Thursday, April 30, 2015

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና - ዘመኑን ዋጁ !

ዲቮሽን 232/07 ሓሙስ ሚያዚያ 22/07
(
በወንድም ጌታሁን ሓለፎም)


ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና - ዘመኑን ዋጁ !

"እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው እና ዘመኑን ዋጁ" (ኤፌ 5-15-17)

ቴክኖሎጂው በረቀቀበት በዚህ ዘመን፤ በአራቱም ማእዘን በተለያዩ ክፍለ አለማት የሚከናወነውን ድርጊት እና ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ ሆኖ ለመከታተል እና ለማወቅ ከመቸውም ይልቅ እንደዚህ ዘመን ምቹ የሆነበት ወቅት የለም፡፡ ቴሌቪዥኑ፥ ጋዜጣው፥ እንተርኔቱ ሁሉ የአለምን ገጽታ ያለንበት ቦታ ድረስ ትኩስ ትኩሱን ይዞልን ይመጣልሳሎናችን ድረስ !

ታዲያ አይኖቻችን እና ጆሮቻችን ከመልካሙ ይልቅ ክፉውን፥ ከምስራቹ ይልቅ መርዶውን፥ ከደስታ ይልቅ ሓዘንን እና ድንጋጤን ጠግበው መሽቶ ይነጋል፡፡ ከዚህም ተጽኖ የተነሳ ነፍሳችን በፍርሃት እና በድንጋጤ ጫጭታለች፡፡ በሁሉም ሰው ፊት ተስፋ መቁረጥ ይነበባል፡፡

ዛሬ አለም በውጥረት ላይ እና በጭንቅ ውስጥ እንዳለች ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምድርን እያናወጣት ነው፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ፥ የጎርፍ እና የእሳት ቃጠሎ በተከታታይ የተለያዩ ቦታዎችን እየመታ ነው፡፡ ጦርነት ድርቁ በሽታውና እርዛቱ ለጉድ ነው፡፡ 

ፍርሃት እና ድንጋጤ በየቦታው ወድቋል፡፡ ሁሉ ነገር የአለምን የከፋ ሁኔታ የሚያሳብቅ እንጅ የወደፊቱን መልካም ዘመን የሚጠቁም አይደለም፡፡

በሰዎች መካከል ፍቅር ጠፍቶአል፡፡ ወንድም ወንድሙን ይገድላል፥ አባት በልጅ ላይ ጨክኖአል፥ መንግስታት በመንግስታት ላይ ተነስተዋል፥ በሰዎች መካከል ስነ ምግባር ተበላሽቷል፥ ነውር እርቃኑን ወጥቶ አደባባይ ውሏል፡፡

ዘመኑ ክፉ ነው! ይህንን የተረዳው ጳውሎስ ለዚህ ነው እንግዲህ የዛሬ 2000 አመትገደማ በዘመኑ ለነበሩት ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ምእመን ሲጽፍ ቀኑ ክፉ ስለሆነ አትዘናጉ፥ እንደ እግዚአብሔር ሰው ጥበበኛ ሁኑ፡፡ ቀኑን ወቅቱን መርምሩ በዚህ በከፋ ዘመን እርኩሰት እና ክፋት በተንሰራፋበት ወቅት አካሄዳችሁ እርምጃችሁ የጥንቃቄ ይሁን፤ ዘመኑ እየከፋ፥ እየተበላሸ እንጅ መልካም ዘመን ይመጣል ብላችሁ አትጠብቁ፡፡ ከጌታ እና ከመንፈሱ ጋር ተጣበቁ፡፡

እውነት ነው ወገኖቼ፥ ከመቸውም ይልቅ ስለ ጽድቅ የሚሰበክበት ዘመን ቢኖር አሁን ነው፡፡ የዚህ ዘመን መሪ አገልግሎታችንም ቢሆን ሰዎችን ወደ ንስሃ መጥራት፥ ከሃጢያት እስራት በወንጌል ነጻ ማውጣት፤ በጾም በጾሎት በጌታ ፊት መቆየት ዋነኛ ተግባራችን መሆን አለበት፡፡

እያንዳንዱ ቀናችንን እንደዋጀን እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ የምትባክን በፌዝ እና በቧልት የምታልፍ ጊዜ ሊኖረን አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ እናንተ የጌታ ብሩካን እንድንጸና እና እንድንጸልይ በመጠን እየኖርን፤ ለጌታ ክብር ጊዜውን እንዋጅ !

ትምህርቱ ጠቅምዎት ከሆነ፥ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

Wednesday, April 29, 2015

ሚሊዮኖች ሲወድቁ - ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ዲቮሽ 231/07፥ ረቡዕ፥ ሚያዝያ 21/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ሚሊዮኖች ሲወድቁ - ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

እግዚአብሔርም አለ፥ የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቷልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና … በከተማዪቱ አስር ጻድቃን ባገኝ ሥፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ … አላጠፋትም (ዘፍ 18፡20-33)

ከሰሞኑ በደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት በኔፓል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የማለቃቸውን ዜና ሰማን፡፡ ከሳምንታት በፊትም 30 ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት አንገታቸው ሲቀላ፥ የጥይት ናዳ እንደዝናብ ሲዘንብባቸው አየን፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ከዚህ ወቅት ትንሽ ቀደም ብሎም ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ፥ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ መጤ ዘጎች ከነሕይወታቸው ሲቃጠሉ ተመለከትን፡፡ ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎም፥ 21 ግብጻዊያን ክርስቲያኖች እንደ በግ ሲታረዱ አየን፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ከጥቂት ወራት በፊትም በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ኩርዶች፥ ኢራቃዊያን፥ ሶሪያዊያን፥ ሊባኖሳዊያን፥ ፓክስታናዊያን፥ ሕንዳዊያንና ሌሎችም የአረብ ክርስቲያኖች ጅምላ ጭፍጨፋ ሲደርስባቸው አየን፥ ሰማንም፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎም በኬንያ፥ በናይጄሪያ፥ የሚዘገንኑ ጅምላ ጨራሽ ጭፍጨፋዎች መደረሳቸውን አየን፡፡ ከዚህ ቀድም ብሎም በፈረንሣይ፥ በአረብ ኢሚሬትስ ጅምላ ጭፍጨፋዎች ደርሰዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ከዚህ በፊትም፥ በኢትዮጵያና ኤርትራ፥ በሶማሊያና ሱዳን፥ በኮንጎና ሩዋንዳ፥ በሌሎቹም ቦታዎች በሚሊዮችና በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የሰው ልጆች ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ጅምላ ጭፍጨፋዎች ሲደርሱ አይተናል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ከዚህም ቀደም ብሎ፥ በኢትዮጵያ የደረሰው ቀይና ነጭ ሽብር፥ በየዘመኑም የሚከሰተው አረንጓዴ ቢጫ ሰማያዊ ችግር፥ የቅንጅት፥ የሌጣ፥ ሐይማኖታዊና የፖለቲካ ችግር የብዙ ሰው ሕይወት በከንቱ ተቀጥፏል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ወገኖች ሆይ፥ በጠራራ ጸሐይ ይኼ ሁሉ አደጋ፥ ይኼ ሁሉ ጥፋት፥ ይኼ ሁሉ እልቂት በየቦታው ሲደርስ ጻድቃን ወዴት አሉ? በጨካኞች ካራ ሚሊዮኖች ሲቀሉ በጨካኞች ጥይት ሚሊዮኖች ሲወድቁ፥ ሚሊዮኖች ተስድደው፥ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው፥ ሚሊዮኖች ሲጠፉ ጻድቃን ወዴት ሄዱ?

ወገኖች ሆይ፥ "አስር ጻድቃን ያሉበት ከተማ አትጠፋም" ከተባለ፥ ከተሞች ሲፈርሱ፥ ከተሞች ሲጠፉ ጻድቃን ወዴት አሉ? በከተማ ሽብር፥ በገጠሩ ሽብር፥ በሀገሩ ሽብር፥ በአህጉሩ ሽብር፥ በዓለማችን ሽብር ሲሆን ጻድቃን ወዴት አሉ? ይኼ ሁሉ ሲሆን ጻድቃን ወዴት ሄዱ? ወይስ፥ በየከተማው ያሉ የጻድቃኖቻችን ቁጥር አስርም አይሞላም?

ትምህርቱ ጥቅምዎት ከሆነ ላይክ ያድርጉ! ጌታ ይባርክዎ!

Tuesday, April 28, 2015

ሰይፍ የሚያነሡ - በሰይፍ ይጠፋሉ!

ዲቮሽን 230/07፥ ማክሰኞ፥ ሚያዝያ 20/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ሰይፍ የሚያነሡ - በሰይፍ ይጠፋሉ!

ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው፡፡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፥ "ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ" (ማቴ 26፡51-52)

ወገኖች ሆይ፥ ኢየሱስን ተመልከቱ! ጌታችን ኢየሱስ ቀጭን ትዕዛዝ ቢሰጥ፥ የሰማይ ሠራዊት ከጸሐይ ፍጥነት ይልቅ ፈጥነው ሊደርሱለትና የተነሱበትንም ኃይሎች ሊደመስሱትና ሊያጠፉም በቻሉ ነበር! ነገር ግን ያንን መድረግ አልፈለገም! ራሱን ለመከላከልም፥ ጋሻ ጦርና ሰይፍ ፍጹም አልታጠቀም! ለዚህም ነው ጴጥሮስን መገሰጽ የቻለው!

ታውቃላችሁ፥ ጴጥሮስ የማልኮስን ጆሮ ቆርጦ ሲጥል፥ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን ገስጾ፥ የማልኮስን ጆሮ መልሶ ፈወሰ፡፡ ወገኖች ሆይ፥ የክርስትና እምነት የሰይፍና የጦር ድጋፍ አይፈልግም! የክርስትና ሐይማኖት ጠላቶችን መውድድ፥ የሚረግሙትን መባረክ እንጂ፥ የእኔን እምነት ካላመንክ፥ የኔን መንገድ ካልሄድክ ብሎ የሰውን ጆሮ መቁረጥ፥ የሰው አንገት ማረድ በክርስትና ዓለም እንዲህ ያለ የለም!

ታውቃላችሁ፥ የክርስትና እምነት እውነት ስለሆነ፥ የጦር የሰይፍ ድጋፍ አያስፈልገውም! የክርስትና እምነት የሠራዊቱን ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ስለሆነ፥ ይህን እምነት በዓለም ለማስፋፋት የሰው ጡንቻና ኃይል አያስፈገውም!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ ለጴጥሮስ ሲናገር፥ የሰማዩ አባቴ ብጠይቀው ከ12 ጭፍሮች(ከ72ሺ) የሚበልጡ መላዕክት ሊሰድድልኝ እንደሚችል አታውቅምን? ያለው ታላቅ ትምህርት አለው፡፡
ወገኖች ሆይ፥ በሮማ ዘመነ መንግሥት አንድ ጭፍራ (ሌጊዮን) 6ሺ ወታደሮችን ይይዛል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት፥ ጌታ 12 ጭፍሮችን(ሌጊዮኖችን) ማለትም 72ሺ መላዕክት ማዘዝ ይችል ነበር፡፡ ይህን አላደረግም፡፡ ነገር ግን፥ ይህን ቢያደርግ ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር?

ወገኖች ሆይ፥ በግብጽ ሀገር አንድ መልዐክ ባንዲት ሌሊት ብቻ፥ የተቀረቀሩ በሮች መስበር ሳያስፈልግ፥ የተዘጉ ደጆች መክፈት ሳያስፈልግ፥ ከቤተ መንግሥቱ እስከ ጥበቃ ድረስ (ዘጸ 12፡23) ማንም ሳያግደው ማንም ሳይቋቋመው የግብጽን በኩራት ለመግደል መቻሉን ልብ ያለው ልብ ይሏል!
ወገኖች ሆይ፥ እስራኤልን በመቁጠር ዳዊት በፈጸመው ጥፋት አንዱ መልዐክ ብቻ፥ በአንዲት ቀን ብቻ (2ሳሙ 24፡15-17) 70ሺ እስራኤላዊያን መጨረሱን አሁንም ልብ ይሏል!

ወገኖች ሆይ፥ በሕዝቅያስ ዘመን የአሶር ንጉስ ሴናክሬም በትዕቢት ተነስቶ በእስራኤላዊያን ላይ ሠራዊት ሰብስቦ ሲመጣ፥ አንዱ መልዐክ ብቻ፥ በአንዲት ቀን ብቻ (2ነገ 19፡35) 185ሺ አሶራዊያንን መደምሰስ መቻሉን አሁንም ልብ ይሏል!

ታውቃላችሁ፥ ጌታ ከተዋጋ፥ አንዱ መልዐክ ብቻ፥ የፔንታጎንንና የተባበሩት መንግሥታት የጦር ኃይሎቻቸውን፥ የባህር ኃይሎቹን የምድር ተዋጊዎቹን፥ ሚሳይሎቻቸውን፥ ሚጎች መናምኖች፥ ድሮኖቻቸውን በመብረቅ ብልጭታ፥ በሰከንዶች ፍጥነት ድባቃቸውን መትቶ፥ ድራሻቸውን ሁሉ ሊያጠፋ ይችላል!

ታውቃላችሁ፥ ጌታችን ኢየሱስ የቁጥራቸውን ብዛት፥ የሰው ቋንቋ ስሌት ሊገልጽ የማይችለውን የሰማይ መላዕክት ፈጣሪና አዛዥ ተቆጣጣሪያቸውም ነው! ይህንን ኃይል ይዞ፥ ይህን ጉልበት ይዞ፥ ሲወጉት ሲወግሩት፥ በእንጨት ላይ ሲሰቅሉት የሚያደርጉትን ነገር ምንም ለማያውቁ፥ በመንፈስ ጭለማ ለሚመላለሱ ለሐይማኖት መሪዎች፥ ሰይፍና ጦር ይዘው ሲሰድቡት፥ ሲያዳፉት፥ ሲያንገላቱትም ለነበሩ ለሮማዊያን ጭፍሮች ምሕረትን ለመነ፡፡

ወገኖች ሆይ፥ ይህ ነው ፍቅር ማለት! ይህ ነው እምነት ማለት! መመካት ቢያስፈልግ ደግሞ ይህ ነው ክርስትና፥ ይኼ ነው ሐይማኖት!

ወገኖች ሆይ፥ በጦርና በሰይፍ የሚስፋፋ ሐይማኖት፥ ጤና የሌለው ነው! ሀገር በማሸበር፥ የሰው ደም በማፍሰስ የሚያስፋፉት ሐይማኖት ከአጋንንት አምልኮ የተሻለ ቦታ ሊሰጠው አይችልም! የሰውን ልጅ በማረድ የሚደሰት መንፈስ ከአጋንንት እንጂ ከሰው ልጅ አይደለም!

ወገኖች ሆይ፥ ጌታችን ኢየሱስ የወንጌን እምነት እንድናስፋፋ ያስተማረን በፍቅር ብቻ ነው! ወንጌል ስንመሰክር፥ እንደ በጎች ወደ ተኩላዎች መሀል ሰተት ብለን ገብተን፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር በሰው ልጆች መሃል ተግተን እንድናስፋፋ ተልዕኮ ሰጥቶናል፡፡ ይኼ ነው እውነቱ፥ ይህ ነው እምነት ማለት፥ መመካት ቢያስፈልግ ይኼ ነው ሐይማኖት!

ሰይፍን የሚያነሱ - በሰይፍ ይጠፋሉ! በሐይማኖት ሰበብ ሰውን የሚገድሉ ሲዖል ይገባሉ!

Monday, April 27, 2015

እግዚአብሔር ይነሣ – ጠላቶቹም ይበተኑ!



ዲቮሽን 229/07፣ ሰኞ ሚያዚያ 19/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

እግዚአብሔር ይነሣ – ጠላቶቹም ይበተኑ!

እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ። ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኅጥኣን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ (መዝ 68፡1-2)።

ወገኖች ሆይ፣ ሙሴ እስራኤላዊያንን ወደተስፋዪቱ ምድር ለማድረስ በምድረበዳ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ ይዘምር የነበረው ዝማሬ፣ ይጮኽ የነበረው ጩኸት ይኼ ነው! እግዚአብሔር ይነሣ! ጠላቶቹም ይበተኑ! ወገኖች ሆይ፣ ጌታ እንዲነሣ፣ ጠላቶቹም እንዲበተኑ – ወደ ጌታ እንጩኽ !

ወገኖች ሆይ፣ የኃጢአተኞች ክፋት በምድር ላይ ሲበዛ፣ ለጻድቃን መከራ ይበዛል! እግዚአብሔር ዝም ሲል፣ የጻድቃን መከራ የትየለለ ይሆናል! ጌታ ካልተነሣ፣ እግዚአብሔር ዝም ሲል፣ ጠላት በሕዝቡ ላይ የፈለገውን ሥራ ሊሠራ ይችላል!

ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ካልተነሣ፣ ጠላት በጻድቃን ላይ ምላሱን አውጥቶ እኚኝያ ይሰጣል! ጌታ ካልተነሣ፣ ጠላት በጻድቃን ላይ ጦሩን ከነነቅነቅ፣ ሰይፉን ከመምዘዝ አልፎ፣ ጦሩን ይወረውራል፣ በጭካኔ ካራ አንገት ይሰይፋል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጌታ ካልተነሣ፣ ጠላት በጻድቃን ላይ ቀስቱን በመለጠጥ፣ ፍላጻ በመላክ፣ ድንጋይ በመወርወር፣ ሰላምን በማወክ ምድርን ያሸብራል! ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር ዝም ሲል፣ ጠላት ይፈነጫል! ዳንኪራ ይረግጣል፣ የጻድቃንን ደም በማፍሰስ፣ ጠጥቶ ይሰክራል!

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር በኃይሉ ሲነሣ ግን ጠላቶቹ ይወድቃሉ! እግዚአብሔር በኃይሉ ሲነሣ ጠላቶቹ ከፊቱ ይሸሻሉ! እግዚአብሔር ሲነሣ፣ ጢስ በንኖ እንደሚጠፋ ሁሉ ጠላቶቹ በንነው ይጠፋሉ! ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ ሁሉ እግዚአብሔር ሲነሣ ጠላቶቹ ይቀልጣሉ!

ወገኖች ሆይ፣ የጠላት ብርታት፣ የጻድቃን መከራ መብዛት ምክንያቱ የእግዚአብሔር አለመነሣት ነው! በዓለም ዙሪያ ባሉ በጻድቃን ላይ መከራ የበዛው፣ ደማቸው በከንቱ እየፈሰሰ በአፈርና ወንዝ ጋር የሚቀላቀለው፣ ጌታ ዝም ስላለ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ዝምታ አደገኛ ነው! ጌታ ዝም ካለ፣ ለእኛ ችግር አለው! ጌታ ዝም የሚለው በሕዝቡ አዝኖ ነው! እግዚአብሔር ካዘነ ለእኛ አደጋ ነው! ወገኖች ሆይ፣ ጻድቃን ሲታረዱ ጌታ ዝም ካለ፣ ጻድቃን ከነሕይወታቸው በእሳት ሲቃጠሉ ጌታ ዝም ካለ፣ የሕጻናት ደም በመሬት ላይ እየጎረፈ ጌታ ዝም ካለ – ይኼ አደጋ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአን በጻድቃን ላይ፣ ያሻቸውን ሠርተው፣ ከልካይ ሰው ከሌለ – ይኼ አደጋ ነው! የጻድቃን ሚስቶች በባሎቻቸውና በልጆቻቸው ፊት እርቃን ስትደፈር ከልካይ ሰው ከሌለ – ይኼ አደጋ ነው! የጻድቃን እጆች ወደኋላ ታስሮ፣ እንደ ቄራ ከብቶች በግፍ ሲታረዱ ጌታ ዝም ካለ – ይኼ አደጋ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሌላ ሌላ ነገር ትተን፣ ሌላ ሌላ ሥራ ትተን፣ ንስሐ እንግባ! ወገኖች ሆይ፣ መነቋቆራችንን ትተን፣ መወጋገዛችንን ትተን፣ መካሰሳችንን ትተን፣ እግዚአብሔር እንዲነሣ ወደ እግዚአብሔር እንጩኽ! ወገኖች ሆይ፣ አሕዛብ፣ በእውነት ለጻድቅ ፍሬ እንዳለው እንዲያውቁ፣ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ እንዲሉ – ጌታ እንዲነሣ፣ ወደ ጌታ እንጩኽ

የሕዝቡ ጠላቶች እንዲደመሰሱ፣ የጻድቃን ጠላቶች ከምድር ገጽ ፍጹም እንዲጠፉ ወደ ጌታ እንጩኽ! በጻድቃን ሁሉ ላይ ሰይፋቸውን የሚነቀነቁ፣ በሰይፍ እንዲጠፉ – ጌታ እንዲነሣ፣ ወደ ጌታ እንጩኽ።፣ በቆፈሩት ጉድጓድ ራሳቸው እንዲገቡ – ጌታ እንዲነሣ ወደ ጌታ እንጩኽ

ትምህርቱ ጠቅምዎት ከሆነ፣ ላይክ ያድርጉ! ጌታ ይባርክዎ!