖች ሆይ፣ አገራችን ኢትዮጵያ በምግብ
ራሷን ችላ መላው ሕዝቦቿን መግባ የምታጠግብበት፣ የሀገራችን ብልጽግና ከራሳችን ተርፎ ለሌሎች የእህልና የገንዘብ ድጋፍ የምናደርግበት
ዘመን ሩቅ አይደለም! የኢትዮጵያ ተሐድሶ ለዓለምን ሕዝብ ሁሉ ትኩረት ከመሳብም አልፎ፣ የመላው ዓለም ሕዝቦች አትዮጵያን ለመጎብኘት
የሚጎርፉበት፣ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ለመኖር ላይ ታች የሚሉበት ዘመን እሩቅ አይደለም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ዛሬ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ
በሕገወጥ መንገዶች በውርደት በየባህሩና በየበረሃው አቋርጦ ወደ ሌሎች ሀገሮች ለመግባት ሲል ሕይወቱን ለባሕር እንስሳትና ለምድረበዳ
አውሬዎች ቀለብ የሚያደርገው ሕዝባችን፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ሲሆን በሕጋዊ ቪዛ በክብርና ሞገስ ወደፈለገበት ዓለም የሚዘዋወርበት
ዘመን እሩቅ አይደለም!
No comments:
Post a Comment