ዲቮሽን 213/07፥ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
መጋረጃው ተቀደደ – መቃብሮች ተከፈቱ – የሞቱ ቅዱሳን ተነሡ!
ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ (ማቴ 27፡50-53)።
ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል የሚያደርገው የክርስትና እምነትና ይኼው እምነት አስተምህሮውን የመሠረተበት
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኝነታቸው በተግባር የተረጋገጠ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ በአይሁድ ቤተመቅደስ ውስጥ ሁለት መጋረጃዎች ነበሩ – አንደኛው የሚገኘው በቅድስት ፊትለፊት ሲሆን፣ ሁለተኛው
ደግሞ በቅድስትና በቅድስተ ቅዱሳን መካከል ነበረ፡፡ ኢየሱስ በሞተ ጊዜ የተቀደደው ቅድስትን ከቅድስተ ቅዱሳን የሚለየው ሁለተኛው
መጋረጃ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ቅድስተ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ማደሪያ (ሀልዎት) ነው! በብሉይ ኪዳን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው
ሊቀካህኑ ብቻ ሲሆን ይህም በዓመት ለአንዴ ብቻ ነው፡፡ ከሊቀካህኑ በስተቀር ለሌሎች ሰዎች ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የተከለከለ
ነው! ኢየሱስ በሞተ ጊዜ የተወገደው ይኼ ክልከላ ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ መጋረጃው የተቀደደው ከላይ ወደ ታች ነው! ይህም እግዚአብሔር ራሱ ልጁን መስዋዕት በማድረግ ከሕዝቡ ጋር
መታረቁን ያሳያል! ደግሞም በእርሱና በሕዝቡ መካከል የነበረው የዘመናት የኃጢአት ግድግዳ መፍረሱን ያመለክታል! ከኢየሱስ ሞት በኋላ
ሰዎች ያለማንም ሌላ መካከለኛ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንዲችሉ በሩ መከፈቱንም ያሳያል!
ታውቃላችሁ፣ በኢየሱስ ሞት ምክንያት ያለ ማንም ሌላ አማላጅ፣ ያለ ማንም ሌላ የነፍስ አባት፣ ያለ ማንም ሌላ የንስሐ
አባት፣ ያለ ማንም ሌላ ሰማዕታትና መላዕክት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንድንችል በሩ ተከፍቶልናል!
ታውቃላችሁ፣ እንግዲህ፥ ወንድሞች
ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት አለን
(ዕብ 10፡19-20)፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ኢየሱስ በሞተ ጊዜ፣ የተሰነጠቀው መጋረጃው ብቻ አይደለም! በመስቀሉ ሥራ ጸሐይ
ጨልማለች፣ ምድር ተናውጣለች፣ አለት ተሰንጥቋል፣ መቃብሮች ተከፍተው፣ የሞቱ ቅዱሳን ከሞት ተነስተዋል!
ታውቃላችሁ፣ ኢየሱስ በሞተ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከተማ መካነ መቃብር የወጡ ቅዱሳን፣ እንደ አላዛር
ሁሉ (ዮሐ 11፡43-44)፣ እንደ ኢያኢሮስ ሴት ልጁ ሁሉ (ሉቃ 8፡52-56)፣ እንደ ናይን ከተማዋ መበለት፣ ለእናቱ አንዲያ ወንድ ልጅ ሁሉ(ሉቃ
7፡13-15) ኢየሱስ ሲሞት እነርሱ ከመቃብር ወጥተዋል!
ታውቃላችሁ፣ ኢየሱስ በሞተ ጊዜ ከመቃብር የወጡ ቅዱሳን፣ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ደግሞ ወደ
ከተማ ገብተው ከየከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል!
ወገኖች ሆይ፣ የሞቱ ሰዎች ከመቃብር መውጣት፣ ለቅዱሳን ትንሣኤ እንደ በኩር ፍሬ ሆኗል፡፡ የሞቱ
ቅዱሳን ከሞት እንደሚነሱ ሕያው ማረጋገጫ፣ ሕያው ምስክርም መሆን የቻለ ነው!
---------
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment